ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ለምን “ዝምታን” መረጡ?

የተወካዮች ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም. የሥራ ዘመኑን እንደሚጀምር አስታውቆ ሁለት ቀናት ሲቀሩት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ያጋሩት መልዕክት ግራ መጋባትን ፈጥሮ ባለፉት ቀናት መነጋገሪያ ሆኗል።

ፕሬዝዳንቷ ምን እንደገጠማቸው እና ለምን ያንን ግልጽ ያልሆነ መልዕክት አሁን ማስተላለፍ ፈለጉ የሚለው ምላሽ አላገኘም።

ጉምቱዋ ዲፕሎማት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ወደ ፌደራል መንግሥቱ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን መንበር የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ነበር። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገር ውስጥ እና ከውጪ ከፍተኛ ድጋፍ ባስገኘላቸው እና በርካታ ሴቶችን ወደ አመራርነት ባመጣው ውሳኔ ነው ፕሬዝዳንቷ የተሾሙት።

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለርዕሰ ብሔርነት ሲታጩ በናይሮቢ እና በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታት ኃላፊ እና ተወካይ ሆነው ከዋና ፀሐፊ በመከተል ከፍተኛ ሥልጣን ከነበራቸው የድርጅቱ ሰዎች መካከል አንዷ ነበሩ።

ከስድስት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን ያመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ዲፕሎማቷ ሳህለ ወርቅን ብቻ ሳይሆን በርካታ በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የሳበ ከመሆኑ በተጨማሪ ብዙዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፈቃደኛ እንደነበሩ ይታወሳል።

በመጪው የካቲት 75 ዓመት የሚሆናቸው ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ ታሪክ በአምባሳደርነት ከተሾሙ ሴት ዲፕሎማቶች መካከል ከቀዳሚዎቹ የሚመደቡ ሲሆኑ፣ የሁለት ልጆች እናት ናቸው።

የሳህለ ወርቅ በአዲሱ አስተዳደር ለሥልጣን መታጨት ከተሰማ በኋላ በርካቶች ለአሥርታት በዓለም ዙሪያ በሠሩበት፣ ልምድ እና ዕውቀትን ባዳበሩበት በዲፕሎማሲው መስክ ሊሾሙ እንደሚችሉ ሲገምቱ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊሆኑ እንደሚገባም ሃሳብ ሲሰነዝሩ ነበር።

በዚህም የተነሳ በርዕሰ ብሔርነት ሲሾሙ ቦታው ጉልህ ኃላፊነት እና ሥልጣን የሌለው ነው በማለት የተቹ የነበሩ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ የፕሬዝዳንትነቱን መንበር በመጠቀም የአገሪቱ ምልክት በመሆን በሴትነታቸው እና በልምዳቸው ጠቃሚ ተግባራትን የሚያካነውኑበት ዕድል ሊኖር ይችላል ማለታቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቷን ያስከፋቸው ምንድን ነው?

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ቅዳሜ መስከረም 25/2017 ዓ.ም. በኤክስ ገጻቸው ላይ የታዋቂውን ድምጻዊ የማህሙድ አህመድን የዘፈን ስንኞች በመጥቀስ ያሰፈሩት ግልጽ ያልሆነ መልዕክት በማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮቻቸው ዘንድ ግራ መጋባትን ፈጥሯል።

ቢሆንም ግን ከዘፈኑ ግጥም ውስጥ የመዘዙት ሃሳብ እና ያሰፈሩት መደምደሚያ ግን ፕሬዝዳንቷ “እንደከፋቸው” እና “መሄጃ መውጫ” እንደጠፋቸው፤ ለዚህም መልሳቸው “ዝምታ” መሆኑን ይጠቁማል። በአጭር ጽሁፋቸው ማጠቃለያ ላይም ይህንን የዝምታ አማራጭ “ለአንድ ዓመት” እንደሞከሩት ገልጸዋል።

ቢሆንም ግን ርዕሰ ብሔሯ ዝምታን አማራጭ እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው መገፋት ከየትኛው ወገን እንደገጠማቸው እና ምን እንደሆኑ በግልጽ ያሉት ነገር የለም። ጽህፈት ቤታቸውም ፕሬዝዳንቷ በግል ገጻቸው ላይ ስላሰፈሩት መልዕክት ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጿል።

