የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ ዓለምን እንዴት ሊቀይር ይችላል?
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአውሮፓውያኑ የካቲት ወር 2023 ለዩክሬን አጋርነታቸውን ለማሳየት ድንገት ከቮሎድሚር ዜሌኒስኪ ጋር በመሆን ኪየቭ ሲደርሱ የአደጋ ጊዜ ደውሎች ከፍ ብለው ይሰሙ ነበር። “ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ . . . የሆነ ነገር ተሰማኝ” ሲል ያስታውሳሉ። “አሜሪካ የዓለም መሪ ናት” ብለዋል።
አሜሪካኖች በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማን ድምጻቸውን እንደሚሰጡ እና ይህችን የዓለም ቁንጮ የሆነች አገር ማን ያስተዳድራታል የሚለውን በጉጉት ነው እየጠበቁ ያሉት።
ካማላ ሃሪስ “በዚህ ባልተረጋጋ ወቅት አሜሪካ ወደ ኋላ እንደማታፈገፍግ ግልጽ ነው” በሚል የፕሬዝዳንት ባይደንን እግር ይተካሉ ወይስ “ሉላዊነት ሳይሆን አሜሪካዊነት ይለምልም” የሚሉት ዶናልድ ትራምፕ ይረከባሉ?
አሜሪካ በዓለም ላይ ያላት ተጽዕኖ ጥያቄ ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት ላይ ነው የምንገኘው።
የቀጠናው ኃያል አገራት በየራሳቸው አቅጣጫ የሚሄዱበት፣ አምባገነን አገዛዞች ቢጤዎቻቸውን እየፈለጉ አጋርነት የሚፈጥሩበት፣ በጋዛ፣ በዩክሬን እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ያሉ አውዳሚ ጦርነቶች ዋሽንግተን ስለሚኖራት ሚና የሚነሱ ፈታኝ ጥያቄዎችን አርግዘዋል።
ነገር ግን በምጣኔ ሀብቷ እና በወታደራዊ አቅሟ እንዲሁም በበርካታ አጋሮቿ ዘንድ ባላት ወሳኝ ሚና ተጽዕኖ ምክንያት ዛሬም እጇ ረዥም፣ መዳፏም ጠንካራ ነው።
ወታደራዊ አቅም
“እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች መቀባባት አልፈልግም” ይላሉ የቀድሞዋ የኔቶ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሮዝ ጉተሞይለር።
“ዶናልድ ትራምፕ በሁሉም ጆሮ ከየሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አባልነታቸው ለመውጣት ደጋግሞ በማስፈራራት የአውሮፓ ቅዠት ሆነዋል።”
የአሜሪካ መከላከያ በጀት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ካሉት 31 አባል አገራት ሁሉ ሁለት ሦስተኛውን ይሆናል።
ከኔቶ ባሻገር አሜሪካ ለመከላከያ ኃይሏ የምታወጣው ቻይና እና ሩሲያን ጨምሮ 10 አገራት ተደምረው ከሚያወጡት ይበልጣል።
ትራምፕ ሌሎች የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አባል አገራት የሚያዋጡትን መዋጮ እንዲከፍሉ ጫና እያደረጉ መሆናቸውን በመግለጽ ይኩራራሉ።
የኔቶ አባል አገራት ከጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸውን 2 በመቶ ማዋጣት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2024 ይህንን ማሳካት የቻሉት 23 አገራት ብቻ ናቸው።
ነገር ግን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አጥብቆ ወትዋችነት በርካቶችን ምቾትን ይነሳቸዋል።
ካማላ ሃሪስ የምታሸንፍ ከሆነ ይላሉ ጎተሞይለር “ኔቶ በዋሽንግተን መልካም እጅ ላይ ይቆያል” የሚል እምነት አላቸው።
ነገር ግን ይህም ቢሆን ስጋት አላቸው።
አሜሪካ “ኔቶ እና የአውሮፓ ኅብረት በዩክሬን ድል እንዲቀናቸው መሥራት ለመቀጠል ዝግጁ ልትሆን ትችላለች። ነገር ግን አውሮፓ የምታዋጣው ላይ ተጽዕኖ ከማድረግ ላትመለስ ትችላለች።”
