ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ዕጩ ሆነች

የቢቢሲ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ማን ልትሆን ትችላለች? ድምፅ መስጠት ተጀምሯል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ እግር ኳስ ተመልካቾች ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ። የዘንድሮ ዕጩዎች ባርብራ ባንዳ፣ አይታና ቦንማቲ፣ ናኦሚ ግርማ፣ ካሮላይን ግራሀም ሀንሰን እና ሶፊያ ስሚዝ ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2015 የተጀመረው የቢቢሲ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማት 10ኛ ዓመቱን ይዟል።

አድናቂዎች እስከ ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም. ድረስ ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ። አሸናፊዋ ኅዳር 17/2017 ዓ.ም. ይፋ ትደረጋለች።

ለዘንድሮው ሽልማት የታጩት አምስቱ እግር ኳስ ተጫዋቾች በዘርፉ ባለሙያዎች የተመረጡ ናቸው።ለቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማት የታጩ (ከግራ ወደ ቀኝ) ባርብራ ባንዳ፣ አይታና ቦንማቲ፣ ናኦሚ ግርማ፣ ካሮላይን ግራሀም ሀንሰን እና ሶፊያ ስሚዝ

ናኦሚ ግርማ ማን ናት?

  • ዕድሜ፡ 24
  • የምትጫወትበት ቦታ፡ ተከላካይ
  • ቡድን፡ ሳን ዲየጊ ዌቭ እና የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ቡድን

የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኤማ ሀየስ “እስከዛሬ ካየኋቸው ተከላካዮች ምርጧ ናት” ስትል ናኦሚን ትገልፃታለች። ለአገሯ እና ለክለቧ የጀርባ አጥንት ናት።

ከኢትዮጵያውያን እናት እና አባት የተወለደችው የ24 ዓመቷ ናኦሚ የአሜሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብላ የተመረጠች የመጀመሪያዋ ተከላካይ ናት።

የዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የኦሊምፒክ ወርቅ ባለቤት ሲሆን እያንዳንዱን ደቂቃ ተጫውታለች። የኋላ ደጀን የምትባለው ናኦሚ ኳስ በመቆጣጠር እና በመሪነት ችሎታዋ አድናቆት ይጎርፍላታል።

ምስጋና ለኦናሚ ግርማ ይሁንና የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በ2024 የፓሪስ ወርቅ፣ ኮንካካፍ ጎልድ ዋንጫ እና ሺ ቢሊቭስ የተባለው ዋንጫ ባለቤት መሆን ችላለች።

ናኦሚ በክለብም ዋንጫ አልተለያትም። ቡድኗ ሳን ዲየጎ ዌቭ የኤንደብሊውኤስኤል እና የቻሌንጅ ዋንጫዎችን አንስታለች።

ከናኦሚ አንደበት

በፓሪስ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን ምን ይመስላል?

“በጣም ልዩ ነበር። አሠልጣኝ ቀይረን፤ እንደዚያ ተጫውተን ባለድል መሆናችን በጣም አስደስቶናል” ትላለች ናኦሚ።

ናኦሚ እናት እና አባቷ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ስላሳደረባት በጎ ተፅዕኖም ተጠይቃለች።

“ወላጆቼ ኢትዮጵያ ነው የተወለዱት። ገና በ20ዎቹ ዕድሜያቸው ነው ወደ አሜሪካ የመጡት። አባቴ ስደተኛ ነበር። በሱዳን አቋርጦ ነው ካሊፎርኒያ የገባው። እናቴ ደግሞ ለትምህርት ነው ወደ ዩኤስ የመጣችው” ስትል ታስረዳለች።

“ባህሉ፣ ምግቡ፣ ቋንቋው፤ ሁሉም ነገር ልዩ ነው። ካሊፎርኒያ ሳን ሆዜ ሳድግ ማኅበረሰቡ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቶልኛል። እግር ኳስ መጫወት የጀመርኩትም እዚያ ነው።”

ናኦሚ ተከላካይ መስመር ላይ መጫወቷን ትወደዋለች። የክለብ እና የብሔራዊ ቡድን አጋሮቿ በጋራ በመጫወት ታምናለች ይሏታል።

የወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኤማ ሀየስ ስለናኦሚ ግርማ ተናግራ አትጠግብም።

“እስከዛሬ ካየኋቸው ተከላካዮች ምርጧ ናት። ሁሉንም ነገር ተክናለች። በተጠንቀቅ ነው የምትጠብቀው፣ ጠንካራ ተከላካይ ናት፣ ቡድኑን መምራትም ላይ ጎበዝ ናት” ትላለች።

ለቢቢሲ ስፖርት ምርጥ ሴት ተጫዋች ተብላ የታጨችው ሌላኛዋ አሜሪካዊት ሶፊያ ስሚዝ “በዓለማችን ምርጧ ተከላካይ ናት። የቡድናችን የጀርባ አጥንት ናት” ስትል ናኦሚን ታሞካሻታለች።ናኦሚ በ2024 ያገኘቻቸው ሽልማቶች

ስለናኦሚ አንዳንድ እውነታዎች

  • ናኦሚ ገና ልጅ ሳለች አባቷ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባቋቋመው ክለብ ውስጥ ትጫወት ነበር
  • ከእግር ኳስ በተጨማሪ ቅርጫት ኳስ እየተጫወተች ነው ያደገችው። ጂምናስቲክም ትሠራ ነበር
  • ኮመን ጎል ለተባለ በአእምሮ ጤና ላይ የሚሠራ በጎ አድራጊ ድርጅት አባል ነበረች
  • በ2024 የአሜሪካ ዓመቱ ምርጥ ተጫዋች እና የሊጉ ምርጥ ተከላካይ ሆና ተመርጣለች። የፓሪስ ኦሊምፒክ ወርቅ ባለቤትም ናት

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)