የቲክቶክ መሥራች የቻይና ቁጥር አንድ ባለሀብት ሆነ

በዓለም ዙሪያ ታዋቂነቱ እየጨመረ የመጣው ቲክቶክ ከመሥራቾቹ መካከል አንዱ የሆነው ዣንግ ይሚንግ በቻይና ቁጥር አንድ ሀብታም ለመሆን በቃ።

ሁሩን የተባለው የምርምር ተቋም ባወጣው የሀብታሞች ዝርዝር ውስጥ ቁጥር አንድ ለመሆን የቻለው ይሚንግ ያለው ሀብት 49.3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከነበረው ገንዘብ በ43 በመቶ ጨምሯል።

የ42 ዓመቱ ዣንግ ይሚንግ ባይትዳንስ በተባለው ድርጅት ሥር የሚተዳደረውን ቲክቶክ አስከ 2021 ድረስ ሲመራ ቆይቶ ከሦስት ዓመታት በፊት ቦታውን ቢለቅም በድርጅቱ ላይ የ20 በመቶ ድርሻ አለው።

ቲክቶክ ምንም እንኳን ከቻይና መንግሥት ጋር ባለው ግንኙነት የተነሳ በአንዳንድ አገራት በጥርጣሬ ቢታይም፣ በዓለም ዙሪያ በጣም ተወዳጅ ከሆኑት የማኅበራዊ ሚዲያ መተግባሪያዎች መካከል አንዱ ነው።

የቲክቶክ ባለቤት የሆነው ኩባንያ ከቻይና መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በተደጋጋሚ የገለጸ ቢሆንም፣ የአሜሪካ መንግሥት ግን ባይትዳንስ ቲክቶክን የማይሸጠው ከሆነ በሚመጣው ጥር ከአገልግሎት እንደሚያግደው አስጠንቅቋል።

ምንም እንኳን ቲክቶክ ከአሜሪካ በኩል ከባድ ጫና እየደረሰበት ያለ ቢሆንም በመላው ዓለም የሚያገኘው ትርፍ ባለፈው ዓመት በ60 በመቶ ከፍ ብሏል፤ ይህም የዣንግ ይሚንግ ግል ሀብት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

“በ26 ዓመታት ውስጥ ዣንግ ይሚንግ በሀብት መጠን በቻይና ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንደኛ ሲሆን 18ኛው ሰው ነው” ሲል መረጃውን ያጠናቀረው ሁሩን ተቋም ኃላፊ ሁጌዌርፍ ተናግሯል።

“በንጽጽር እስካሁን በአሜሪካ አራት ብቻ በሀብት አንደኛ የሆኑ ሰዎች ተመዝግበዋል። እነሱም ቢል ጌትስ፣ ዋረን ባፌት፣ ጄፍ ቤዞስ እና ኤላን መስክ ናቸው። ይህም በቻይና ምጣኔ ሀብት ውስጥ ያለውን ተለዋዋጭ ሁኔታን የሚያመለክት ነው” ተብሏል።

በባለሀብቶቹ ዝርዝር ውስጥ ዣንግ በቻይና ግዙፍ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቸኛው ግለሰብ አይደለም።

ቴንሴንት የተባለው የቴክኖሎጂ ተቋማት ስብስብ አለቃ የሆነው ፖኒ ማ ባካበተው 44.4 ቢሊዮን ዶላር በተገመተው ሀብቱ በሰንጠረዡ ላይ ሦስተኛ ሆኗል።

ባለፈው ዓመት የቻይና ምጣኔ ሀብት እና የአክስዮን ገበያ አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሟቸው ስለነበረ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት የባለሀብቶች ቁጥር እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ሁጌዌርፍ ገልጸዋል።

“በ2021 ከነበረው ከፍተኛ ቁጥር በ25 በመቶ ያሽለቆለ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በሰንጠረዡ ውስጥ የተመዘገቡት የቻይና ባለሀብቶች መጠን ከቀደመው ዓመት በ12 በመቶ በመቀነስ 1100 በታች ሆኗል።”

ኃላፊው ጨምረውም በተሰበሰበው የባለሀብቶች መረጃ መሠረት ባለፈው ዓመት ለዘመናዊ የሞባይል ስልኮች አምራቾች ከገቢ አንጻር መልካም የነበረ ሲሆን፣ ከብክለት ነጻ የሆነ ኃይል ለሚያመርቱት ደግሞ ማሽቆልቆል የታየበት ነበር።

“በፀሐይ ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ሳህኖች፣ የኤሌክትሪክ ባትሪዎች እና ለኤሌክትሪክ መኪና አምራቾች ባለፈው [የአውሮፓውያን] ዓመት ፉክክሩ ከባድ የነበረበት እና የታሪፍ ጭማሪ ስጋት የነበረበት በመሆኑ ፈታኝ ነበር” ተብሏል።

በ2021 ከነበረው ከፍተኛ ገቢ አንጻር በፀሐይ ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ሳህኖችን የሚያመርቱ ኩባንያዎች ሀብት እስከ 80 በመቶ በሚደርስ መጠን አሽቆልቁሏል፣ በተመሳሳይ የኤሌክትሪክ መኪና እና ባትሪ አምራቾች ገቢም እስከ ግማሽ በሚደርስ መጠን ቀንሷል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)