ሩሲያዊው የፑቲን ተቃዋሚ ለዩክሬን ሲዋጋ ተገደለ

አንድ ዝነኛ የፖለቲካ መብት ተቆርቋሪና የፑቲን ተቃዋሚ ሩሲያዊ ለዩክሬን ተሰልፎ ሲዋጋ በአውደ ውጊያ ተገደለ።

ኢልዳር ዳዲን በሚል ስም የሚታወቀው ሥመ ጥሩ ተቃዋሚ የተገደለው ከሰሞኑ በነበረ ፍልሚያ ነው።

የርሱን ሞት ይፋ ያደረገው ሲቪክ ካውንስል ለቢቢሲ እንደገለጸው ”የዳዲን ሞት የጀግና ሞት ነው፤ ጀግንነቱ ሲዘከር ይኖራል” ብሏል።

የመብት ተቆርቋሪው ተዋጊ በበጎ ፈቃደኛ ታጋዮች ባታሊዮን ሥር ሆኖ የገዛ አገሩን ሩሲያን ሲዋጋ ነበር።

ዳዲን በካርኪቭ ክልል፣ ሰሜን ምሥራቅ ዩክሬን ግንባር በአውደ ውጊያ ላይ ሳለ ከሩሲያ ኃይሎች በተተኮሰ መድፍ እንደተገደለ ነው የተዘገበው።

አንዲት በስደት የምትኖር የፖለቲካ ተቃዋሚ ሩሲያዊት የዳዲንን መሞት ለቢቢሲ አረጋግጣለች።

ኢልዳር ዳዲን በሩሲያ ሰላማዊ ተቃውሞዎችን በመምራት የሚታወቅ ሰው ነበር። እርሱን ለማጥቃት እንደወጣ የሚነገር አንቀጽ 212.1 ለመታሰር የመጀመርያው ሲሆን ዛሬም ድረስ ይህ አንቀጽ በተለምዶ “የዳዲን አንቀጽ’ ተብሎ ይጠራል።

ይህ የሕግ አንቀጽ ተደጋጋሚ ተቃዋሚ ሰልፎችን የሚያዘጋጁ ዜጎችን የሚቀጣ ነው። ይህ አደባባይ መፈክር ይዞ መቆምን የሚጨምር ነው።

ኢልዳር ዳዲን በዚህ አንቀጽ ሁለት ዓመት ተኩል የታሰረ ሲሆን ከዚያ ወዲህ የረሃብ አድማ አድርጎ በማስቸገሩ ምግብ እንዲበላ ለማስገደድ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት ነበር።

በፈረንጆቹ 2017 ከተፈታ በኋላ “በእስር ላይ ሳለሁ የእስር ቤት ፖሊሶች እንደሚደፍሩኝ ያስፈራሩኝ ነበር’ ሲል ያሳለፈውን አስቸጋሪ ጊዜ አብራርቷል። በታሰረበት የእጅ ሰንሰለትም የእስር ቤት ግድግዳ ላይ እንደ ኮት ያንጠለጥሉት እንደነበር መስክሯል።

ከዚህ ሁሉ ስቃይ በኋላ እጄን አጣጥፌ የሩሲያን አስተዳደር ግፍ ልመለከት አልችልም ያለው ዳዲን ፑቲንን ለመጣል ከዩክሬን ጎን ተሰልፎ አገሩን መውጋት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ አምኖ ነበር።

በተደጋጋሚ ‘እጄን አጣጥፌ አልቀመጥም’ ይል እንደነበር ወዳጆቹ ይመሰክራሉ።

ሩሲያ አንዲትን ነጻ አገር መውረሯ ከፍተኛ ጥፋት እንደሆነ ያምን የነበረው ዳዲን ድርጊቱን አምርሮ ይቃወም ነበር ተብሏል።

ከዚህ አልፎ ዳዲን ብቸኛው በክብር የመኖር መንገድ ፑቲንና አስተዳደራቸውን መገርሰስ ነው ብሎ በጽኑ በማመኑ በ2023 የሳይቤሪያ ባታሊዮን ጦርን የተቀላቀለው።

የዚህ ባታሊዯን ምልምሎች ብዙዎቹ በዜግነት ሩሲያዊያን ሲሆኑ ዩክሬን ጋር መሰለፍ ፑቲንን ለመጣል ትክክለኛ አካሄድ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው።

በጦር አውድማ ከተሳተፈ በኋላ ግን በዩክሬን በኩል በቂ ትጥቅና ስንቅ አለመኖሩ ያበሳጨው እንደነበረና በርካታ ዩክሬናዊያን የትግል ባልደረቦቹ ከንቱ ሞት መሞታቸው ያንገበግበው እንደነበር ወዳጆቹ ይመሰክራሉ።

እሱን የመለመላው የሲቪክ ሰርቪስ “ዳዲን ጠንካራ፣ ጀግና፣ የጠራ አቋም ያለውና በሥነ ሥርዓት የታነጸ ታጋይ ነበር፤ የምናስታውሰውም ጀግንነቱን ብቻ ነው” ብሏል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)