የሐማሱ ምክትል መሪ ከቢቢሲ ጋር ያደረጉት ሞጋች ቃለ-ምልልስ

ከሐማስ ነባር መሪዎች መካከል አንዱ የሆነት ኻሊል አል-ሀያ ለቢቢሲ ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል። ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰው እና ቡድናቸው ያስጀመረው ጦርነት ምክንያታዊ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ከቢቢሲው ጄሬሚ ቦዌን ጋር ቆይታ ያደረጉት የሐማስ ምክትል መሪ ኻሊል አል-ሀያ ከአንድ ዓመት በፊት ቡድናቸው እስራኤላውያን ሰላማዊ ዜጎችን አልገደለም ሲሉ ያስተባብላሉ። ነገር ግን መረጃዎች የሚጠቁሙት ሌላ ነው።

ባለፈው ዓመት መስከረም 26 (ጥቅምት 7/2023) ሐማስ በእስራኤል ምድር ላይ በፈጸመው ጥቃት አብዛኞቹ ሲቪል የሆኑ 1200 ሰዎች ተገድለዋል። ቡድኑ ከ250 በላይ ሰዎች አግቶ ወደ ጋዛ ወስዷል።

ሐማስ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች አገራት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ ተፈርጇል።

ቃለ-ምልልሱ የተካሄደው አብዛኞቹ የሐማስ ፖለቲካዊ አመራሮች በሚኖሩባት የኳታሯ መዲና ዶሃ ነው።

እስራኤል ባለፈው ሐምሌ ኢስማኢል ሃኒያህን መግደሏን ተከትሎ ኻሊል አል-ሀያ ከጋዛ ውጪ ካሉ የሐማስ መሪዎች ነባሩ ሆነዋል። እነሆ ቃለ-ምልልሱ።

ቢቢሲ፡ አንድ ዓመት ወደኋላ ተመልሰን ሁኔታውን እንቃኘው። ሐማስ እስራኤልን ያጠቃው ለምንድነው?

ኻሊል፡ ድምፃችንን ለዓለም ማሰማት ነበረብን። ዓለም ምክንያት ያለን፤ ጥያቄ የያዝን መሆኑን ሊያውቅ ይገባል። ጥቃቱ ለፅዮናዊው ጠላት እስራኤል ኪሳራ ነበር። ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደግሞ የማንቂያ ደወል ነው። ለአስርት ዓመታት በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ያለ ሕዝብ እንዳለ ለዓለም ሕዝብ ማሳወቅ ነበረብን።

ቢቢሲ፡ ለምንድነው አባሎቻችሁ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች የገደሉት?

ኻሊል፡ ተዋጊዎቻችን ሰላማዊ ሰዎች እንዳትገድሉ የሚል ትዕዛዝ ሰጥተናቸዋል። በተለይ ሴቶች እና ሕፃናት። ዒላማችን የነበሩት ወታደሮች ናቸው። ሁሌም ጋዛ ውስጥ ሰዎችን የሚገድሉ፣ ቦምብ የሚጥሉ እና ጋዛን የሚያጠፉ ወታደሮች። ሰላማዊ ዜጎችን መግደል ትክክል ነው ብለን አናምንም።

ነገር ግን መሬት ላይ ስህተት ሠርተናል። ምናልባትም ተዋጊዎቻችን ሕይወታቸው ስጋት ላይ እንደወደቀ ተሰምቷቸው ይሆናል።

ቢቢሲ፡ የእርስዎ ተዋጊዎች ምንም አደጋ አልነበረባቸውም። የእርስ ወታደሮች መሬት ላይ ከተቀመጡ እና ካልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ጋር ነበሩ። ይህ ውጊያ አይደለም።

ኻሊል፡ ሁላችንም እንዴት ተዋጊዎቻችን ወደ ሰዎች ቤት እንደገቡ አይተናል። ከቤተሰቦች ጋር ሲያወሩ፤ የበሉትን በልተው የጠጡትን ሲጠጡ ነበር።

ቢቢሲ፡ በጣም ይቅርታ ግን እየተኮሱ ነበር። ይህን የሚያሳዩ ቪድዮዎች አሉ።

ኻሊል፡ ወደ አንዳንድ ቤቶች ሲገቡ ሕፃናት እና ሴቶች ምንም ፍርሃት አልነበረባቸውም። አንተ የምትለው ቪድዮ በእስራኤል የተቀነባበረ ነው። እኛ ያወጣነው ቪድዮ አይደለም።

ቢቢሲ፡ እሺ ቀጥለን ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. በኋላ የተከሰተውን እንመልከት። ይኸው ከአንድ ዓመት በኋላ ጋዛ ፈራርሳለች። ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በርካቶቹ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው። የእርስዎ ቡድን እስራኤልን የመዋጋት አቅሙ ተዳክሟል። ግጭት መቀስቀሳችሁ ትክክል ነበር? ይሄ ይሆናል ብላችሁስ ጠበቃችሁ ነበር?

ኻሊል፡ ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂው ማነው? ወራሪው ኃይል እና ወታደሮቹ ናቸው። ጋዛን ማነው ያፈራረሳት? ሕዝቧን ማን ነው የገደለው? አሁንስ መጠለያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን እየገደለ ያለው ማነው?

የተቀረውን ዓለም ጠይቅ – ዓለም አቀፍ ሕግ አውጥተናል የሚሉትን ጠይቅ። እኛ ራሳችንን እየተከላከልን ነው ያለነው። ከወራሪው ኃይል 1200 ሰዎች ከተገደሉ እንዴት ነው እስራኤል 50 ሺህ ሰዎችን መግደሏ ምክንያታዊ የሚሆነው? ጋዛን ማፈራረሷ ምክንያታዊ የሚሆነው? በቂያቸው አይደለም ማለት ነው? እነሱ እኛን ገድለው ለመጨረስ ባላቸው ጥማት ነው የሚነሳሱት፤ የመውረር እና የማጥፋት ጥም።

ቢቢሲ፡ እስራኤሎች የጦርነት ሕግን እናከብራለን እያሉ ነው። በርካታ ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉት ሐማስ በሰላማዊ ሰዎች መካከል እየተደበቀ ስለሚዋጋ ነው ይላሉ። ሰላማዊ ዜጎችን እንደ ምሽግ እየተጠቀማችሁም ነው ይላሉ።

ኻሊል፡ ይህ ፍፁም ሐሰት ነው። መስጂድ አውድመዋል። ውስጡ ተዋጊዎች አልነበሩም። መኖሪያ ቤቶች አወድመዋል፤ ሕንፃዎችን አፈራርሰዋል። በውስጣቸው ማንም አልነበረም። ቤቶች ላይ ቦምብ ሲጥሉ በውስጡ ማንም ተዋጊ አልነበረም። ይህ የእስራኤል ፕሮፖጋንዳ ነው።

ቢቢሲ፡ ስለታገቱት ሰዎች ማውራት እንችላለን? ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ ከ250 በላይ ሰዎች አግቶ መውሰድ አስፈላጊ ነበር?

ኻሊል፡ የጥቃቱ አንዱ ዓላማ የነበረው ጥቂት የእስራኤል ወታደሮችን አግቶ በእስር ላሉ ፍልስጤማውያን ማስፈቻ ማዋል ነበር። ነገር ግን የጋዛ ክፍል በተዋጊዎቻችን ፊት አመድ ሲሆን በርካታ ታጋቾችን ወሰድን። ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎችን ማገት ዓላማችን አልነበረም።

ቢቢሲ፡ ከታገቱት ሰዎች መካከል የተወሰኑ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብናል ይላሉ።

ኻሊል፡ የተዋጊዎቻችን እና የሁሉም ፍልስጤማውያን ሥነ-ምግባር ሰብዓዊነት ነው። የእስልምና ሃይማኖት እና ባሕል እንዲሁም ብሔራዊ ሥልጣኔን ተምረን ነው ያደግነው። ራሳችንን እንደምንጠብቀው ሁሉ እንጠብቃቸዋለን። ወሲባዊም ሆኑ ወሲባዊ ያልሆኑ ጥቃቶች የሚባሉት ውሃ የማያነሱ ናቸው።

ቢቢሲ፡ አይደለም። አንዳንድ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብናል ብለዋል። በተለይ በኖቫ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ የተሳተፉ ወጣት ሴቶች። በጥቃቱ ዕለት እና ከዚያ በኋላ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብናል የሚሉ ሴቶች ቁጥር በርካታ ነው። ማስረጃም አለ።

ኻሊል፡ እንዳልኩህ መመሪያው ግለፅ ነበር። በአንዳንድ ኃላፊነት በጎደላቸው ሰዎች አስነዋሪ ድርጊቶች ተፈፅመው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አልተረጋገጠም።

ቢቢሲ፡ የተኩስ አቁም ጉዳይስ? እስራኤል በትክክለኛው መንገድ ከተሄደ የተኩስ አቁም ስምምነት እፈርማለሁ ብላለች። የታገቱ ሰዎችን መልሳችሁ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈርሞ ጦርነቱ ቢቆም – ይሄን ይቀበላሉ? በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት እንደነበር አውቃለሁ።

ኻሊል፡ ጥያቄው መቼ ነው ኔታኒያሁ ጦርነቱን የሚያቆመው? የሚል ነው። መቼ ነው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጦርነቱን እንዲያቆም የሚያስገድደው? ጦርነቱን የማቆም ጉዳይ ይሄ የኔታኒያሁ እና የወራሪዊ የእስራኤል ውሳኔ ነው።

ቢቢሲ፡ እናንተም ልታደርጉት ትችላላችሁ። እጃችሁን መስጠት ትችላላችሁ።

ኻሊል፡ እንዴት ነው እጃችንን የምንሰጠው? ወረራን የሚቃወሙ ሰዎች እጃቸውን አይሰጡም። በፍፁም የሚሆን ባይሆንም እኛ እንኳ እጃችን ብንሰጥ ልጆቻችን እና ሕዝባችን እጁን አይሰጥም።

ለምንድን ነው እጃችንን የምንሰጠው? ወራሪው ኃይል መግደሉን ማቆም አለበት። ባለፈው ሐምሌ የተኩስ አቁም ሊደረስ ነበር። ማነው አዲስ ቅድመ ሁኔታ ይዞ የመጣው? ኔታኒያሁ አይደለምን? ከስምምነት ያልደረስነው ለዚህ ነው።

ቢቢሲ፡ ጦርነቱን እየተሸነፋችሁ ነው። ጋዛ ፈራርሳለች። በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል። እስራኤል ደግሞ ወደ ሊባኖስ እያቀናች ነው። ጠንካራ ሆናለች። ጦርነቱን እያሸነፋችሁ አይደለም። አይደል እንዴ?

ኻሊል፡ ቤተሰቦቼ፣ ልጆቼ፣ ዘመዶቼ እና ጎረቤቶቼ ጋዛ ነው ያሉት። የሚያዩትን እናያለን። ስቃያቸው ይሰማናል። ቁስላቸው ያመናል። እነሱን የሚያማቸው እኛንም ያመናል።

ዓለም ሕጋዊ የሆነ መብታችንን ቢሰጠን ግጭቱ ይቆም ነበር። ነገር ግን እስራኤል ይህን አትፈልግም። ዓለም ሊረዳው የሚገባው ነገር እስራኤል ቀጣናውን ማውደም እንደምትፈልግ ነው።

ፍልስጤማውያን አገር የመመሥረት መብታቸውን ካላስከበሩ፤ የስደተኞች መመለስ ካልተከበረ እና የራሳችንን ዕድል በራሳችን መወሰን ካልቻልን ቀጣናው ሰላም አይሆንም። የትኛውም ሞት እና ግድያ ይሄን አያስቆመውም።

ቢቢሲ፡ ለእርስዎ እስራኤል የምትባል አገር ወደፊት ትኖራለች? የሐማስ መመሪያ ፅዮናዊቷ አገር መጥፋት አለባት ይላል።

ኻሊል፡ እኛ የምንለው እስራኤል ሐማስ እና የፍልስጤም ሕዝብን ማጥፋት ትፈልጋለች ነው።

እስራኤል ሐማስ እና የፍልስጤም ሕዝብ ሊያጠፉኝ ይፈልጋሉ ስትል ለቅሶ ታሰማለች። እስቲ እስራኤላውያን ስለፍልስጤም ሕዝብ ምን እንደሚያስቡ እንጠይቃቸው። መብታችንን ስጡን። ራሷን የቻለች አገረ ፍልስጤምን ስጡን።

ቢቢሲ፡ እስራኤሎች የሁለት አገራት መፍትሔ የማይቀበሉት እንደ እርስዎ ያሉ ሰዎች ሊያጠፉን፤ ሕዝባችንን ሊገድሉ ይፈልጋሉ በማለት ነው።

ኻሊል፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ እስራኤል ምንም ዓይነት አገር እንዲፈጠር አትፈልግም። እስራኤል ሁሉንም ሐሳቦች ውድቅ አድርጋለች። ዓለም አቀፍ መፍትሔዎችን፣ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እና የእኛን መብት ውድቅ አድርጋለች።

ቢቢሲ፡ እስራኤሎች ሽብርተኛ ነው ይሉዎታል። እርስዎ ሽብርተኛ ነኝ ብለው ያስባሉ?

ኻሊል፡ እኔ ነፃነት ነው የምፈልገው። ሕዝቤን መጠበቅ ነው የምፈልገው። ለወራሪው ኃይል ሁላችንም ሽብርተኞች ነን። መሪውም ሆነ ሕፃናትና ሴቶች ሽብርተኛ ናቸው። እስራኤላዊያን መሪዎች ምን ብለው እንደሚጠሩን ሰምተሃል። እነሱ እንስሳት ናቸው ብለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)