ጋዜጠኛ ሙህዲን ሞሃመድ በሶማሌ ክልል ፍርድ ቤት የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደበት

የሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ሙህዲን ሞሃመድ ላይ የሁለት ዓመት እስራት እንደተፈረደበት የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ገለጸ።

በጋዜጠኛው ላይ የቅጣት ውሳኔው የተወሰነው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሚያዝያ 24፤ 2016 ዓ.ም. ነው።

ይህን የዞኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ በጋዜጠኛው ጠበቃ በኩል መቅረቡን የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አብዱራዛቅ ሀሰን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ተቋም ሲፒጄ ከፋፈን ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማግስት ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የጋዜጠኛ ሙህዲን ሞሃመድ አብዱላሂን ይግባኝ እንዳይቃወሙ” ጥሪ አቅርቧል።

ጋዜጠኛው የተከሰሰበት ወንጀል “የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ” በማሰራጨት መሆኑን ሲፒጄ ባወጣው መግለጫ ገልጿል። ተቋሙ ለጉዳይ ቅርበት ያላቸውን ግለሰብ ጠቅሶ ሙህዲን ክስ የተመሰረተበት “ሙህዲን ሾው” በተሰኘ የፌስቡክ ገጹ ካሰራጨው ልጥፍ ጋር የተገናኘ መሆኑን አስታውቋል።

ሲፒጄ ጋዜጠኛ ሙህዲን አሁን በተሰረዘ የፌስቡክ ልጥፍ “ህዝቡን እያነሳሳ ነበር” ማለታቸውን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ሙህዲን በጅግጅጋ ከተማ “ማንነታቸው ባልታወቁ የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ ሙህዲን ወደ አካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ከመዘዋወሩ በፊት ለስድስት ቀናት በማይታወቅ ሁኔታ ታስሮ እንደነበር” ሲፒጄ ገልጿል።

ጋዜጠኛ ሙህዲን በክልሉ ዋና ከተማ ጂግጂጋ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የካቲት 4፤ 2016 እንደነበር አቶ አብዱራዛቅ ተናግረዋል። ሙህዲን በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከአንድ ወር ገደማ በፊት መጋቢት 30/ 2016 ዓ.ም. በ40 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር አንዲፈታ ቢወሰንለትም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አለመከበሩን አቶ አብዱራዛቅ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ “ላለፉት ሶስት ወራት በእስር ላይ የሚገኘው ሙህዲን ላይ የተላለፈው የሁለት ዓመት የእስር ቅጣት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን አሳዛኝ የመገናኛ ብዙሃን አፈና የሚያስታውስ ነው” ብለዋል።

አስተባባሪዋ አክለውም “ዐቃቤ ህግ የሙህዲንን የይግባኝ አቤቱታ መቃወም የለባቸውም፤ ባለስልጣናትም ጋዜጠኞች በሚሰሩት ጠንካራ ዘገባ እና በሚሰጡት አስተያየት ለእስር አለመዳረጋቸውን ማረጋገጥ አለባቸው” ብለዋል።

በሲፒጄ የ2023 ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት በርካታ ሁለተኛዋ የጋዜጠኛ አሳሪ ሀገር ናት። እስካለፈው ታህሳስ ወር ድረስ ስምንት ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ የተቋሙ ሪፖርት ያሳያል።

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (RSF) ባለፈው ሳምንት አርብ ባወጣው የሀገራት የፕሬስ ነጻነት ደረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከነበራት ሰባት ደርጃዎችን አሽቆልቁላለች። ባለፈው ዓመት ከ180 ሀገራት 130ኛ የነበረችው ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 141ኛ ደረጃ አግኝታለች።

የተቋሙ መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ አራት ዓመታት በፕሬስ ነጻነት ደረጃ እያሽቆለቆለች ትገኛለች። በአውሮፓውያኑ 2020 ኢትዮጵያ 99ኛ ደረጃ አግኝታ የነበረ ሲሆን ሲሆን በአራት ዓመታት ውስጥ 42 ደረጃዎችን አሽቆልቁላ በ2024/ 141ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን አስመልክቶ በአዲስ አበባ የሚገኙ 18 ኤምባሲዎች ባወጡት መግለጫ “ሥራቸውን ሲሰሩ ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ የታሰሩ” ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ጠይቀው ነበር።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትን ጨምሮ በጋራ መግለጫ ያወጡት ኤምባሲዎች “የፕሬስ ነጻነት አስፈላጊነት እንዲሁም እውነትን ለመዘገብ ያለመታከት የሚሰሩ መገናኛ ብዙኃንን እና ጋዜጠኞችን የመከላከል አስፈላጊነትን ያስታውሳል” ብለዋል።

ይህ የኤምባሲዎቹ መግለጫ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ እኔ አውቅልሀለሁ የሚል የጋራ መግለጫ ለሁለትዮሽ ግንኙነት የሚበጅ አይደለም፤ እንዲሁም በአገሪቱ ያለውን የሕግ የበላይነትን ማስከበር ዝቅ የሚያደርግ ነው” ሲል የኤምባሲዎቹን የጋራ መግለጫ አጣጥሎታል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ መግለጫው ላይ “ [ኤምባሲዎቻቸው] በሚገኝበት አገር ጋር እንዲህ ያለ ግንኙነት ፍሬያማ ያልሆነ እና ከተለመደው የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚቃረን ነው” ሲል ገልጾታል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )