ኢራን እና እስራኤል ለምን ደመኛ ጠላቶች ሆኑ?

ወትሮም በጠላትነት የሚተያዩት እስራኤል እና ኢራን ባለፉት ሳምንታት ወደ ለየለት ፍጥጫ በመግባታቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት አይሏል።

እስራኤል በሶሪያ መዲና ደማስቆ የሚገኘውን የኢራን ቆንስላን ጽህፈት ቤት በቦምብ ማጋየቷ ነው ሁለቱ አገራት ወደ ቀጥተኛ ጥቃት እና ፍጥጫ እንዲገቡ ያደረጋቸው።

ባለፍነው ቅዳሜ ሌሊት ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏ ቀጠናውን ከውጥረት ወደ ለየለት ጦርነት የሚያመራ ሁኔታን ፈጥሯል ተብሎለታል።

ከዚህ ጥቃት በፊት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አገራቸው ከኢራን ሊቃጣባት የሚችለውን ጥቃት ለመመከት የመከላከያ ሥርዓቶቿ በተጠንቀቅ እንዲቆም ማድረጋቸውን ለጦር ካቢኔያቸው ተናግረው ነበር።

እስራኤል እና ኢራን ለዘመናት የዘለቀ ባላንጦች ናቸው። በሁለቱ አገራት መካከል የቆየው ኃያሉ የጠላትነት ስሜት በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲርቅ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።

ቴህራን ከምድረ ገጽ እንድትጠፋ የምትሻትን እስራኤልን “ትንሿ ሰይጣን” ስትላት፣ አሜሪካንን ደግሞ “ትልቋ ሰይጣን” በማለት ለሁለቱም ያላትን ተመሳሳይ አመለካከት ስታንጸባርቅ ቆይታለች።

ኢራን እስራኤል ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ከመፈጸም ይልቅ በገንዘብ እና በትጥቅ የምትደግፋቸውን ቡድኖች በመጠቀም በእጅ አዙር እስራኤልን ላይ ጥቃት እንደምታስፈጽም ይነገራል።

በእነዚህ ሁለት ኃያላን ጠላቶች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች ለበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል።

በጋዛ የተከሰተው ጦርነት ደግሞ ይበልጥ ሁኔታዎችን አባብሷል።

የቴህራን እና የቴል አቪቭ ጠላትን ምንጭ ምንድን ነው?

እስከ አውሮፓውያኑ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የነበረው ግንኙነት አዎንታዊ ነበር።

እስራኤል በ1948 ላይ ከተመሠረተች በኋላ ከግብፅ በመቀጠል እውቅና በመስጠት ሁለተኛዋ እስላማዊት አገር የሆነችው ኢራን ነበረች።

በወቅቱ ኢራን ትመራ የነበው በመካከለኛው ምሥራቅ ጠንካራ የአሜሪካ አጋር በነበረው የሻህ ፓህላቪ ሥርወ መንግሥት ነበር።

እአአ 1979 ላይ የኢራን እስላማዊ አብዮትን ተከትሎ መንግሥታዊ ለውጥ ሲደረግ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት መልኩን ቀየረ።

የአያቶላህ ኾሜኒ እስላማዊ አብዮት የሻህ መንግሥትን ገርስሶ እራሱን የጭቁኖች መሪ አድርጎ ብቃ አለ። የዚህ መንግሥት ዋነኛ መለያም የአሜሪካን እና የአጋሮቿን “ኢምፔሪያሊዝም” መቃወም ሆነ።

የአያቶላ አስተዳደር ኢራን ከእስራኤል ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠ። ለእስራኤል ፓስፖርትም እውቅና ነስቶ በቴህራን የነበረውን የእስራኤል ኤምባሲን፣ የእስራኤል መንግሥትን ሲዋጋ ለነበረው ለፍልስጤም ነጻነት ግንባር (ፒኤልኦ) አሳልፎ ሰጠ።

በመላው ዓለም የሚካሄዱ ግጭቶችን የሚያጠናው ኢንተርናሽል ክራይሲስ ግሩፕ ዳይሬክተር የሆኑት አሊ ቫኤዝ የኢራን መሪዎች ጥላቻ የጀመረው ገና ከጠዋቱ ነው ይላሉ።

“እስራኤል ላይ ያመረረ ጥላቻ የአዲሱ የኢራን መንግሥት መገለጫ የሆነው፤ አብዛኞቹ የኢራን አመራሮች እንደ ሊባኖስ ባሉ አካባቢዎች ከፍልስጤም ታዋጊዎች ጋር ወታደራዊ ልምምድ እና የሽምቅ ውጊያ ሲያደርጉ ቅርበት ስለፈጠሩ ነው” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም አዲስቷ ኢራን እራሷን የፍልስጤማውያን ጉዳይን በማጉላት የሙስሊሞች ተቆርቋሪ አገር ሆና ለመታየት ስለምትሻ ፀረ እስራኤል ሆና ብቃ ብላለች።

እንደ ቫኤዝ ገለጸ ቀደም ባሉት ዓመታት ለእስራኤል ትልቋ ስጋት ኢራቅ በነበረችበት ዘመን፣ ለኢራን ትልቅ ትኩረት አትሰጥም ነበር ይላሉ።

ከሳዳም ሁሴን መንግሥት መውደቅ በኋላ እስራኤል በቀጠናው ለደኅንነቷ አደገኛዋ አገር ኢራን መሆኗን መረዳት ጀመረች።

የእስራኤል እና ኢራን የእጅ አዙር ጦርነት

ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ እና በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ከእስራኤል ውጪ በቀጠናው ጠንካራ አገር የሆነችውን ሳዑዲ አረቢያን በጥርጣሬ ነው የምትመለከታት።

በአብዛኛው ሱኒ ሙስሊሞች በሚኖሩበት ቀጠና፣ የብዙኃን ሺዓ ሙስሊሞች መገኛ የሆነችው ኢራን ወደፊት ሊቃጣባት ከሚችል ጥቃት እራሷን ለመጠቅ ስትል በመረጠችው ስትራቴጂ ከተቀረው ዓለም ልትነጠል መቻሏን ቫዬዝ ይገልጻሉ።

በዚህም የኢራን መንግሥት ከአገራት ይልቅ በአካባቢው የተለያዩ ዓላማዎችን አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር በማበር ፍላጎቷን ለማስጠበቅ ስትጥር ቆይታለች።

ኢራን “አክሲስ ኦፍ ሬዚዝታንስ’ ስትል የምትጠራው ስብስብ በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በኢራቅ እና በየመን ተንሰራፍቶ ይገኛል።

ቴህራን በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን እና መቀመጫውን በሊባኖስ ያደረገውን ሂዝቦላህን ታስጣጥቃለች።

ጋዛን ለሚያስተዳድረው ሐማስ፣ በየመን ለሚንቀሳቀሱት ሁቲ አማጺያን ኢራን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በአካባቢው ተጽእኖ ስትፈጥር ቆይታለች።

እስራኤል ደግሞ ኢራን በዙሪያዋ ይህ ሁሉ ስታከናወን ዝም ባላ አልተመለከተችም። ኢራን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን እንዲሁም በዙሪያዋ ባሉ አገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በቴህራን የሚደገፉ ቡድኖች ላይ እርምጃ ስትወስድ ቆይታለች።

ባለፉት ዓመታት በኢራን እና በእስራኤል መካከል የነበረው ጦርነት “ከመጋረጃ ጀርባ” ያለ ጦርነት ተብሎ ሲገለጽ ኖሯል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሁለቱ አገራት በሌሎች አገራት ውስጥ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ኃላፊነት ሲወስዱ አይታይም።

በተለይ ኢራን እስራኤልን በቀጥታ ከመተንኮስ ይልቅ በምትደግፋቸው ታጣቂ ቡድኖች በኩል በእጅ አዙር ስታጠቃት ኖራለች።

እአአ 1992 የወቅቱ የሂዝቦላህ መሪ የነበሩት አባስ አል-ሙሳዊ ግድያን ተከትሎ ለኢራን ቅርበት ያለው እስላማዊ ጂሃድ ቡድን በቦነስ አይረስ የሚገኝ የእስራኤል ኤምባሲን በቦምብ አጋይቶ 29 ሰዎችን ገድሎ ነበር።

እስራኤል ለሂዝቦላህ መሪ ግድያ ኃላፊነት ባትወስድም የቴል አቪቭ የደኅንነት ተቋም የሆነው ሞሳድ ግድያውን መፈጸሙ ይታመናል።

እስላማዊው የጂሃድ ቡድንም ቢሆን የእስራኤልን ኤምባሲ ያጋየው ያለ ኢራን እውቅና እንደማይሆን ግልጽ ነው።

የኢራን ኑክሌር እና የእስራኤል ስጋት

እስራኤል የኢራን ጉዳይ አንገብጋቢ የሚሆንባት የአያቶላህ ቴህራን የኑክሌር ፕሮግራም ነው። ለዚህም ኢራን የኑክሌር ቦምብ ባለቤት እንዳትሆን እስራኤል የተቻላትን ስታደርግ ቆይታለች።

ኢራን ግን የኑክሌር ፕሮግራሟ ብቸኛው ዓላማ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚውል ሰላማዊ ዓላማ ያለው ነው ቆይታለች።

ይህን ምክንያት ጨርሶ የማትቀበለው ኢራን በዲፕሎማሲ በኩል ኢራን ላይ ማዕቀብ ከማስጣል አልፋ ከአሜሪካ ጋር አብራ የኢራንን የኑክሌር ማብላያ ጣቢያን ‘ስቱአኔት’ በሚባል ኮምፒዩተር ቫይረስ አውካ ከፍተኛ ጉዳት አድርሳ ነበር።

እስራኤል የኢራን ኮምፒዩተሮችን ብቻ ሳይሆን ሳይንቲስቶቿንም ዒላማ እያደረገች በቴህራን ጎዳናዎች ላይ ገድላለች።

በአውሮፓውያኑ 2020 በጉምቱው የኑክሌር ሳይንስ ተመራማው ሞህሰን ፋክሪዛሄድ ላይ የተፈጸመው ግድያም ብዙ ያነጋገረ ነበር።

የእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ እኒህን ተመራማሪ ለመግደል ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች ሳይሳካሉት ቆይተው ነበር፣ ከአራት ዓመታት በፊት ከኢራን መዲና ቴህራን ወጣ ብሎ ከሚገኝ ስፍራ ፋክሪዛሄድን የመግደል ውጥኑ የሰመረለት።

ኢራንም ብትሆን በእስራኤል ላይ ድሮኖችን እና ሮኬቶችን ስታስወነጭፍ እንዲሁም የእስራኤል ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።

የአረብ አብዮትን ተከትሎ እአአ 2011 በሶሪያ የተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ሌላኛው የእስራኤል እና የኢራን የቅራኔ ምንጭ ነው።

ምዕራባውያን እንደሚሉት ከሆነ አመጽ የተነሳባቸውን ፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድን በሥልጣን ለማቆየት ኢራን ጦር መሳሪያ፣ ገንዘብ እና ሥልጠና የሚሰጡ የጦር መኮንኖችን ልካለች።

እስራኤል ደግሞ ጠንካራው የሊባኖስ ሂዝቦላህ ቡድን ከኢራን የሚገኛቸው ድጋፎች በሶሪያ በኩል የሚያልፉ ስለነበሩ የባሻር አል-አሳድ መንግሥት መወገድን አጥብቃ ትሻ ነበር።

እስራኤል እና ኢራን በየብስ ላይ “ከመጋረጃ ጀርባ” የሚያካሂዱት ጦርነት ወደ ባሕር ላይም ተሸጋግሮ በተለያዩ ጊዜያት በመርከብ የጉዞ መስመሮችም ላይ ስጋትን ሲደቅን ቆይቷል።

