የአውሮፓ ኅብረት ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ከአህጉሩ ሊያባርር ነው

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ቮን ድር ሌየን ተጨማሪ ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ከአህጉሪቱ ለማባረር ያላቸውን ዕቅድ ይፋ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።

ኅብረቱ ሐሙስ እና አርብ በቤልጂየም ዋና ከተማ ብራስልስ ስደተኞች ላይ ያተኮረ ስብሰባ ያደርጋል።

ፕሬዝደንቷ ከስብሰባው በፊት ለአባል አገራት በላኩት ደብዳቤ ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ለማባረር ያዋጣል ያሉትን ዕቅድ አስቀምጠዋል።

በቅርቡ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊ ሆነው ድጋሚ የተመረጡት ቮን ዴር ሌየን ወደ አውሮፓ የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ጫና ያደረባቸው ይመስላል።

ኃላፊዋ በደብዳቤያቸው በአሁኑ ወቅት ወደመጡበት አገር እየተመለሱ ያሉ ሕገ-ወጥ ስደተኞች 20 በመቶ ብቻ ናቸው ብለው አውሮፓን ለቀው እንዲወጡ የተጠየቁ ስደተኞች የተባሉት እየፈፀሙ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

እሳቸው እንደሚሉት አህጉሪቱን ለቀው እንዲወጣ የተነገራቸው ስደተኞች አገር ይቀይራሉ አሊያም ካሉበት ቦታ አይንቀሳቀሱም ሲሉ ገልፀዋል።

ስደተኞች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እየወሰደች ያለችው ጣሊያን አዲስ ባወጣቸው ዕቅድ መሠረት በሜዲቴራኒያን በኩል የመጡ ስደተኞች ወደ አልቤኒያ ተልከው ከአውሮፓ የሚወጡበት ሁኔታ ይመቻችላቸዋል።

በዚህ ሳምንት ከባንግላዴሽ እና ከግብፅ የመጡ 16 ስደተኞች ከላምፔዱሳ ወደ አልቤኒያ እንዲወሰዱ ተደርገዋል። ስደተኞቹ ወደ አልቤኒያ ከሄዱ በኋላ የጥገኝነት ጥያቄያቸው እንደ አዲስ ይታያል።

በአልቤኒያ ለዚህ ሒደት የሚሆኑ ሁለት ማዕከሎች በ650 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ተገንበተዋል። ማዕከሎቹ በጣሊያን ወጪ የተገነቡ ሲሆኑ፣ ማዕከላቱ የሚመሩትም በጣሊያን ሕግ መሠረት ነው።

በዚም አሠራር ወደ ጣሊያን የመጡ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸው በአልቤኒያ ይታያል ማለት ነው። ነፍሰጡሮች፣ ሕፃናት እና ተጋላጭ የሚባሉ ሰዎች ከዚህ ዕቅድ ውጪ ናቸው።

የቀኝ ዘመሟ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ ተቃዋሚዎች እና በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጣሊያን ከአልቤኒያ ጋር የገባችውን ስምምነት ተቃውመውታል።

ድንበር የለሽ የዶክተሮች ማኅበር (ዶክተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ) “የበለጠ የሰዎች ሰብዓዊ መብት እንዲገፈፍ ምክንያት ይሆናል” ሲል አዲሱን አካሄድ ተቃውሞታል።

በርካታ የአውሮፓ አገራት ጣሊያን ከአልቤኒያ ጋር የገባችውን ስምምነት በቅርበት እየተከታተሉት ይገኛሉ። ስደተኞች ወደ አውሮፓ መጉረፋቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ወደ ቀኝ ዘመም አገዛዞች እያመዘኑ እንደሆነ ይነገራል።

በቅርብ ሳምንታት ብቻ ጀመርን በየብስ በኩል የሚመጡ ሰዎች ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር ያጠበቀች ሲሆን፣ የፈረንሳይ መንግሥት ደግሞ የስደተኞች ሕጉን ጠበቅ እንደሚያደርገው አስታውቋል። ፖላንድ በበኩሏ በድንበር አቋርጠው ለሚመጡ ስደተኞች የሚሰጠው የጥገኝነት ጥያቄ ለጊዜው መቆሙን ገልፃለች።

በፈረንሳይ እና በጀርመን ሕጎች መጥበቅ የጀመሩት ስደተኞች ግድያዎችን ከተፈፀሙ በኋላ ነው። በቅርቡ የጥገኝነት ጥያቄው ውድቅ የሆነ አንድ ሶሪያዊ ሦስት ሰዎች በስለት ወግቶ ሲገድል፣ አንድ ሞሮኳዊ ደግሞ ፓሪስ ውስጥ አንዲት ታዳጊ ተማሪን ገድሏታል።

ሁለቱም ግለሰቦች የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ ሆኖ ከአገር እንዲወጡ ታዘው ነበር።

ባለፈው ወር ኦስትሪያ እና ኔዘርላንድስ ያቀረቡትን ስደተኞችን የማባረር ዕቅድ 15 የአውሮፓ ኅብረት አገራት ደግፈውታል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)