በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ አቅራቢያ ሁለት ሽጉጥና ሐሰተኛ ፓስፖርት ይዞ የተገኘው ግለሰብ ታሰረ

ዶናልድ ትራምፕ በካሊፎርኒያ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ባሉበት መድረክ አቅራቢያ ሁለት ያልተመዘገቡ ሽጉጦች ይዞ ተገኝቷል የተባለው ግሰለብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ ገለፀ።

የ49 ዓመቱ ተጠርጣሪ ቬም ሚለር ጥቁር መኪና እየነዳ ሳለ ነው በፖሊስ እንዲቆም ታዞ ፍተሻ የተደረገበት። ፖሊስ ከመኪናው ውስጥ ሁለት ሽጉጥ እና “ብዙ ጥይቶች ያሉት ካርታ” ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።

በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ አሳውቀዋል።

የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሲክሬት ሰርቪስ ግለሰቡ ለትራምፕ “አደጋ የሚሆን አይደለም” ብሎ ምንም ዓይነት ግርግር እንዳልተፈጠረ አስረድቷል።

የአካባቢው ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋለውን ግለሰብ “ወፈፌ” ሲሉ የገለፁት ሲሆን የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ታዳሚዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደገነም ብለዋል።

ነገር ግን አሁንም በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም።

የሪቨርሳይድ ክፍለ ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ተጠርጣሪው ምን ዕቅድ እንደነበረው ማወቅ ከባድ ቢሆንም ግለሰቡ ግን ፖሊስ ፕሬዘደንቱን ከሶስተኛ የግድያ ሙከራ እንደታደጋቸው ነው “የሚያምነው” ይላሉ።

ኃላፊው አክለው የግለሰቡ ሐሳብ የግድያ ሙከራ ማድረግ ይሁን አይሁን ግን ማወቅ ከባድ መሆኑን ገልፀዋል።

ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር የዋለው በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 11፡00 ሲሆን ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ አንድ ሰዓት ቀርቷቸው ነበር።

የአሜሪካ ምርጫ ድምፅ መስጫ ቀን ሶስት ሳምንታት ይቀሩታል። በየቦታው እየዞሩ የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረጉ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ ከባድ የሚባል ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው።

የቀድሞው ፕሬዝደንት ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው እንደነበር ይታወሳል።

የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ አክለው እንደገለፁት ተጠርጣሪው አክራሪ የቀኝ ዘመም ቡድን የሆነው ሶቨሬይን ሲቲዝንስ አባል እንደሆነ ተናግሯል። ተጠርጣሪው የያዘው መኪና የመለያ ቁጥር (ታርጋ) የሚጠቁመውም ይህን ብለዋል።

“ታጣቂ ቡድን ነው ማለት ይከብደኛል። በመንግሥት እና በመንግሥት ቁጥጥር የማያምን ቡድን ነው ማለት ይቀላል። በመንግሥት አያምኑም፤ ሕግ አይገዛንም ብለው ነው የሚያምኑት” ይላሉ ኃላፊው።

ትራምፕ ከአንድም ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ስለተደረገባቸው ሲክሬት ሰርቪስን ጨምሮ ኤፍቢአይ እና ሌሎች የደኅንነት ጥበቃቸውን አጠናክረው ይጠብቋቸዋል።

ከወራት በፊት ወደ ፔንሲልቬኒያ ግዛት አቅንተው በትለር በተባለ ሥፍራ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ የተተኮሰባቸው ጥይት ጆሯቸውን ጨርፎ ማለፉ ይታወሳል። የግድያ ሙከራ ያደረገው ግለሰብ በደኅንነት ሰዎች ሲገደል በክስተቱ አንድ የትራምፕ ደጋፊ ሕይወቱን ማጣቱ አይዘነጋም።

ባለፈው መስከረም ደግሞ ዌስት ፓልም ቢች በሚገኘው ጎልፍ ክለባቸው ሳሉ አንድ ተጠርጣሪ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘቱ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየደረገበት ይገኛል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)