ቢቢሲ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ቀናት ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ከሥልጣን የመልቀቅ ሃሳብ እንዳላቸው የሚገልጽ መረጃ አግኝቶ በቅርብ ከሚያውቋቸው ሰዎች ለማጣራት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ቢሆንም ግን አሁን ያጋሩት ጽሁፍም ቢሆን ከሥልጣን ስለመልቀቅ የሚያመለክተው ነገር የለም።

ከፕሬዝዳንቷ ጽሁፍ በኋላ ቢቢሲ፤ የቅርብ ወዳጆቻቸው ስለገጠማቸው ነገር የሚያውቁት ነገር ካለ በሚል ሁለት ሰዎችን ጠይቋል። ፕሬዝዳንቷ ባለፉት ዓመታት በዙሪያቸው በሚከናወኑ ነገሮች በተለይም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚካሄዱት ጦርነቶች ደስተኛ አለመሆናቸውን እንደሚያውቁ ከመናገር ውጪ በእርግጠኝነት ይህ ነው ለማለት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት በቅርብ ከሚያውቋቸው ሰዎች መካከል አንደኛው እንዳሉት ፕሬዝዳንቷ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ላይ በሚያደርጓቸው ንግግሮች የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደስተኛ አለመሆናቸውን የሚያመልክት መልዕክት በተዘዋዋሪ እንደሚደርሳቸው አውቃለሁ ብለዋል።

በዚህም የተነሳ ፕሬዝዳንቷ ደስተኛ እንዳልሆኑ እና በተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም በሌሎች ጥቂት ዓመታዊ ዝግጅቶች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከመገናኘት ባሻገር እንደ ርዕሰ ብሔር እና ርዕሰ መንግሥት በሁለቱ መካከል የቀረበ ግንኙነት እና ምክክር እንደሌለ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቷ ያጋሩትን አጭር ጽሁፍ በተመለከተም ሌላኛው የሚያውቃቸው ግለሰብ፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እራሳቸው እንደሚጽፉ እንደሚያውቅ ጠቅሶ፣ ጽሁፉ የራሳቸው ሊሆን እንደሚችል ከመጠቆም ባለፈ ስላሰፈሩት ሃሳብ ከግምት ውጪ መናገር እንደማይችል ለቢቢሲ ገልጿል።

ግምቱም ፕሬዝዳንቷ ቅሬታቸውን በይፋ መጻፍ የፈለጉት ሰኞ መስከረም 27/2017 ዓ.ም. ከሚካሄደው የተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባኤ ንግግራቸው ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ብሏል። በየዓመቱ ምክር ቤቶቹ ሥራ ሲጀመሩ ፕሬዝዳንቷ በአጠቃላይ አገራዊ ሁኔታዎች ላይ እና የመንግሥትን ዕቅድ በሚመለከት ንግግር እንደሚያደርጉ ይታወቃል።

እንደ ቢቢሲ ምንጭ ከሆነ ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ላይ በፕሬዝዳንቷ ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ደስተኛ አለመሆናቸው በማንሳት ምናልባት ዛሬ ሰኞ በሚደረገው የፕሬዝዳንቷ ንግግር ዙሪያ አለመግባባት ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

የመጨረሻቸው ይሆን?

ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ስድስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋባዥነት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ሳይዛመዱ ባላቸው ዝና እና ብቃት ወደ አገሪቱ የተለያዩ የሥልጣን መንበሮች የመጡት ባለሙያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ቀስ በቀስ ከመድረኩ እየራቁ ነው። የቀሩት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል።

ቁልፍ በሚባሉ የኃላፊነት ስፍራዎች ላይ ከነበሩት መካከል የሚጠቀሱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ኮሚሽነሩ ዳንኤል በቀለ በራሳቸው ምክንያት ቦታቸውን ባለፉት ዓመታት በየተራ መልቀቃቸው ይታወሳል።

