ከ90 በላይ ፍልስጤማውያንን የገደለውን የእስራኤል ጥቃት ‘አሰቃቂ’ ስትል አሜሪካ ገለጸች

በሰሜን ጋዛ ቤይት ላሂያ ከተማ ላይ እስራኤል በፈጸመችው አየር ጥቃት ቢያንስ 93 ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ሲያስታውቅ፤ አሜሪካ በበኩሏ ‘አሰቃቂ’ ስትል ፈርጃዋለች።

የነፍስ አድን ሠራተኞች ባለ 5 ፎቅ የመኖሪያ ህንጻ መመታቱን የገለጹ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ቪዲዮዎች ደግሞ በብርድ ልብስ የተሸፈኑ በርካታ አስከሬኖችን አሳይተዋል።

የእስራኤል ጦር “(ማክሰኞ) በቤይት ላሂያ አካባቢ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሚገልጹ ዘገባዎችን አውቋል” ብሏል። የአደጋው ዝርዝር ሁኔታ እየተጣራ መሆኑንም አክሏል።

የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ወረራ ባካሄደባቸው በሰሜን ጋዛ በተለይም በጃባሊያ፣ ቤይት ላሂያ እና በቤይት ሃኖን አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

በአቅራቢያው የሚገኘው የጃባሊያ ካማል አድዋን ሆስፒታል ዳይሬክተር የሆኑት ሁሳም አቡ ሳፊያ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ህጻናት በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን በሐኪሞች እና በመድሃኒት እጥረት ምክንያት ህሙማንን ለማከም እየታገሉ መሆኑን ገልጸዋል።

“ሠራዊቱ የሕክምና ቡድናችንን እና ሠራተኞቻችንን ካሰረ በኋላ ከመጀመሪያ እርዳታ መስጫዎች ውጭ በካማል አድዋን ሆስፒታል ውስጥ ምንም የቀረ ነገር የለም” ብለዋል።

ሆስፒታሉን የሐማስ ተዋጊዎች እየተጠቀሙበት ነው በማለት የእስራኤል ጦር ባለፈው ሳምንት ወረራ ፈጽሞበታል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር አገራቸው “በአሁኑ ክስተት የዜጎች ህይወት በመጥፋቱ በጣም አሳስቧታል። ይህ አሰቃቂ ውጤት ያስከተለ አሰቃቂ ክስተት ነው” ብለዋል።

በጥቃቱ “በርካታ ህጻናትን የመሞታቸው ዘገባ መኖሩን” ጠቁመዋል።

በአሁኑ ጥቃት “በሲቪሎች ላይ በደረሰው አሳዛኝ ኪሳራ” ምክንያት “ይህ ጦርነት ለምን መቋጨት እንዳለበት የሚያሳይ ሌላ ምስክርነት ነው” ብለዋል ሚለር።

እስራኤል በሰሜን ጋዛ የምታደርገውን ወረራ ሐማስ እንደገና እንዳይሰባሰብ ለመከላከል ታስቦ ነው ስትል ብትገልጽም ሐማስ ግን እንደማይቀበለው አስታውቋል።

ጦሩ ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ በጃባሊያ 40 “አሸባሪዎችን” መግደሉን ገልጿል። በማዕከላዊ ጋዛ ደግሞ ባለፉት 24 ሰዓታት “በወታደሮቹ አቅራቢያ ፈንጂ ለመትከል የሞከሩትን” ጨምሮ “ብዙ አሸባሪዎችን” አስወግጃለሁ ብሏል።

በሰሜናዊው የጋዛ ሰርጥ ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ የገጠመ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የከፋ ህይወት ለመምራት ተገደዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ሃላፊ ቮልከ ተርክ አርብ ዕለት እንዳሉት ከሆነ “የእስራኤል ጦር መላውን ህዝብ ለቦምብ ጥቃት፣ ለከበባ እና ለረሃብ አደጋ እያጋለጠ ነው።”

የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች የተፈናቃዮች መጠለያዎችን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች መካከል እየተንቀሳቀሱ እና ሰላማዊ ዜጎችን ጉዳት ላይ እየጣሉ መሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግሯል።

ሰኞ ዕለት የእስራኤል ፓርላማ ባደረገው ስብሰባ የተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ ኡንርዋ በአገሪቱ እንዳይንቀሳቀስ የሚከለክል ህግ ማውጣቱ ለጋዛ የሚደርሰው እርዳታ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በርካታዎች አስጠንቅቀዋል።

ሐማስ መስከረም 26 በደቡብ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ሲገድል 256 አግቶ መውሰዱን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ የተቀናጀ ጥቃት ጀምራለች።

ሲቪሎችን እና ተዋጊዎችን ሳይለይ እስካሁን በጋዛ ከ 42 ሺህ 924 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ሲል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

እስራኤል ቢቢሲን ጨምሮ የሚዲያ ተቋማትን ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችን ወደ ጋዛ እንዲገቡ ባለመፍቀዷ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለማጣራት አስቸጋሪ አድርጎታል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)