የፑቲን ቀንደኛ ተቃዋሚ የነበረው ናቫልኒ “እስር ቤት ሊሞት እንደሚችል” ያውቀው ነበር

ባለፉት 10 ዓመታት በሩሲያ ቀንደኛ ከሚባሉ የመንግሥት ተቃዋሚዎች መካከል አንዱ የነበረው አሌክሲ ናቫልኒ እስር ቤት ውስጥ ሊሞት እንደሚችል ያውቀው እንደነበር የሕይወት ታሪኩን የሚዳስሰው መፅሐፍ ጠቆመ።

የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ቀንደኛ ነቃፊ የነበረው ናቫልኒ ባለፈው ዓመት የካቲት ነበር እስር ቤት ውስጥ ሳለ የሞተው።

ናቫልኒ ፅንፈኛ አቋም በማሳየት 19 ዓመት እስር ተፈርዶበት ወደ አርክቲክ ሰርክል እስር ቤት ሲላክ ብዙዎች ፍርዱ ፖለቲካዊ ነው ሲሉ መቃወማቸው ይታወሳል።

ዘ ኒው ዮርከር እና ታይምስ የተባሉት ጋዜጦች በቅርቡ ለንባብ ከሚበቃው መፅሐፍ የተወሰነውን ያሳተሙ ሲሆን፣ መፅሐፉ የናቫልኒን የመጨረዎቹን ዓመታት ይዘክራል።

“ከዚህ በኋላ ያለውን ሕይወቴን እስር ቤት ውስጥ ነው የምኖረው፤ የምሞተውም እዚሁ ነው” ሲል በአውሮፓውያኑ መጋቢት 22/2022 ፅፎ ነበር።

“ደኅና ሁኑ የምላቸው ሰዎች የሉኝም. . . ሁሉም በዓላት ያለእኔ ይከበራሉ። የልጅ ልጆቼን አላያቸውም።”

ናቫልኒ በ2024 የአውሮፓውያኑ ዓመት መባቻ ሞቱ ሲነገር በርካቶች በድንጋጤ እና በሐዘን ነበር ዜናውን የተቀበሉት። በፖለቲካ ሕይወቱ ላበረከተው አስተዋፅዖ አድናቆት ጎርፎለታል።

ብዙዎች ለሞቱ ፕሬዝደንት ፑቲንን ተጠያቂ ያደረጉ ቢሆንም፣ ሞቱ ከተሰማ በኋላ መግለጫ ያወጣው የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ክሬምሊን ስለሞቱ መስማቱን ከማሳወቁ ውጪ ያለው ነገር አልበረም።

ናቫልኒ ነሐሴ 2020 ወደ ሳይቤሪያ እስር ቤት በተወሰደበት ወቅት ኖቪቾክ በተባለ ነርቭ አጥቂ ንጥረ ነገር ተመርዞ እንደነበር ይታወሳል።

‘ፓትሪዮት’ ሲል የሰየመውን የሕይወት ታሪኩን የሚዘክር መፅሐፍ መፃፍ የጀመረው ጀርመን ሕክምና እየተከታተለ ሳለ ነበር።

ከሕክምናው ካገገመ በኋላ ጥር 2021 ወደ ሩሲያ መዲና ሞስኮ እንደተመለሰ ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር ዋለ። ናቫልኒ የቀሩትን 37 ወራት እስር ቤት ነበር ያሳለፈው።

ተቃዋሚው ፖለቲከኛ ጥር 2022 “ሊያስፈራን የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር እናት አገራችን በዋሾዎች፣ በወንበዴዎች እና በግብዞች መመራቷ ነው” ሲል ፅፏል።

መፅሐፉ የጤናው ሁኔታ እያሽቆለቆለ ሲመጣ፤ እስር ቤት ሳለ የነበረው ብቸኝነት እንዲሁም ጨዋታ አዋቂነቱን ያዘለ ነው ሲሉ ጋዜጣዎቹ አስነብበዋል።

ፓትሪዮት የተባለው መፅሐፍ በዚህ ወር [ጥቅምት] ለበገያ ይቀርባል። አሜሪካ የሚገኘው አሳታሚ ድርጅት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመውን መፅሐፍ በሩሲያ ቋንቋም ለማሳተም አቅዷል።

ኒው ዮርከር እንደዘገበው ናቫልኒ እስር ቤት ሳለ በቡድኑ አባላት በኩል ከመፅሐፉ ላይ እየቆነጠረ በማኅበራዊ ሚድያው ላይ ይለጥፍ እንደነበር ዘግቧል።

ጋዜጣው አክሎ ናቫልኒ እስር ቤት ሳለ ሌሎች እስረኞች እና የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ለምን ወደ ሩሲያ ተመለስክ ብለው እንደሚጠይቁት ፅፏል።

ምላሹ ይላል ናቫልኒ “አገሬ ላይ ተስፋ መቁረጥ አልፈልግም፤ ልክዳትም አልፈልግም። ለአንድ ነገር ቁርጠኛ ከሆናችሁ በዓላማችሁ ልትፀኑ ይገባል፤ አስፈላጊ ከሆነ መስዋዕትነትም መክፈል አለባችሁ።”

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)