ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ክፍል ተማሪዎች ፊደል መለየት እንደማይችሉ ጥናቱ አመለከተ

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ክፍል ተማሪች 56 በመቶዎቹ ምንም ዓይነት ቃል ማንበብ እንደማይችሉ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ባደረገው ጥናት አመልክቷል።

አገልግሎቱ በጥናቱ ተሳተፊ ካደረጋቸው የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ቢያንስ አንድ ቃል ማንበብ የሚችሉ 37 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ በአገልግሎቱ የትምህርት ምዘናና ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤፋ ጉርሙ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የተቀሩት 63 በመቶዎቹ አንድም ቃል ማንብብ የማይችሉ (Zero renderers) ናቸው።

በሌላ በኩል 49 በመቶ የሚሆኑት የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች አንድም ቃል ማንብብ እንደማይችሉ ጥናቱ ማመልከቱን ኃላፊው ታናግረዋል።

በድምሩ በጥናቱ ከተሳተፉት የ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 56 በመቶ የሚሆኑት በትምህርት ደረጃቸው ከሚጠበቀው በተቃራኒ አንድም ቃል ማንበብ እንደማይችሉ ጥናቱ አሳይቷል።

ተመሳሳይ ጥናት ባለፈው ዓመት መካሄዱን የገለጹት ኤፋ (ዶ/ር) በዚያ ጥናት ከ2ኛ ክፍል ተማሪዎች ቢያንስ አንድ ቃል ያነበቡት ተማሪዎች 31 በመቶዎቹ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከ3ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ 55 በመቶ የሚሆኑት ከየትኛውም ፊደል ጋር እንደማይተዋወቁ ጥናቱ ጠቁሟል።

በባለፈው ዓመት በጥናቱ የተሳተፉ የ2ኛ እና የ3ኛ ክፍል ተማሪች በድምሩ 68 በመቶ የሚሆኑት አንድም ቃል ለማንብብ ተቸግረዋል።

በዚህ ንባብን መሠረት ባደረገ ጥናት ከ9 ክልሎች የተወጣጡ ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

ተማሪዎቹ ከ401 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተመረጡ ናቸው።

በዘፈቀደ (Random sampling ) የተመለመሉት ተማሪዎቹ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተጻፉ 50 ቃላት ቀርበውላቸው ቃላቱን ያነቡ እንደሆነ ተጠይቀዋል።

ትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ የጥናት ስልት የተመረጡ ናቸው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ በደቂቃ ቢያንስ 60፤ የ3ኛ ክፍል ተማሪ ደግሞ 90 ቃላትን እንዲያነብ ይጠበቃል። ይህ ዓለም አቀፍ መመዘኛ ሀገራት እንደሚያስተምሩባቸው ቋንቋዎች ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይችላል።

በዚህ መሠረት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚማሩት የ2ኛ ክፍል ተማሪዎች ቢያንስ በደቂቃ 43 እንዲሁም የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች 53 ቃላትን እንዲያነቡ ይጠበቃል።

ይሁን እንጂ 56 በመቶ የሚሆኑት የ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች ከ50ዎቹ ቃላት በተሰጣቸው ጊዜ አንዱንም ቃል ማንበብ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጥናቱ ለታዳጊ ሀገራት ተማሪዎች የንባብ እውቀት መለኪያ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ መስፈረት እንደተከናወነም ኤፋ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በአፋርኛ፣ በሶማሊኛ፣ በሀዲይኛ፣ በወላይትኛ፣ በሲዳምኛ እና ቤንሻንጉል ውስጥ በሚነገረው በርታ ቋንቋ የሚማሩ ተማሪዎች በዚህ ጥናት ተሳትፈዋል።

“ልጆቹ የተጠየቁ ፊደልን የመለየት፣ ቃላት ወይም አጭር አንቀጽ የማንበብ እና የማድመጥ እና የመረዳት ችሎታችን ነው የተጠየቁት . . . ግኝቱን ስናየው ተማሪዎቹ ከተቀመጠው ደረጃ በታች ነው ያሉት” ሲሉ ኃላፊው ገልጸዋል።

ጥናቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ ምክር ሀሳብ ማቅረቡንም ጠቁመዋል።

“ልጆች ምንም ፊደል ሳይለዩ ወደ 2ኛ እና 3ኛ ክፍል እየመጡ እንደሆኑ በመገንዘብ እንደ ሀገር የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት ቅደሚያ ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል።

በተጨማሪም “በተለምዶ ታዳጊ የሚባሉ ክልሎች በጣም ወደ ኋላ የቀሩ እና ምንም ቃላት የማያውቁ ተማሪዎች ስለሚበዙ ልነሱ ትኩረት የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻች” ሲሉ አንስተዋል።

በአዲሱ የትምህርት ስርዓት ለመምህራን ስልጣና በቂ ትከረት እንዲሰጥ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ቤተ መጽሀፍትን ጨምሮ በቂ መሠረተ ልማት እንዲሟላ የሚሉት በጥናቱ ከተቀመጡት ምክረ ሀሳቦች መካከል አንዱ ነው።

ተቋሙ መሰል ጥናቶችን ከቅደመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ እንደሚያከናውን የተናገሩት ኃላፊው ይህ ጥናት “ትምህርቱ በጤነኛ ሁኔታ እየሄደ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ለማወቅ” የተደረገ መሆን አመልክተዋል።

በዚህ መነሻ በጥናቶቹ ግኝቶች መሰረት በፍጥነት ማስተካከያ እንዲደረግ ለፖሊስ አውጪዎች እና ለስፈጻሚዎች የሚቀርብ እንደሆነም አክለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )