እስራኤል በኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች? የኢራንስ ምላሽ ምን ይሆናል?

ኢራን ባለፈው ሳምንት ለፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት እስራኤል የአጸፋ እርምጃ መውሰዷ አይቀሬ ሲሆን፣ የእስራኤል የበቀል ጥቃት ጊዜ እየቀረበ ነው።

ኢራን ጥቃቱን የፈጸመችው ዋነኛ ወዳጆቿ የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ እና የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኢል ሃኒያህ በእስራኤል የተፈጸሙ ናቸው በተባሉ ጥቃቶች በመገደላቸው መሆኑን ጠቅሳለች።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት ከሆነ የእስራኤል የበቀል እርምጃ “ዒላማውን የጠበቀ እና ገዳይ” ይሆናል። አጸፋው ኢራን የማትጥብቀው ዓይነት መሆኑንም አክለዋል።

ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው የባሕረ ሰላጤው አረብ አገራት የአየር ክልላቸውን ለማንኛውም ጥቃት እንዳይፈቅዱ ኢራን አስጠንቅቃለች። ኢራን እንድትጠቃ እስራኤልን የሚረዳ ማንኛውም አገርም የኢራን ዒላማ እንደሚሆንም ገልጻለች።

የእስራኤልን የበቀል እርምጃ በተመለከተ ዋሽንግተን እና ቴል አቪቭ መክረዋል። የኢራን ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ከግምት ውስጥ ከሚገቡት ነገሮች መካከል ናቸው።

በኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ የሚደረግን ማንኛውንም እርምጃ እንደምትቃወም አሜሪካ ከወዲሁ ይፋ አድርጋለች።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከአራት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል። ዋሽንግተን በነዳጅ ተቋማት ላይ በሚደርስ ጥቃት ምክንያት የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን አትቀበልም። ወደ ሌላ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ተጎትታ የመግባትም ፍላጎት የላትም።

የእስራኤል ዒላማ ምን ሊሆን ይችላል?

የእስራኤል አጋሮች በሚያዝያ ወር ከሰጡት ማስጠንቀቂያ አንጻር አሁን ብዙዎቹ ዝምታን መርጠዋል። እስራኤል በሊባኖስ፣ በጋዛ፣ በየመን እና በሶሪያ ያሉ ሁሉንም ጠላቶቿን በአንድ ጊዜ ለመጋፈጥ ቁርጠኛ ሆናለች። የኔታንያሁ መንግሥት ከዚህ አቋም ወደ ኋላ ለመመለስ ምንም ፍላጎት ያለው አይመስልም።

በዩናይትድ ስቴትስ የሳተላይት መረጃ እና የእስራኤል የስለላ ተቋም የሆነው ሞሳድ ኢራን ባሉት መረጃ አቀባዮች በመታገዝ የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) ዒላማ ሊያደርጋቸው የሚችላቸው በርካታ አማራጮች አሉት። እነዚህ ሰፋ ባሉ ሦስት ምድቦች ሊከፈሉ ይችላሉ፡

  • ወታደራዊ ተቋማት – የመጀመሪያው እና ግልጽ የሆኑት ዒላማዎች ኢራን የባለስቲክ ሚሳዔሎችን ያስወነጨፈችባቸው ካምፖች ናቸው። እነዚህም ማስተኮሻ ጣቢያዎች፣ የዕዝ እና የቁጥጥር ማዕከላት፣ ነዳጅ ማከማቻ ጣቢያዎች እና የመሣሪያ የማከማቻዎች ናቸው። አለፍ ሲልም የአብዮታዊው ዘብ ንብረት የሆኑትን የአየር መከላከያዎችን እና ሌሎች የሚሳዔል ማስወጪፊያዎችንም ልትመታ ትችላለች። በኢራን የባሊስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራም ውስጥ የተሳተፉ ቁልፍ ግለሰቦችን መግደል አማራጭ ሊሆን ይችላል።
  • ኢኮኖሚያዊ ተቋማት – ይህ ደግሞ የኢራንን ወሳኝ ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ማጥቃት ሊሆን ይችላል። የፔትሮኬሚካል ማዕከላት፣ የኃይል ማመንጫዎች እና ምናልባትም መርከቦችን ያጠቃልላል። ይህ ግን በጦር ኃይሉ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ይልቅ የተራውን ሕዝብ ሕይወት ስለሚጎዳ ተመራጭ ያልሆነ እርምጃ ይሆናል።
  • ኑክሌር ተቋማት – ይህ ለእስራኤል ትልቁ ዒላማ ነው። ኢራን ለሲቪል አገልግሎት ኃይል ከሚያስፈልገው 20 በመቶ በላይ ዩራኒየምን እያበለፀገች እንደሆነ በተባበሩት መንግሥታት የኑክሌር ተቆጣጣሪ አካል ጭምር የታወቀ እውነታ ነው። ኢራን የኒውክሌር ቦምብ መሥራት ከምትችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ እየሞከረች ነው ብለው እስራኤል እና ሌሎች አገራት ይጠረጥራሉ። ከእስራኤል የዒላማ ዝርዝሮች ውስጥ ፓርቺን፣ የኢራን ወታደራዊ የኑክሌር መርሃ ግብር ማዕከል፣ ቴህራን፣ ቦናብ እና ራምሳርን ጨምሮ በቡሽህር፣ ናታንዝ፣ ኢስፋሃን እና ፌርዶው ያሉ ዋና ዋና ተቋማትን ያካትታል።ኢራን እስራኤል ላይ የፈጸመችው ጥቃት አስደስቷቸው ወደ አደባባይ የወጡ ኢራናዊያን

የኢራን አጸፋ ምን ሊሆን ይችላል

አብዛኛው ስሌት የኢራንን ምላሽ መለየት እና እንዴት ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል የሚለውን ያካትታል። ኢራን በእስራኤል ላይ ያስወነጨፈቻቸው ሚሳዔሎች ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ ማድረጋቸውን እና ለቀደመው ጥቃት ምላሽ ተሰጥቷል የሚል ሐሳብ ነው በኢራን በኩል የተያዘው አቋም። እስራኤል ገፍታ የአጸፋ እርምጃ ከወሰደች ቴሄራንም በተራዋ ምላሽ እንደምትሰጥ በማስጠንቀቅ ላይ ትገኛለች።

ጥቃቱን ተከትሎ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዝሽኪያን “ይህ ካለን አቅም በጣም ጥቂቱ ብቻ ነው” ብለዋል። ኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብም “ፅዮናዊው መንግሥት ለኢራን ምላሽ ከሰጠ አሰቃቂ ጥቃቶች ይደርስበታል” ሲል ፕሬዝዳንቱን መልዕክት አጠናክሮታል።

ኢራን እስራኤልን በወታደራዊ ኃይል ማሸነፍ አትችልም። የአየር ኃይሏ ያረጀ እና የተዳከመ ነው። የአየር መከላከያው ሥርዓቱ ያልዘመነ ከመሆኑም በላይ ለዓመታት በዘለቀው የምዕራባውያን ማዕቀቦች ይበልጥ ተዳክሟል።

አሁንም ግን እጅግ በጣም ብዙ የባላስቲክ እና ሌላ ዓይነት ሚሳዔሎች፤ ፈንጂ የሚሸከሙ ድሮኖች እና በመካከለኛው ምሥራቅ ዙሪያ ያሉ በርካታ ተባባሪ ታጣቂ ቡድኖች አሏት።

ቀጣዮቹ ሚሳዔሎቿ ከወታደራዊ ሰፈሮች ይልቅ የእስራኤልን የመኖሪያ መንደሮችን ሊያጠቁ ይችላሉ። በኢራን የሚደገፉ ሚሊሻዎች እአአ በ2019 በሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ተቋማት ላይ ያደረሱት ጥቃት ጎረቤቶቿ ለጥቃት ምን ያህል ተጋላጭ እንደሆኑ አሳይቷል።

በባህረ ሰላጤው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የአብዮታዊው ዘብ ጓድ ባሕር ኃይል ፈጣን ሚሳዔል ተሸካሚ ጀልባዎች የአሜሪካ ባሕር ኃይል የጦር መርከብን ሊወሩ ይችላሉ።

የባሕር ኃይሉ ትዕዛዝ ከተሰጠው በሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ ላይ ፈንጂዎችን ለማጥመድ ሊሞክር ይችላል። ይህ ደግሞ እስከ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ የሚመላለፍበትን መንገድ ስለሚያቋርጥ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ከኩዌት እስከ ኦማን ደግሞ በባሕረ ሰላጤው አካባቢ እዚህም እዚያም የሰፈሩ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ይገኛሉ። ኢራን ጥቃት ከተሰነዘረባት እስራኤል ላይ ብቻ ሳይሆን ጥቃቱን የሚደግፉትን አገራትን ዒላማ እንደምታደርግ አስጠንቅቃለች።

በዚህ ሁኔታ ደግሞ አሜሪካ እና ሌሎቹም ጥቃት የሚሰነዘርባቸው አገራት ወደ ግጭቱ ተስበው ሊገቡ እና በኢራን ላይ የአጸፋ ጥቃት በመሰንዘር መጠነ ሰፊ ጦርነት ሊከሰት ይችላል።

ስለዚህም በቴል አቪቭ እና በዋሽንግተን ያሉ የእስራኤል እና የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት ሊያጤኗቸው ከሚችሏቸው ሁኔታዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)