ነገር ግን በዋይት ሐውስ የሚገኙ የካማላ ሃሪስ ቡድኖች በቅርቡ በሪፐብሊካን እጅ ከሚወድቁት ከሴኔት ወይንም ከኮንግረስ ጋር መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ስለዚህ ልክ እንደ ዲሞክራቶቹ አቻዎቻቸው በሌላ አገር ጦርነት ላይ ለመሳተፍ ያላቸው ፍላጎት አናሳ ሊሆን ይችላል።
የአሜሪካ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ማንም ሆነ ማን፣ ኪየቭ ከዚህ ጦርነት የምትወጣበትን መንገድ እንድትፈልግ ለማድረግ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች የሚሰጡትን ከፍተኛ እርዳታ በመቀነስ ግፊት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ጎተሞይለር ምንም ይሁን ምን ይላሉ “ኔቶ መፈረካከስ አለበት ብዬ አላምን” ስለዚህ አውሮፓ “የመሪነቱን መንበር ለመውሰድ ወደ ፊት መምጣት አለባት” ይላሉ።
ሰላም አስከባሪዋ
ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ የተፈጠረውን እና ዓለም ትልቁ የኃይል ሚዛን ግጭት ስጋትን በሚጋፈጥበት ዑደት መሥራት ይጠበቅበታል።
“አሜሪካ በሰላም እና በደኅንነት ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዋ የጎላ ሆና ትቀጥላለች” ሲሉ የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ፕሬዝዳንት እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኮምፕርት ኤሮ ይናገራሉ።
ማስጠንቀቂያ ሲያክሉ ደግሞ “ነገር ግን ግጭቶችን የመፍታት አቅሟ እየቀነሰ መጥቷል” ይላሉ።
ጦርነቶች ለመቋጨት አስቸጋሪ እየሆኑ መጥተዋል። “ገዳይ ግጭቶች ይበልጥ እያየሉ መጥተዋል፤ የግዙፍ ኃይል እና ጠንካራ የጦር ፉክክር እየተፋጠነ እና መካከለኛ ኃይል ያላቸው ደግሞ እየጨመሩ መጥተዋል” ሲሉ ኢሮ ያለውን ሁኔታ ይገልጻሉ።
እንደ ዩክሬን ያሉ ጦርነቶች ብዙ ኃያላንን ይጋብዛሉ፤ እንደ ሱዳን ያሉ ግጭቶች ደግሞ በቀጠናው እርስ በእርሳቸው የሚፎካከሩ አገራትን ያመጣል፣ እናም አንዳንዶቹ ከሰላም ይልቅ በጦርነት ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ያደርጋል።
አሜሪካ ያላትን የሞራል የበላይነቷን እያጣች ነው ሲሉ ኢሮ ጠቁመዋል።
“ዓለም አቀፋዊ ተዋናዮች ሩሲያ በዩክሬን ለምትፈጽመው ድርጊት ያላት መመዘኛ እና በጋዛ ውስጥ የእስራኤልን ድርጊት የምትመለከትበት መነጽር እንደሚለያይ አስተውለዋል። በሱዳን ያለው ጦርነት አስከፊ ግፍ እየተፈጸመበት እንደሆነ ቢታይም እንደ ሁለተኛ ጉዳይ ተቆጥሯል።”
ካማላ ሃሪስ የዋይት ሐውስን ድል ቢጨብጡ “አሁን ያለው አስተዳደር ቀጣይነትን ይረጋገጣል” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ትራምፕ ካሸነፉ ግን “ለእስራኤል በጋዛ እና በሌሎች ቦታዎች የበለጠ ነፃ መጋለቢያ ፈቃድ ሊሰጡ ይችላሉ። በኪየቭ እስትንፋስ ላይ ደግሞ ከሞስኮ ጋር ስምምነትን ሊደርሱ ይችላሉ” ሲሉ የሚፈጠረውን ያስረዳሉ።
በመካከለኛው ምሥራቅ የዴሞክራቲክ ዕጩዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ እስራኤል “ራሷን የመከላከል መብት” አላት የሚውን አቋማቸውን ደጋግመው አስተጋብተዋል። ነገር ግን “ንጹሃን ፍልስጤማውያንን መግደል መቆም አለበት” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ትራምፕም እንዲሁ “ወደ ሰላም የምንመለስበት እና ሰዎችን መግደል የምናቆምበት ጊዜ ነው” ብለዋል። ነገር ግን ለእስራኤሉ መሪ ቤንጃሚን ኔታንያሁ “ማድረግ ያለብህን አድርግ” ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል።
