የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የህወሓት ኃይሎች ለሱዳን ጦር ወግነው እየተሳተፉ ነው የሚለውን ክስ አወገዘ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የህወሓት ኃይሎች ለሱዳን ጦር ወግነው እየተዋጉ ነው በሚል ያቀረበውን ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ሲል አወገዘ።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትናንት ሚያዝያ 28/2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ይህንን ክስ ያሰማው የአስር ሺዎችን ህይወት የቀጠፈውን የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት አለም አቀፋዊ ድጋፍ ለማግኘት እና ጦርነቱንም አለም አቀፋዊ ለማድረግ ነው ብሏል።

በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት አንደኛው ተፋላሚ የሆነው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የህወሓት ኃይሎች ለተቀናቃኙ የሱዳን ጦር ወግነው እየተዋጉ ስለመሆናቸው መረጃዎች አሉኝ ሲል ከሰሞኑ ገልጿል።

በጄነራ ልመሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሱዳን ጦር የውጭ ቅጥረኞችን በመቅጠር እያሳተፈ ነው ሲል ከሶ ከህወሓት ኃይሎች በተጨማሪ አጋር ታጣቂዎቹ አሉበት ብሏል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በበኩሉ ህወሓት የፖለቲካ ፓርቲ በመሆኑ ታጣቂ ክንፍ፣ የተደራጀ ሚሊሻ የለውም ብሏል።

ኃይሉ ከህወሓት ኃይሎች በተጨማሪ በስም ያልጠቀሳቸው ከአሸባሪ ኔትወርክ ጋር ግንኙነት ያላቸው የጂሃዲስት ኃይሎች እና ቅጥረኛ ቡድኖች እንዲሁም በስም ያልጠቀሳቸው አገራት ቅጥረኛ ተዋጊዎች ለጦሩ ወግነው በተለያዩ መንገዶች እየደገፉ ነው ብሏል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህንን ውድቅ አድርጎ የትግራይ እና የሱዳን ህዝብ ትስስር ታሪካዊ ነው ያለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ በተለይም የትግራይ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ከምዕራብ ትግራይ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ የትግራይ ተወላጆች ሱዳን መጠለያ እንደሆነቻቸው አስታውሷል።

“ የሱዳን ህዝብ እና መንግሥት አሳሳቢ የሆኑ ውስጣዊ ተግዳሮቶች ላይ ቢሆኑም በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ የትግራይ ተፈናቃዮች እርዳታ እና ጥበቃ በማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል” ብሏል።

በእነዚህ ምክንያቶች “ትግራይ፣ የትግራይ ተወላጆች እንደ ሁለተኛ ቤታቸው የሚቆጥሯትን ሱዳን በበለጠ የመጉዳት እና በእርስ በርስ ጦርነት የምትገባበት ምክንያት የለም” ብሏል።

በተጨማሪም በውስጥ ግጭት የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚያስከትለውን አስከፊ መዘዝ ከትግራይ ህዝብ በላይ የሚረዳ እንደሌለ አስታውሶ “በትግራይ ጦርነት በውጭ ኃይሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የከፋ ስቃይ የደረሰበት የትግራይ ህዝብ በሱዳን ግጭት የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚያስከትለውን እዳ የበለጠ ያውቃል” ብሏል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በበኩሉ በርካታ የውጭ ቅጥረኛ ተዋጊዎች ከጦርነቱ ጅማሬ ማግስት ለጦሩ ደግፈው በአየር ኃይሉ ዘመቻ፣ በከባድ መሳሪያዎች፣ በድሮን ስምሪት እና በመረጃ ጦርነት እየተሳፉ እንደሆነ ገልጿል።

ለዚህም የላቀ ነው ያለው የክትትል ስርዓቱን በመጠቀም በጦር ግንባሩ ላይ የተገደሉ ቅጥረኛ ወታደሮች መኖራቸው መረጃ እንዳገኘና በህዳር እና ታህሳስ ወራት በሱዳን አየር ማረፊያ በኩል አስከሬናቸው መውጣቱን ደርሸበታለሁ ብሏል።

በሱዳን ጦር መሪ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከአንድ አመት በላይ አስቆጥሯል።

ሁለቱ ጄነራሎች ለሶስት አስርት ዓመታት ሱዳንን የመሯትን ኦማር አልበሽርን በአውሮፓውያኑ 2019 ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ አገሪቷንም ሲመሯት ቆይተዋል።

በቀጣናዊ እና አለም አቀፍ አጋሮች አማካኝነት የተደረሱ በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶችም በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ተጥሰዋል።

በጦርነቱ በአስር ሺዎች ሰዎች ሲገደሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ተፈናቅለዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን ከሚያቀጣጥሉ መግለጫዎች ተቆጥበው ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ለፖለቲካዊ ችግሩ እልባት በማበጀት አሰዛኙን ክስተት ሊቋጩት ይገባል ብሏል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )