የእስራኤል ጥቃት ድምቀቷን ያደበዘዘባት ቤይሩት

ጋዛን ወደ ፍርስራሽነት የቀየረችው እስራኤል በቤይሩትም የማያባራ ጥቃት ከጀመረች ሳምንታት ተቆጠሩ።

በደማቅነቷ የምትወሳው የሊባኖሷ መዲና ቤይሩት መጠጥ ቤቶቿ እንዲሁም መጻህፍት ቤቶቿ በአሁኑ ወቅት ወና ሆነዋል።

የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ድምጽ ነዋሪዎችን ማሸበራቸው የየዕለት ተግባራቸው አድርገውታል።

“ለሚያነሱን ፎቶ ጥሩ ሆነን እንድንታያቸው ፈገግ እንበል” በቤይሩት ሆቴል ዋና አስተናጋጅ የሆነው ማርዋን የሚያንዣብቡትን ድሮኖች ድምጽን እየሰማ ይቀልዳል።

በሐዘን ጊዜ መቀለድ ሳያዋጣ አይቀርም ያለ የሚመስለው ማርዋን የእስራኤል ቃኚ ድሮኖችን ለማየት ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ወደ ሰማይ አንጋጦ ነው ይህንን የሚለው።

ከሆቴሉ የሚጫወተው ሙዚቃም ሆነ የወፎች ድምጽ የድሮኖቹን ጥዝዝዝ የሚል ጆሮ የሚሰረስር ድምጽ መሸፈን አልቻሉም።

የማርዋን ሆቴል የሚገኝበት ይህ አክራፊየህ የተሰኘው ስፍራ ከጠንካራ የሄዝቦላህ ይዞታዎች መካከል አይደለም።

ከእስራኤል ጋር በነበሩ የቀደሙ ጦርነቶች ባለጸጎች የሆኑ ክርስቲያኖች ሰፈር የሆነው አክራፊየህ ዒላማ አልተደረገም ነበር።

የቢቢሲ ጋዜጠኛም መኖሪያው በዚሁ ሰፈር አካባቢ ነው።

ከቀናት በኋላ ሁለት ድሮኖች በአክራፊየህ ዙሪያ ማንዣበብ ጀመሩ።

የሰፈሩ ህጻናት እና ነዋሪዎች ጩኸታቸውን አቀለጡት። የሰፈሩ ሰው ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ወደ በመስኮቶቻቸው እንዲሁም ወደ በረንዳቸው ሮጡ። በሰኮንዶች ውስጥ ኃይለኛ ፍንዳታ ተሰማ። በጎዳናዎች ላይ ያሉ ዛፎች በፍንዳታው ተንቀጠቀጡ።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ባለበት ህንጻ ያሉ ነዋሪዎች በሄዝቦላህ ቁጥጥር ስር ወዳለችው የቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ ዳሂህ አካባቢ እየተመለከቱ ነበር። ነገር ግን ፍንዳታው የደረሰው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ካለበት ህንጻ በመኪና የአምስት ደቂቃ ርቀት ላይ ነበር።

የአገር ውስጥ ሚዲያዎች በዚህ ጥቃት ዒላማ የተደረገው የሄዝቦላህ የደኅንነት ከፍተኛ ባለሥልጣን እና በቅርቡ የተገደለው መሪ ሐሳን ናስራላህ አማች ዋፊቅ ሳፋ እንደሆነ ዘግበዋል።

በዚህ ጥቃት ባለሥልጣኑ ምንም አልሆነም። በዚህ የእስራኤል ጥቃት ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረው ህንጻ ከሌሎች ከተሞች ወደ ቤይሩት ሸሽተው በመጡ ነዋሪዎች የተሞላ ነበር።

ከጥቃቱ በፊት እስራኤል ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ያልሰጠች ሲሆን፣ ቢያንስ 22 ሰዎች ተገድለዋል። ይህም እስራኤል እስካሁን ከፈጸመቻቸው አስከፊ ጥቃቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ተነግሯል።

“አምላኬ! በዚያ መንገድ እያለፍን ቢሆንስ?” አንድ ጎረቤት ይጮሃል። “ያ መንገድ እኮ በየቀኑ ወደ ሥራ የማልፍበት ነው” ሲልም ይሰማል።

“በቀጣዩ የምንኖርባቸው ህንጻዎች ላለመታቸው ምን ዋስትና አለን?” ጎረቤትየው ይጠይቃል።

የእስራኤል የዚህ ዙር የአየር ጥቃት የተጀመረው መስከረም 7 እና መስከረም 8/2017 ዓ.ም። በዚህም ሄዝቦላህ ለመረጃ ልውውጥ የሚጠቀምባቸውን የሬዲዮ መገናኛዎች (ፔጀሮች) በመላው ሊባኖስ በተመሳሳይ ጊዜ አፍንድታ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል።

