ጤፍ እና ስንዴ ተቀቅሎ የሚቀለበው የጅሩ ሠንጋ

ለፋሲካ ለገበያ የቀረበው የጅሩ ሠንጋ ዋጋ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞረት እና ጅሩ ወረዳ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ግን ይህ የተለመደ ነው።

በዚሁ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ታደለ አስራት፣ ለዓመት ያህል ያደለቡት በሬ 550 ሺህ ለመሸጥ ማሰባቸውን ገዢ ግን 430 ሺህ ለመክፈል ጠይቆ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንዴት ይህንን ያህል ሊያወጣ ቻለ ተብለው የተጠየቁት አቶ ታደለ “በሬው እኮ የተቀለበው ከአምና ጀምሮ ነው” ይላሉ።

በሬው ይህን ያህል ዋጋ ከመገመቱ በፊት ጤፍ እና ፉርሽካ እየተቀለበ ማደጉንም ጨምሮ ተናግረዋል።

በርግጥ አቶ ታደለ ሲገዙት ጥጃ ሆኖ በ130ሺህ ብር መሆኑንም አልሸሸጉም።

በሬው ዓመት ያህል ሲቀለብ ብቻ ሳይሆን “ሽልም” ብለው እንደሚጠሩትም ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ተናግረዋል።

“በሬው እኮ ሁለት በሬ ያክላል” የሚሉት አቶ ታደለ “ከ500 ኪሎ በላይ ይገመታል” ይላሉ።

‘ሽልም’ የሚያድረው ሊሾ የተደረገ ቤት ውስጥ ነው። የሚመገበው ደግሞ እንደ መሰሎቹ ሳር እና ጭድ ብቻ ሳይሆን፣ ክክ ባቄላ እና የተቀቀለ ጤፍ ጭምር ነው።

‘ሽልም’ አያርስም። በዋናነት በሊሾው ቤቱ ውስጥ ሆኖ አልያም በተከለለት ስፍራ ቅቅል ጤፉን እና ክክ ባቄላውን እየበላ ከጉድጓድ በሚቀዳ ንፁህ ውሃ አልያም አተላ ያወራርዳል።

የደለበ ስለሆነ ራቅ ያለ ቦታ ሄዶ ውሃ አይጠጣም ይላሉ የሽልም አሳዳሪ አቶ ታደለ። ጤንነቱን በባለሙያ ክትትል መንከባከብ ብቻ ሳይሆን ገላውንም እንደሚያጥቡት ገልጸዋል።

“ጠዋት ጸሐይ ይሞቃል፣ ቀን ደግሞ ወደ ማረፍያው ይሄዳል።”

በሞረት እና ጅሩ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ደረጀ አለማየሁ ይህ ከብቶችን የማድለብ ስራ በአካባቢው የተለመደ መሆኑን ይናገራሉ።

አርሶ አደሩ ከብት የማድለብ ባህል ማዳበሩ ብቻ ሳይሆን ወይና ደጋ የሆነው የአየር ጠባይም ለዚህ አጋዥ ሆኗል።

ሞረት እና ጅሩ በሚያደልባቸው የቁም አንስሳት ምክንያት በአገር አቀፍ ደረጃ ስሙ እንደሚነሳ አቶ ደረጀ ይናገራሉ።

“እንደውም በአገር ደረጃ የሚታወቅ ነው። እዚህ አካባቢ የደለበ ከብት በአገር ደረጃ እውቅና የተሰጠው ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ማኅበረሰቡ ከብት የመንከባከብ አቅሙ ዳብሯል” ይላሉ።

አቶ ደረጀ ገበሬው ለሚያደልበው ከብት ጤፍ፣ ስንዴ ቀቅሎ እንደሚመግብ ይህም ለየት እንደሚያደርገው ይናገራሉ።

ነጋዴዎች ከሐዋሳ፣ ከአዳማ፣ ከደሴ እንዲሁም ወልድያ ድረስ መጥተው እንደሚገዙ ይናገራሉ።

አቶ ደረጀ ስለ አካባቢው አርሶ አደር ሲናገሩ የማድለብ ስራውን በባለሙያ ምክር እንደሚያስደግፉ ገልጸው “ግብዓትን እና ቴክኖሎጂን አጣጥሞ የሚያስኬድ ነው” ይላሉ።

በዚህም የተነሳ አርሶ አደሮቹ የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙም ይናገራሉ።

በሞረት እና ጅሩ ወረዳ ስር በሚገኙ ሰባት ደጋ ቀበሌ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ገበሬዎች ያደልባል ይላሉ።

ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ያለው አለመረጋጋት የገበሬው ጥረት ላይ እክል ፈጥሮበታል።

በዚህም የተነሳ በዚህ ዓመት እንደ ከዚህ ቀደሙ ብዙ ገበሬ አለማድለቡን ገልጸዋል።

“ምርቱ ትንሽ ቀንሷል፣ ሰብልም ብዙ አላዘመረም፤ በየቤቱ አንድ ሁለት ማድለብ የተለመደ ነው። በዚህ ዓመት ግን ቁጥሩ ቀነሰ” ይላሉ።

የባቄላ ክክ፣ የተቀቀለ ጤፍ እና ስንዴ የሚቀለቡት በሬዎች በጣም እንደሚደልቡ ተናግረው “አንዳንዶቹን ስታያቸው ፊታቸው ለመቆም ትፈርያለሽ፤ በጣም ግዙፍ ይሆናሉ” ብለዋል።

የጅሩ እና ሞረት አካባቢ በሬ ሻጮች እና ገዢዎች የሚገናኙበት ብቻ ሳይሆን የጅሩ በሬን ጮማ ለመብላትም ሰበብ ፈልጎ የሚመጣ ሰው መኖሩን አቶ ደረጀ ይናገራሉ።

“እህል ስለሚበሉ ስጋው በጣም ይጣፍጣል። ለየት የሚያደርገውም ይህ ጥፍጥናው ነው።”

አቶ ደረጀ በሳይንሱ አንድ በሬ መቀለብ ያለበት ሦስት ወይንም አራት ወር ብቻ ቢሆንም በአካባቢው ግን ለአንድ አመት ያህል እየቀለቡ ማደለብ የተለመደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ ፋሲካ አንድ ወር ሲቀረው ጤፍ ቀቅሎ በመመገብ ኪሏቸው እንዲጨምር፣ አካላቸው እንዲጠብቅ ያደርጋሉ ሲሉም የአርሶ አደሩን ጥረት ይመሰክራሉ።

እንዲህ መኝታ ተለይቶለት፣ ንፁህ በልቶ ጠጥቶ፣ ሕክምና ተከታትሎ የደለበ በሬ ምን ያህል ይመዝናል ብለው ይገምታሉ የቢቢሲ ጥያቄ ነበር “ከ600 እስከ 700 ኪሎ ይሆናል” ደግሞ የእርሳቸው ግምት።

ገበሬው የሚያደልበውን በሬ የሚያየው ልክ እንደ ልጁ ነው የሚሉት አቶ ደረጀ ምን በላ ምን ጠጣ? ብቻ ሳይሆን ጤንነቱስ የሚለው የዘወትር ጭንቀቱ ነው ይላሉ።

ይህም በገቢ እንዲካስ አድርጎታል ሲሉ ሀሳባቸውን ይጠቀልላሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )