የጃፓን መንግሥት የሚኒስትሮችን ‘ከርፋፋ’ የቡድን ፎቶ ማስዋቡን አመነ

መጀመርያ በጋዜጠኞች የተነሳው ፎቶ ላይ ያሉ ግድፈቶች በኋላ በጥንቃቄ መስተካከላቸው በጃፓን ማኅበራዊ ተጠቃሚዎች ዘንድ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ሚኒስትሮቹ በጋራ በተነሱት በዚህ የቡድን ፎቶ ላይ ብዙዎቹ አዲስ ተሿሚዎች ልብሶቻቸው ከርፈፍ ብለው ይታያሉ። ይህ ግን በጋዜጠኞች በተነሱ ፎቶዎች ላይ ነው የተጋለጠው።

በተለይም አዲሱ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺገሩ ኢሺባ እና መከላከያ ሚኒስትራቸው ነጭ ቲሸርታቸው ከለበሱት ጥቁር ቶክሲዶ ሾልኮ ወጥቶ ተንከርፍፎ ይታይ ነበር።

ይህም በማኅበራዊ ሚዲያ ለቧልት በር ከፍቶ ቆይቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሐሙስ ዕለት በይፋ ገጹ ባተመው ተመሳሳይ ምስል ሁሉም ነገሮች ተስተካክለው መውጣታቸው ነገሩ ይበልጥ እንዲጋጋል ምክንያት ሆኗል።

ከብዙ የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳልቆት እና ቧልት በኋላ መንግሥት ትናንት ሰኞ “አዎ፣ ፎቶው እንዲያምር በስሱ ነካክቼዋለሁ” በሚል ድርጊቱን አምኗል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ዮሺማሳ ሐያሲ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ‘በፎቶው ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገው በቢሮው የሚነሱ ፎቶዎች ለረዥም ዘመን ማኅደር ውስጥ ስለሚቀመጡ ነው” ብለዋል።

“መለስተኛ ማስተካከያ ፎቶዎች ላይ ማድረግ ደግሞ ያለና የነበረ ነው” ብለዋል።

ይህ አስተያየታቸው የመጣው ጃፓናዊያን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በፎቶ ላይ ማስተካከያ ማድረጉን ባለማመኑ ብዙ ከተሳለቁበት በኋላ ነበር።

አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ “ሚኒስትሮቹ የተሰፋላቸው ሱፍ በልካቸው አይደለም” በማለት እንዲያስጠብቡት መክራለች።

ሌላ ጃፓናዊ በኤክስ ገጽ በሰጠው አስተያየት ደግሞ የሚኒስትሮቹ ሱሪ ከሰውነታቸው ጋር “አልመጠኑም” (Ill -fitting) ሲል ‘ለፖለቲካውም አትመጥኑም’ የሚል ትርጉም ያዘለ አሽሙራዊ አስተያየት ሰጥቷል።

ይህ የቡድን ፎቶ የተነሳው ሐሙስ በጃፓን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱን ካቤኒያቸውን ሰይመው የመጀመርያ ስብሰባቸውን ካደረጉ በኋላ ነው።

በጃፓን የ67 ዓመቱ ኢሺባ ተሰናባቹን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳን ተክተው የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበር መሆናቸው ይታወሳል።

ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ኢሺባ በይፋ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገው ተሹመዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)