እአአ 2021 ላይ እስራኤል ዕቃ ጫኝ መርከቦቿ ላይ በኦማን ባሕረ ሰላጤ በኩል ሲያልፉ በኢራን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ከሳለች። ኢራን ደግሞ ቀይ ባሕር ላይ ሲጓዝ በነበረው መርከቧ ላይ ለደረሰው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋለች።

የሐማስ ጥቃት እና የሁለቱ አገራት ፍጥጫ

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የተጀመረው የጋዛው ጦርነት መካከለኛው ምሥራቅን ብሎም መላው ዓለምን ከማሳሰቡ ባሻገር፣ በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለውን ጠላትነት አንድ እርምጃ ከፍ አደረገው።

በኢራን የሚደገፈው ፍልስጤማዊው ቡድን ሐማስ የእስራኤልን ድንበር ተሻግሮ ድንገተኛ ጥቃት ፈጸሞ ከ1ሺህ በላይ እስራኤላውያንን ገደለ።

ይህ አጋጣሚ ኢራን እና እስራኤልን ወደ ለየለት ጦርነት ያስገባል ሲሉ በርካቶች ገና ከመነሻው ስጋታቸውን ሲያስቀምጡ ነበር።

ለስድስት ወራት እስራኤል የጋዛውን አስተዳዳሪ ሐማስን ለማውደም ጠንካራ ወታደራዊ ዘመቻ ስታካሂድ ቆይች። በዚህ ወታደራዊ ዘመቻ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ ከ34 ሺህ ያላነሱ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ፣ ኢራን እና ሌሎችም ጦርነቱ ይቁም ሲሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

በአካባቢው የሚገኙ እና በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖችም እስራኤልን ዒላማ ያደረጉ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ሲያስወነጭፉ ቆይተዋል።

በዚህ መካከል የኢራን ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን እና የኑክሌር ሳይንቲስቶችን እያደነ የሚያጠፋው የእስራኤል የስለላ ተቋም፣ ሶሪያ ውስጥ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጸመ።

በዚህ ጥቃትም ዒላማ ሆነው የተገደሉት ቀላል የሚባሉ የኢራን ባለሥልጣናት አልነበሩም። ሁለት ጄኔራሎች እና በርካታ የጦር መኮንኖች ደማስቆ ውስጥ እንደወጡ ቀርተዋል።

ነገር ግን እስራኤል በኢራን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት በይፋ ኃላፊነቱን ባትወስድም ዓለም ግን ከእሷ ውጪ ይህንን ጥቃት ሊፈጽም የሚችል ኃይል እንደሌለ ይስማማል።

ኢራንም የደረሰባትን ጉዳት በውስጧ ይዛ ዝም ብላ እንደማትቀመጥ በይፋ ደጋግማ ስታስታውቅ ዒላማዋም እስራኤል መሆኗን ገልጻ፣ የአጸፋ እርምጃ መውሰዷ እንደማይቀር ስታስጠነቀቅ ቆይታ ነበር።

ባለፈው ቅዳሜም ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ እስራኤልን ዒላማ በማድረግ ከ300 በላይ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን አስወንጭፋ በሁለቱ አገራት መካከል የኖረው ውጥረት መልኩን እንዲቀይር አድርጋለች።

ምንም እንኳን የኢራን ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በእስራኤል እና በአጋሮቿ የከሸፈ ቢሆንም፣ እስራኤል ለተሰነዘረባት የኢራን ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ዓለም በስጋት እየተጠባበቀው ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን መንግሥት እስራኤልን በቀጥታ ለማጥቃት የወሰደው እርምጃ ምን ያህል ትክክለኛ ነበር ሲሉ በርካቶች እየጠየቁ ይገኛሉ።

በአገር ውስጥ ምጣኔ ሃብት የተዳከመው እና የፖለቲካ ጥያቄ የሚነሳበት የኢራን መንግሥት የምዕራባውያን ወዳጅ በሆነችው እስራኤል ላይ የወሰደው እርምጃ በዓለም መድረክ የበለጠ የተገለለ እንዲሆን የሚያደርግ ነው ይላሉ ተንታኞች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(BBC)