ከእነዚህ ተሿሚዎች ጋር ወደ አገሪቱ የርዕሰ ብሔርነት የሥልጣን መንበር የመጡት ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቷ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ቀጣይዋ ተሰናባች ሊሆኑ እንደሚችሉ አብረዋቸው የሠሩ እና በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ። ባለፉት ዓመታት “በተለይም ጦርነቶች በሚካሄዱባቸው እና ጥቃቶች በሚፈጸሙባቸው ጊዜያት ሐዘናቸው ከባድ እንደነበረ” ቢቢሲ ያናገራቸው የቅርብ ሰዋቸው ይገልጻሉ።

በተለይ በምክር ቤቶች መክፈቻ እና በአንዳንድ ዓመታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ብቻ ከሚያገኟቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያላቸው ግንኙነት የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑ ፕሬዝዳንቷ ተነጥለው በኢዮቤሊዩ ቤተ መንግሥት እንዲቀሩ እና በመንግሥት ውስጥ ለሚካሄዱ ነገሮች ባዳ ሳያደርጋቸው እንደማይቀር ምንጩ ይናገራሉ።

በትግራይ የተካሄደው ጦርነት በተለይ በሴቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት በእጅጉ እንዳሳዘናቸው በተደጋጋሚ እንደሚናገሩ የሚገልጹት የቢቢሲ ምንጭ፣ ከዚያም ጋር በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የሚካሄዱት ግጭቶችም በጣሙን እንደሚያሳስባቸው እና በቶሎ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ይሻሉ ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ በአንድ ወቅት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ዛሬ የሚሠሩት እስከ ዛሬ በሙያ ሕይወታቸው የገነቡትን እና ያካበቱትን ልምድ እንዳይንድባቸው እንደሚጠነቀቁ ተናግረዋል።

ስለሰላም እና ስለ ሴቶች በተደጋጋሚ ሲናገሩ የሚደመጡት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው አስቸጋሪ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው ታሪክ ሲወሳ “ኢትዮጵያ በእንደዚህ ዓይነት መከራ ውስጥ ስታሳልፍ ሴት ፕሬዝዳንት ነበረች ተብሎ መገምገሜ አይቀርም። ምን ማድረግ እችል ነበር የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው። ነገር ግን ይህንንም መቀበል አለብኝ” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ወደ ሥልጣን የመጡበት የኋላ ታሪክ አገሪቱን ከሚመሩት የፖለቲካ ልሂቃን የተለየ በመሆኑ በአገሪቱ ሕዝቦች መካከል ያለው የብሔር መለያየት እንዲለዝብ እና ለጋራ አገር በአንድነት እንዲቆም በርከት ባሉ አጋጣሚዎች ላይ መክረዋል።

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንዲሁም የተለያየ አገራት ዲፕሎማቶች በተገኙበት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ሲመረቅ ዓድዋ የዘመቱ ኢትዮጵያውያን የተሰባሰቡት በሃይማኖት እና በብሔር ተመራርጠው አለመሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ “አገርን ማዳን ከልዩነታችን በላይ ነው” ሲሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

የአገሪቱ ክልሎች ፕሬዝዳንቶች እና ባለሥልጣናት በታደሙበት በዚያ ዝግጅት ላይ ከርዕሰ ብሔሯ ቀድመው ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የነበሩ ሲሆን፣ ይህም የፕሮቶኮል ጥያቄ በአንዳንዶች ዘንድ እንዲነሳ አድርጎ ነበር።

ፕሬዝዳንቷም ወደ መድረክ በተጋበዙበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከንቲባዋ ካሉት ውጪ የሚሉት ነገር እንደሌለ በመናገር በአገሪቱ የሚከሰቱ ልዩነቶችን ለመፍታት ጠመንጃ ማንሳት መለመዱን “. . . ወንድም ወንድሙ ላይ መነሳት አገር ኩራት አይደለም” በማለት “በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን አለመግባቶች በሰከነ መንገድ ተነጋግሮ መፍታት” አስፈላጊ መሆኑን መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚያጋጥሙት ቀውሶች ፕሬዝዳንቷን በዋናነት የሚያሳስቡ ጉዳዮች መሆናቸውን የሚገልጹት ሌላኛዋ የቅርብ ሰው፣ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሁኔታዎቹ ከመርገብ ይልቅ እየተባባሱ መሄዳቸው ከአንድ ዙር የሥልጣን ዘመናቸው መጠናቀቅ በኋላ በፕሬዝዳንትነት ላይቀጥሉ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

