አሜሪካዊው ራፐር ዲዲ ታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሷል የሚል አዲስ ክስ ቀረበበት

ሾን ኮምብስ አሊያም በመድረክ ስሙ ዲዲ እየተባለ የሚጠራው አሜሪካዊ ራፐር የመድፈር ወንጀል ፈፅሟል፣ ወሲባዊ ብዝበዛ እና ጥቃት አድርሷል የሚል አዲስ ክስ ቀረበበት።

ሰኞ ዕለት ኒው ዮርክ ግዛት በሚገኘው ፌዴራል ፍርድ ቤት ክሳቸውን ያስገቡት ሁለት ሴቶች እና አራት ወንዶች ናቸው።

የክስ መዝገቡ ከ1995 እስከ 2021 ባለው ጊዜ የተፈፀሙ ድርጊቶችን ያካትታል።

ስማቸው ያልተጠቀሰው ከሳሾች አንዳንዱ ድርጊት የተፈፀመብን በራፐሩ መኖሪያ ቤት በሚዘጋጁ ‘ፓርቲዎች’ ላይ፤ በርካታ ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት ነው ይላሉ።

የዲዲ ጠበቆች ክሱን ያጣጣሉት ሲሆን ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ ደንበኛችን “ማንም ሰው ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሶ አያውቅም – አዋቂዎችም ሆኑ ታዳጊዎች፤ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች” ብለዋል።

ክሱን ካቀረቡት ሰዎች መካከል አንዱ በአውሮፓውያኑ 1998 የ16 ዓመት ታዳጊ ሳለ የዲዲን ፓርቲ ታድሞ እንደነበር ይናገራል። ከሳሹ እንደሚለው በፓርቲው ላይ በርካታ ታዋቂ አርቲስቶች እና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተው ነበር።

ታዳጊው ወደ መፀዳጃ ቤት እየሄደ ሳለ ዲዲን አግኝቶት ገለል ያለ ሥፍራ ሄደው ወደ ሙዚቃው ዓለም እንዴት መግባት እንደሚቻል አማክሮታል።

ከሳሹ አክሎ ከዲዲ ጋር እያወሩ ሳለ ድንገት ዲዲ ልብሱን እንዲያወልቅ እንደጠየቀው ይናገራል። ከሳሹ ግለሰብ ፓርቲው ላይ መገኘቱን የሚያሳይ ፎቶ ያቀረበ ሲሆን የግለሰቡ ፊት እንዲሸፈን ተደርጓል።

ክሱ እንደሚለው ዲዲ በወቅቱ ወደ ሙዚቃ መግባት ለሚሹ ሰዎች “ወደዝና የሚያደርስ ማማ” ነበር።

ሰኞ ዕለት በቀረበ ሌላ መዝገብ አንዲት ሴት በአውሮፓውያኑ 2004 ገና የ19 ዓመት ታዳጊ ሳለች ዲዲ ሆቴል ውስጥ ደፍሮኛል ስትል ከሳለች።

የክስ መዝገቡ በወቅቱ ራፐሩ ሆቴል ውስጥ በሚያዘጋጀው ፓርቲ ላይ እንድትታደም ጋብዟት ሲያበቃ በፓርቲው ላይ ስትገኝ ግን “ትንኮሳ ፈፅሞባት ቀጥሎም ደጋግሞ ደፍሯታል” ይላል።

የቴክሳሱ ሕግ አዋቂ ቶኒ በዝቢ የከሳሾቹ ጠበቃ ናቸው። ጠበቃው እንደሚሉት ሌሎች ከ100 በላይ ሰዎች ራፐሩ ወሲባዊ ጥቃት፣ መድፈር እና ሌሎች ጥቃቶች ፈፅሞብናል ሲሉ ለመክሰስ በዝግጅት ላይ ናቸው።

ጠበቃው አክለው እንደሚሉት ክሱን ለማቅረብ እየተዘጋጁ ካሉት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ድርጊቱ ተፈፀመብን በሚሉበት ወቅት ሕፃናት ነበሩ።

በዝቢ እንደሚሉት በሚቀጥሉት ሳምንታት በርካታ ሰዎች ዲዲ እና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ወንጀል ፈፅመውብናል የሚል ክስ ለማቅረብ ማስረጃ እያሰባሰቡ ይገኛሉ።

አሜሪካዊው ጉምቱ የሙዚቃ ሰው ሾን ‘ዲዲ’ ኮምብስ ወሲባዊ ጥቃት እና ብዘበዛ በማድረስ እንዲሁም የመድፈር ወንጀል በመፈፀም ክስ ሲቀርብበት ይህ አዲስ አይደለም።

ራፐሩ የሚቀርቡበትን ወቀሳዎች እና ክሶች ሙሉ በሙሉ ያስተባብላል።

በፌዴራል መንግሥት በማጭበርበር ወንጀል እና ወሲባዊ ዝውውር በመፈፀም ተከሶ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው ዲዲ በአውሮፓውያኑ ግንቦት 5/2025 ችሎት ፊት እንዲቀርብ ቀጠሮ ተሰጥቶታል።

ዲዲ በኒው ዮርክ ግዛት ብሩክሊን ከተማ በሚገኘው ሜትሮፖሊታን ዲቴንሽን ሴንተር የተባለ ማቆያ ነው ያለው።

ጠበቃዎች እስር ቤቱ “አስከፊ ሁኔታ ላይ ያለ ነው” በሚል ራፐሩ ቀጠሮው እስኪደርስ ድረስ በዋስ ተለቆ እንዲቆይ እየተከራከሩ ይገኛሉ።

ነገር ግን የኒው ዮርክ ፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ ሾን ኮምብስ “ከሀገር ሊጠፋ ይችላል” በሚል ምክንያት የጠበቃዎቹን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)