የሪፐብሊካኑ ተፎካካሪ ሰላም ፈጣሪ በመሆን ራሳቸውን ያኩራራሉ። ከሳዑዲ አረቢያው አል አረቢያ ቴሌቪዥን ጋር እሁድ ምሽት ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ “በመካከለኛው ምሥራቅ በቅርቡ ሠላም አሰፍናለሁ” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
የ2020 የአብርሃም ስምምነትን ለማስፋትም ቃል ገብተዋል።
እነዚህ የሁለትዮሽ ስምምነቶች በእስራኤል እና በጥቂት የአረብ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ያስታረቁ ቢሆንም ፍልስጤማውያንን ወደ ጎን እንዳደረጉ እና በመጨረሻም ታይቶ ለማይታወቅ የአሁኑ ቀውስ አስተዋፅዖ ማዋጣታቸው በሰፊው ይታመናል።
ትራምፕ እንደ ሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ላሉ ኃያል መሪዎች ያላቸውን አድናቆት በጭራሽ አይደብቁም። በዩክሬን ያለውን ጦርነት እንዲሁም የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ ማቆም እንደሚፈልጉ ግልጽ አድርገዋል።
“እወጣለሁ፤ መውጣት አለብን” ሲሉ በቅርቡ ባካሄዱት የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ተናግረዋል።
በተቃራኒው ካማላ ሃሪስ “ከዩክሬን ጎን በመቆሜ ኩራት ይሰማኛል። ከዩክሬን ጋር መቆሜን እቀጥላለሁ። እናም በዚህ ጦርነት ዩክሬን ድል እንድትቀዳጅ እሠራለሁ” ብለዋል።
ነገር ግን ኤሮ ማንም ይመረጥ ማንም በዓለም ላይ ነገሮች ሊባባሱ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ።
ከቻይና ጋር የሚኖር ግንኙነት
በሁሉም ከውጭ በሚገቡ የቻይና ምርቶች ላይ የዋጋ ተመንን በተመለከተ የትራምፕ አስተዳደር የ60 በመቶ ታሪፍ መጣሉን በማስመልከት ቻይናዊው ምሁር ራና ሚተር “ለአስርት ዓመታት ለዓለም ምጣኔ ሀብት ትልቁ ድንጋጤ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ትራምፕ በቻይና እና በሌሎች በርካታ የንግድ አጋሮች ላይ ከባድ ታክሶችን መጫን “ቅዳሜ አሜሪካ” ለሚለው መፈክራቸው ከማያቋርጥ ማስፈራሪያዎች አንዱ ነው።
ነገር ግን ትራምፕ ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ያላቸውን ጠንካራ ግላዊ ግንኝነትም ያንቆለጳጵሳሉ።
ለዎል ስትሪት ጆርናል የኢዲተሮች ቦርድ ቤይጂንግ ታይዋንን ብትከብ ወታደራዊ ኃይል መጠቀም እንደሌለባቸው ተናግረው ምክንያታቸውንም ሲያስቀምጡ፣ የቻይናው መሪ “እብድ መሆኔን ስለሚያውቁ ያከብሩኛል” ማለታቸው ተሰምቷል።
ቻይናን በሚመለከት የሪፐብሊካን እና ዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዎች ንቁዎች ናቸው። ሁለቱም ቤጂንግ የአሜሪካንን ኃያልነት ለመገዳደር እና ቀዳሚ አገር ሆና ለመውጣት የምትጥር አድርገው ያይዋታል።
ነገር ግን በሀርቫርድ ኬኔዲ ትምህርት ቤት በአሜሪካ እና እስያ ግንኙነት ላይ ጥናት የሚያደርጉት ብሪታኒያዊው የታሪክ ምሁር ሚተር አንዳንድ ልዩነቶችን ተመልክተዋል።
ካማላ ሃሪስ ብታሸንፍ “ግንኙነቱ አሁን ባለበት መስመር ሊዳብር ይችላል” ይላሉ። ትራምፕ ካሸነፉ ግን የበለጠ “ወላዋይ ሁኔታ” ነው የሚኖረው።
ለምሳሌ ይላሉ ሚተር፣ ከአሜሪካ በብዙ ማይሎች ርቃ የምትገኘው ታይዋንን ለመከላከል መቻላቸውን በተመለከተ የትራምፕ አቋም አሻሚ መሆኑን ይጠቁማሉ።
የቻይና ባለሥልጣናት ሃሪስም ሆኑ ትራምፕ አገራቸውን በተመለከተ ጠንካራ ይሆናሉ ብለው ያምናሉ።
ሚተር “ጥቂቶች ሃሪስን የተሻሉ አድርገው ይመለከታሉ። በርግጥ ይህ የማይመስል ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ደግሞ የትራምፕ አይገመቴነት ቻይናን ለመደራደር ይጠቅማታል ብለው ይጠብቃሉ” ብለዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ መሪነት
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ የነበሩት ማርቲን ግሪፊትዝ “ዩናይትድ ስቴትስ በወታደራዊ እና በምጣኔ ሀብት ኃይሏ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰብዓዊ ድጋፍም በበላይነት ለመምራት ባላት ወደር የለሽ ተጽዕኖ ምክንያት የምርጫው ውጤት ትልቅ ጠቀሜታ አለው” ይላሉ።
ካማላ ሃሪስ ካሸነፉ የበለጠ ተስፋ ይታያቸዋል።
“የሃሪስ ፕሬዝዳንትነት ተስፋ ያዘለ ነው” በአንፃሩ “በመገለል እና ወገንተኝነት የሚታወቀው የትራምፕ ወደ ፕሬዝዳንትነት መመለስ ትንሽ አበርክቶ ዓለም አቀፋዊ አለመረጋጋትን እና ተስፋ መቁረጥን በብዛት የሚጨምር ይሆናል።”
አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትልቅ ለጋሽ አገር ነች። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 18.1 ቢሊዮን ዶላር በመለገስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጓ ተመዝግቧል።
ነገር ግን ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የዓለም ጤና ድርጅትን ድጋፍ ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች የሚደረገውን የገንዘብ ድጎማ አቁመዋል።
በወቅቱ ሌሎች ለጋሾች ክፍተቶቹን ለመሙላት ተንደፋደፉ፤ ትራምፕ ፈልገው የነበረውም ይህ እንዲፈጠር ነበር።
ነገር ግን ሚስተር ግሪፊትዝ በሰብዓዊ እርዳታ ማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ጥልቅ ተስፋ መቁረጥን እንዲሁም የባይደን አስተዳደር በመካከለኛው ምሥራቅ እያሽቆለቆለ ባለው ሁኔታ ላይ ያለውን “ማመንታት” ተችተዋል።
የረድኤት ተቋማት ኃላፊዎች ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ሰላማዊ ዜጎች ላይ በድንገት ያደረሰውን ግድያ ደጋግመው አውግዘዋል።
ነገር ግን በጋዛ እና በሊባኖስ ውስጥ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ከባድ ስቃይ ለማስቆም አሜሪካ የበለጠ እንድታደርግ ደጋግመው ጠይቀዋል።
ባይደን እና ከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው ወደ ጋዛ ተጨማሪ እርዳታ እንዲደረግ ደጋግመው ጠይቀዋል እና አንዳንድ ጊዜም ለውጥ አምጥተዋል። ተቺዎች ግን እርዳታው እና ግፊቱ በቂ አልነበረም ይላሉ።
በቅርቡ ከአሜሪካ የተሰማው ወደ ጋዛ እርዳታ የማይገባ ከሆነ አንዳንድ ወሳኝ ወታደራዊ እርዳታዎች ሊቋረጡ እንደሚችሉ የሚገልጸው ማስጠንቀቂያ የአሜሪካ ምርጫ እስከሚያበቃ ድረስ ሊገፋ እንደሚችል ተገምቷል።
“እውነተኛ አመራር የሚታወቀው ሰብአዊ ቀውሶችን በማይናወጥ የሞራል ልዕልና ለመቅረፍ ሲነሳ፣ የሰውን ሕይወት መጠበቅ የአሜሪካ ዲፕሎማሲ እና በዓለም መድረክ ላይ ለሚደረገው ተግባር መሠረት ሲሆን ነው” ሲሉ ሚስተር ግሪፊትዝ ያብራራሉ።
አሁንም ቢሆን ግን አሜሪካ የማትናቅ ኃያል አገር መሆኗን ያምናሉ።
“ዓለም አቀፋዊ ግጭት እና እርግጠኛነት ባልሰፈነበት በዚህ ጊዜ፣ ዓለም ዩናይትድ ስቴትስ ኃላፊነት የሚሰማው፣ በመርኅ ላይ የተመሠረተ አመራር እንድታሳይ ይጠብቃል. . . የበለጠ እንሻለን። የበለጠም ይገባናል። እናም የበለጠ ተስፋ ለማድረግ እንታትራለን።”