በዚህም ጥቃት የሄዝቦላህ ተዋጊ እና 32 ነዋሪዎች ሲገደሉ፣ 5 ሺህ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በርካቶች ዓይናቸውን፣ እጃቸውን ወይም ሁለቱን አጥተው አካል ጉዳተኞች ሆነዋል።

የእስራኤል አየር ጥቃቶች በደቡባዊ ሊባኖስ እንዲሁም በቤይሩት በከባዱ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዦች ተገድለዋል።

መስከረም 20 ደግሞ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ላይ ወረራ ፈጸመች። እስራኤል ባለፉት ሳምንታት በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 1600 ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

የቢቢሲ ጋዜጠኛም በርካቶቹን የአየር ጥቃቶች ተመልክቷል።የቤይሩት ከተማ የቤይሩት ከተማ

ባለፉት ሦስት ሳምንታት የተፈጸሙት ክስተቶችን በቅጡ ማሰላሰል እንዳልቻለ ማርዋን ለቢቢሲ ተናግሯል። የአሁኑ ዙር የእስራኤል እና የሄዝቦላህ ፍጥጫ ከጀመረበት ባለፉት 12 ወራት ጀምሮ ቢቢሲ ማርዋንን ሲያናግረው ነበር። የሁለቱን ውጥረት ለዓመታት ቢታዘብም ወደ ሙሉ ጦርነት ያመራል የሚል እሳቤ አልነበረውም።

“ማመን አልፈለግኩም ነበር። ነገር ግን አሁን ሙሉ ጦርነት ውስጥ ገብተናል” ይላል።

የባለፉት ሳምንታት ጥቃቶች የቤይሩትን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።

የቤይሩት ጎዳናዎች በመኪኖች ተጨናንቀዋል። አንዳንዶቹ መኪኖቻቸውን በመሃል አደባባይ ላይ አቁመዋል። በደቡባዊ ሊባኖስ ካለው የበረታ ጥቃት የሸሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው የተሻሉ ናቸው ባሏቸው የቤይሩት ሰፈሮች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተጠለዋል።

በርካቶች ደግሞ ኑሯቸውን በጎዳናዎች ላይ አድርገዋል። ወደ ቤይሩት አየር ማረፊያ እና ደቡባዊ እስራኤል በሚወስዱ ጎዳናዎች ዳር ዳር የሐሳን ናስራላህ ፎቶዎች ያሉባቸው ቢልቦርዶች ተሰቅለዋል።

ይህ ሁኔታ ለሄዝቦላህ ደጋፊዎች እንዲሁም ለተቃዋሚዎች “ህልም የሆነ ክስተት ነው” የሆነባቸው።

ቀደም ሲል “ሊባኖስ ጦርነትን አትፈልግም” የሚሉ ፖስተሮች ተሰቅለውባቸው የነበሩ አካባቢዎች “ለሊባኖስ እንጸልይ” በሚሉ ተተክተዋል።

ተቃውሞዎችን እና ገናን ጨምሮ በዓላት የሚስተናገድበት የከተማዋ ምልክት፣ የሰማዕታት አደባባይ (ማርቲር ስኩውየር) ወደ ድንኳን ከተማነት ተቀይሯል።

በአደባባዩ ላይ በቆመው ከብረት በተሠራው የገና ዛፍ ስር ቤተሰቦች ተጨናንቀው ተጠልለዋል። ከአምስት ዓመታት በፊት የነበረውን የወጣቶች ተቃውሞ ተከትሎ ቁርጠኝነትን እንዲያሳይ በቆመው የተጨበጠ እጅ ሃውልት አካባቢ ድንኳኖች ተተክለዋል፣ ፍራሾች ተዘርግተዋል፣ ብርድ ልብሶች ተነጥፈዋል። ጊዜያዊ መጠለያዎች ከአደባባዩ ጀምሮ ረጅም ርቀት በሚወስደው ባሕር ድረስ ተተክለዋል።

በእነዚህ አካበቢዎች ያሉት አብዛኞቹ እንደገና ለሌላ መፈናቀል የተደረጉ ሶሪያውያን ቤተሰቦች ናቸው። መጠለያዎቹ ቅድሚያ ለሊባኖስ ዜጎች በመስጠታቸው ሶሪያውያኑ ጎዳናዎች ላይ ለመውጣት ተገደዋል። በርካታ ሊባኖሳውያንም ቢሆኑ ቤት አልባ ሆነዋል።