በተለይ ባለፈው ዓመት በተለያዩ አጋጣሚዎች 2017 ጥቅምት ወር የመጨረሻቸው መሆኑን የሚያመለክቱ ነገሮችን ለቅርብ ሰዎቻቸው ጠቆም ያደርጉ ነበር። በእርግጥም የፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያ ዙር ስድስት ዓመት የሥልጣን ዘመን የሚያበቃው በመጪው ጥቅምት ወር ነው።

በፕሬዝዳንትነት ተሰይመው ከሚያገኙት በላይ በመንግሥታቱ ድርጅት የነበራቸው ቦታ የሚያስገኝላቸው ጥቅምን ትተው ወደ ሥልጣን የመጡት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ “ለዚህ ያበቃችኝን አገሬን በማገልገል ውለታዋን የምመልስበት አጋጣሚ ነው” ብለው ያምኑ እንደነበር የሚገልጹት ምንጫችን ምኞታቸውን ምን ያህል አሳክተዋል የሚለውን ግን እርግጠኛ አይደሉም።

ባለፉት ዓመታት መሥራት የሚፈልጉትን ያህል አለማሳካታቸውን በተዘዋዋሪ መረዳት ይቻላል የሚሉት ላለው ምንጭ ምናልባትም አሁን “ሆድ እየባሳቸው” ዝምታን የመረጡት ከዚህ በላይ መቀጠል ስለማይችሉ ጥቅምት ወርን እየጠበቁ ስለሆነ ይሆናል ይላሉ።

የሪፐብሊኩ አራተኛዋ ፕሬዝዳንት

ኢሕአዴግ ሥልጣን ይዞ አዲስ ፌደራላዊ አወቃቀር እና ሕገ መንግሥትን ለአገሪቱ ከቀረጸ በኋላ በነበሩት 30 ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅን ጨምሮ አራት ፕሬዝዳንቶችን ወደ ሥልጣን አምጥቷል።

ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ውጪ ያሉት ሦስቱ ወንዶች ከመሆናቸው በተጨማሪ የኋላ ታሪካቸው በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው። በተለይም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የገዢው ኢህአዴግ አካል የሆነው የኦህዴድ አባላት ነበሩ። መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስም እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ውጪ እምብዛም የማይታወቅ ፓርቲ አመራር ነበሩ።

አራተኛዋ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ከቀደምቶቻቸው በተለየ በዲፕሎማሲው መስክ ለረጅም ዓመታት ከመሥራታቸው በተጨማሪ ከየትኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር የሚታወቅ ግንኙነት አልነበራቸውም። በተጨማሪም በአገሪቱ ታሪክ በፕሬዝዳንትነት ተሰይመው ሥልጣን የየዙ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው።

ይህ የአገሪቱ ፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ግን ከአገር ምልክትነት ባለፈ ጉልህ ውጤት የሚኖረው ውሳኔን ለማሳለፍ የሚያስችል ኃላፊነት በሕገ መንግሥቱ አልተሰጠውም። በዚህም ሳቢያ የአምባሳደር ሳህለ ወርቅ ፕሬዝዳንት መሆን ያላቸውን የዲፕሎማሲ ሙያ እና ልምድ ያባክነዋል ብለው የተቆጩ ጥቂቶች አልነበሩም።

በሕገ መንግሥቱ ፕሬዝዳንቷ በዋናነት የተሰጣቸው ኃላፊነት በሌሎች የመንግሥት አካላት የተላለፉ ውሳኔዎችን ዕውቅና መስጠት ነው። በዚህም የተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቃቸው ሕጐች እና ስምምነቶችን በነጋሪት ጋዜጣ ማወጅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸውን አምባሳደሮች እና መልዕክተኞችን መሾም እንዲሁም ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረጎችን መስጠት ነው።

በተጨማሪ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽኑን ምክር ቤቶችን የጋራ ስብሰበባ በንግግር መክፈት፣ የውጭ አገራት አምሳደሮችን እና የልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደብዳቤ መቀበል፣ ኒሻኖች እና ሽልማቶችን መስጠት እንዲሁም የቀረቡ ሕጋዊ የይቅርታ ጥያቄዎችን መቀበል ይጠቀሳሉ ነው።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)