እናት እና አባቷን ለገንዘብ ስትል ገድላ ቤታቸው ውስጥ ለዓመታት የደበቀቸው ልጅ ተፈረደባት

በዩናይትድ ኪንግደም ኤሴክስ በተባለው ግዛት ውስጥ ጡረተኛ እናት እና አባቷን ለገንዘብ ስትል በመግደል ለአራት ዓመታት በቤታቸው ውስጥ የደበቀቸው ልጅ የዕድሜ ልክ እስር ተፈረደባት።

የ36 ዓመቷ ቨርጂኒያ ማካሉህ ጡረተኛ እናት እና አባቷ የሚያገኙትን የጡረታ ገንዘብ እና ሌሎች ገቢዎችን ለመጠቀም ስትል የፈጸመችው ግድያ ለአራት ዓመታት ያህል ሳይታወቅ ቆይቷል።

ለጎረቤት እና ለዘመድ አዛውንቶቹ ወላጆቿ ለእረፍት ወደ ባሕር ዳርቻ አካባቢ መሄዳቸውን በመንገር ማንም ጥርጣሬ እንዳይገባው ያደረገችው ልጅ፤ ከዓመታት በኋላ የተፈጠረን ጥርጣሬ መሠረት በማድረግ ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ግለሰቦቹ በልጃቸው መገደላቸውን አረጋግጧል።

የዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩት የ70 ዓመቱ አባት ጆን ማክሉህ ተመርዘው መገደላቸው ሲታወቅ፣ የ71 ዓመቷ እናት ሉዊስ ደግሞ በስለት እና በጠንካራ ነገር ተመትተው ተገድለው ሁለቱም እዚያው ቤታቸው ውስጥ አስከሬናቸው ተደብቶ ቆይቷል።

ይህ ዘግናኛ የግድያ ወንጀል ሊጋለጥ የቻለው በኢሴክስ አውራጃ የሚገኝ የአዛውንቶች ደኅንነትን የሚከታተል ቡድን ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ ምክንያት ነበር።

የሁለቱን አዛውንቶች ጤንነት በየጊዜው የሚከታተል የሕክምና ባለሙያ ጥንዶቹን ለረጅም ጊዜ እንዳላያቸው በመግለጽ ምን እንዳጋጠማቸው አሳውቆ ነበር።

ልጃቸው ወላጆቿ ከሐኪም ጋር ላላቸው ቀጠሮ መገኘት ያልቻሉበትን የተለያዩ ምክንያቶች ስታቀርብ ቆይታለች። በተጨማሪም የኮቪድ ወረርሽን ተከስቶ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ የአዛውንቶቹ መጨረሻ በጊዜ እንዳይታወቅ አድርጎ ቆይቶ ነበር።

ነገር ግን ፖሊስ ልጃቸውን በሚያናግርበት ጊዜ ስለወላጆቿ ዘወትር የሚያገኘው መልስ ቤት የሉም፣ ወደ ሌላ ቦታ ሄደዋል የሚል መሆኑ አጥጋቢ አልነበረም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ለአዛውንቶቹ ቴሌቪዥን ያከራየ አንድ ጎረቤት ያጋጠመው ነገር ጥርጣሬውን አጠናክሮታል። ከዚያም ምንም እንኳን የቴሌቪዥን ኪራዩን የተዋዋለው ከወላጆቿ ጋር ቢሆንም ልጃቸው ደውላ ኪራዩን እንደሰረዙት አሳወቀቸው።

እሱም ቴሌቪዥኑን ለመውሰድ ሠራተኞቹን ሲልክ ወደ ቤት እንዳይገቡ ቴሌቪዥኑ በር ላይ ተቀምጦ ጠበቃቸው፤ ወደ ቤትም እንዲገቡ አልፈቀደችላቸውም ነበር።

እነዚህ ተደራራቢ ጥርጣሬዎች ባሉበት ሁኔታ ፖሊስ ቤቱን በፈተሸበት ጊዜ ለአራት ዓመታት በተለያየ ሁኔታ ተደብቆ የቆየውን የጥንዶቹን አስከሬን እንዲሁም ሌሎች ሰነዶችን አግኝቷል።

ሰነዶቹ ወላጆቿን በማጭበርበር ገንዘባቸውን አላግባብ መጠቀሟን የሚያመለክቱ ሲሆን፣ በባንክ ካርዳቸውም ከፍተኛ ገንዘብ በስማቸው በዱቤ መጠቀሟን ደርሶበታል።

አንድ ቀን እንደምትያዝ ስትጠብቅ የነበረችው ቨርጂኒያ ፖሊስ ለፍተሻ ወደ ቤታቸው ሲገባ እምብዛም አልደነገጠችም ነበር፤ ይልቁንም ያስደነቃት ነገር ወላጆቿን መግደሏን እስካሁን ሳይደርሱበት መቆየታቸው ነበር። ፖሊሶች እጇ ላይ ካቲና ሲያጠልቁም “እንኳን ደስ ያላችሁ፤ ቢያንስ መጥፏዋን ሴት ይዛችኋል” ብላለች።

ልጅ ቨርጂኒያ ማክሉህ ወላጆቿን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደለች በኋላ የጡረታ ገቢያቸውን፣ የባንክ ካርዳቸውን እና ንብረታቸውን በመሸጥ በአጠቃላይ 149,697 ፓወንድ የሚሆን የገንዘብ ጥቅም አግኝታለች። በአራት ዓመታት ውስጥም በበይነ መረብ አማካይነት በሚካሄድ ቁማር 21,000 ፓወንድ ማውጣቷ ተነግሯል።

የቀረበባበትን የግድያ እና የዝርፊያ ወንጀል የተመለከተው ፍርድ ቤት በቨርጂኒያ ላይ የዕድሜ ልክ እስራት የፈረደባት ሲሆን፣ በዚህም ቢያንስ 36 ዓመቱን በእስር ቤት ማሳለፍ አለባት።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)