ተፈናቃዮቹ መጠለያዎች ለማግኘት ከሚራኮቱበት በአንድ ኪሎሜትር ርቀት የ26 ዓመቷ ናዲን ለጥቂት ሰዓታትም ቢሆን ሁሉንም ነገር ለመርሳት እየሞከረች ነው።

በቤይሩት ገምያዝ በተሰኘው ሰፈር ታዋቂ በሆነው አሊያህ ቡክስ ከተሰኘው መጽሃፍት መሸጫ እና መጠጥ ቤት ካሉት ጥቂት ደንበኞች አንዷ ናት።የቤይሩት ከተማ

“ምንም ደኅንነት አይሰማኝም። ሌሊቱን ሙሉ ፍንዳታዎችን እንሰማለን” ትላለች ናዲን በፍራቻ።

ለረጅም ጊዜ ቤይሩታውያን ውጥረቱ ሄዝቦላህ በሚያስተዳደራቸው በደቡባዊ ሊባኖስ የድንበር ከተሞች ተወስኖ እንደሚቆይ ያምኑ ነበር።

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሄዝቦላህን የመሩት እና እስራኤል በአየር ጥቃቷ የገደለቻቸው ሐሳን ናስራላህ አገራቸውን ወደ ጦርነት ለማስገባት ፍላጎት ያልነበራቸው ሲሆን፣ ከእስራኤል ጋር የነበረው ፍጥጫ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያንን ለመደገፍ በሚል ብቻ ነበር።

አሁን ሁሉ ነገር ተቀይሯል።

የከተማዋ ንግድ ተቀዛቅዟል።አሊያህ ቡክስ ከሳምንታት በፊት የተለያዩ ባንዶች ሙዚቃ የሚጫወቱበት፣ የወይን ጠጅ የሚቀመስበት ደማቅ ስፍራ ነበር። በዳሂያ ከደረሰው ጥቃት በፊት የሄዝቦላህ ምክትል አዛዥ ፉአድ ሹክር ከተገደለበት የሐምሌ 23 ጥቃት በፊት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ለሪፖርት ፊልም እየቀረጹ ነበር። የእስራኤል ጄቶች ጥቃቶቹን ሲያደርሱ ፍንዳታዎች እየተሰሙ ነበር።

ነገር ግን የጃዝ ባንድ ሙሉ ምሽቱን ተጫወተ። “እኛም እየደነስን፣ ባሩም ሙሉ ነበር። ነገር ግን በዳሂያ ከደረሰው ጥቃት በኋላ አሊያህ ቡክስ ወና ሆኗል። ሙዚቃም አይሰማም፤ ዳንስም ቀርቷል። “ይላል የቢቢሲው ጋዜጠኛ።

“አሳዛኝ እና ተስፋ አስቆራጭ ነው። የሚጫንህን ስሜት ለማባረር እና ለመዝናናት ወደዚህ ስፍራ ትመጣለህ። ነገር ግን በመጨረሻም የምታወራው ስለ ጦርነቱ ነው። ቀጣዩ ምን ይሆን? የሚለው ነው የሁሉም ጥያቄ” የባሩ ሥራ አስኪያጅ ቻርሊ ሃበር።የቤይሩት ከተማ

ከናስራላህ ግድያ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ሥራ አቁመው እንደገና ቢከፍቱም እንደ ከዚህ ቀደሙ እስከ ሌሊት ሳይሆን የሚሠሩት እስከ ምሽት 2 ሰዓት ብቻ ነው።

በዚህ አካባቢ ምሽት ላይ የሚከፍቱ ሬስቶራንቶችን ሆነ መጠጥ ቤቶችን ማግኘት ፈታኝ ነው።

በጣም ተወዳጁ እና ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በፊት የማይዘጋው ሎሪስ የተሰኘው ሬስቶራንት ሰው እንደሌለው አንደኛው ባለቤቱ ጆ አውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

በዚህ ሬስቶራንት ቀድመው ቦታ ካላስያዙ ጠረጴዛ ማግኘት የማይቻል ቢሆንም፣ አሁን ሁለት ወይም ሦስት ጠረጴዛ የተቀመጡ ሰዎች ካገኘ አስገራሚ ነው።

የሬስቶራንት እና ባር ባለቤቶች ማኅበር የቦርድ አባል የሆኑት ማያ ቤካዚ በቤይሩት 85 በመቶ የሚሆኑ ሬስቶራንቶች እና መጠጥ ቤቶች መዘጋታቸውን ወይም የሚዘጉበትን ሰዓት እንደገደቡት ይናገራሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)