ቴሌግራም፡ ‘ኪሳችን ውስጥ የሚገኝ ጨለማው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ’

ከወራት በፊት አንድ ፅሑፍ ለማሰናዳት ጥናት እያካሄድኩ ነበር። ቴሌግራሜን ስከፍት አደገኛ ዕፅ ከመሸጥ ጋር የተያያዘ አንድ ‘ቻናል’ ውስጥ ራሴን አገኘሁት።

ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የኮምፒውተር ሲስተም ጠለፋ እና የተሰረቁ ክሬዲት ካርዶችን የተመለከተ ቻናል ውስጥ መግባቴን አየሁ።

ቆይቶ የገባኝ ነገር የእኔ ቴሌግራም ‘ሴቲንግ’ ሰዎች ያለእኔ ፈቃድ የፈለጉት ቻናል ውስጥ እንዲያስገቡኝ የሚያስችል መሆኑ ነው። ነገር ግን ይህን ካወቅኩ በኋላም ቢሆን ምን እንደሚሆን ለማየት ክፍት አድርጌው ቆየሁ።

ከወራት በኋላ ያለ እኔ እውቅና የቴሌግራም አካውንቴ 82 የቴሌግራም ቡድኖች ውስጥ ተጨምሮ አገኘሁት።

ምንም እንኳ ‘ሴቲንጉን’ ባስተካክለውም ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ በጣም አደገኛ ከሚባሉ ሕጋዊ ያልሆኑ ቻናሎች በሺዎች የሚቆጠሩ መልዕክቶች ይጠብቁኛል።

አሁን ቢሊየነሩ የቴሌግራም ባለቤት ፈረንሳይ ውስጥ በፖሊስ መታሰሩን ተከትሎ ይህ የማኅበራዊ ሚድያ ትስስር መድረክ የይዘት ቁጥጥር አያሻውም ወይ? የሚለው ጥያቄ መነሳት ጀምሯል።

ፓቬል ዱሮቭ ሕጋዊ ያልሆኑ የገንዘብ ልውውጦች እንዲካሄዱ፣ የዕፅ ንግድ፣ ማጭበርበር እና የሕፃናት ወሲብ ነክ ምሥሎች እንዲስፋፉ ፈቅዷል በሚል ነው ክስ የተመሠረተበት።

እርግጥ ነው በሌሎች ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ ሕጋዊ ያልሆነ በርካታ ድርጊቶች ይታያሉ። ነገር ግን እኔ በልምዴ ያየሁት፤ በጣም ሰፋ ያለ በርካታ የሕግ አስከባሪ አባላትን ሲያስጨንቅ የኖረ እንቅስቃሴ ነው።

እነሆ ያለእኔ ፈቃድ የገባሁባቸው የቴሌግራም ቻናሎች ምን እንደሚመስሉ ላካፍላችሁ ወደድሁ።

የቴሌግራም መተግበሪያዬ ሕጋዊ ያልሆኑ ምርቶች እና አገልግሎቶች መለዋወጫ ሆኗል። ይህን ለማድረግ እኔ ‘ሰርች’ ማድረግ አይጠበቅብኝም።

ሁሉም ምሥሎች የተጫኑት የቴሌግራም ቡድኖች ላይ ነው። የገፆቹን ስም የሸፈንነው ይህን ድርጊታቸውን ላለማበረታት እና ቻናሎቹን ላለማስተዋወቅ ነው።

እንደ ፓትሪክ ግሬይ ያሉ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያዎች በደተጋጋሚ ቴሌግራም “ኪሳችን ውስጥ የሚገኝ የጨለማው በይነ-መረብ ነው” የሚሉት ወደው አይደለም።

የፓቬል ዱሮቭን በቁጥጥር ሥር መዋል ተከትሎ ፓትሪክ ግሬይ፤ ‘ሪስኪ ቢዝነስ’ በተሰኘው ፖድካስት ቴሌግራም ለዓመታት የወንጀለኞች መፈንጫ ሆኖ ቆይቷል ይላል።

“እያወራን ያለነው ወሲባዊ ይዘት ስላላቸው የሕፃናት ምሥሎች ነው፤ እያወራን ያለነው ስለዕፅ ንግድ ነው፤ እያወራን ያለነው ምንም ዓይነት እርምጃ ስላልተወሰደበት ዳርክ ዌብ [የጨለማው በይነ-መረብ] ነው” ይላል ግሬይ።

ዳርክ ዌብ ማለት ልዩ በሆነ ሶፍትዌር እና ዕውቀት ብቻ ሰዎች የሚጎበኙት የኢንተርኔት ዓለም ነው። በአውሮፓውያኑ 2011 ይፋ ከሆነው ሲልክ ሮድ የተባለው የዳርክ ዌብ መገበያያ ጀምሮ በርካታ ድረ-ገፆች ሕጋዊ ያልሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶችን እያገበያዩ ይገኛሉ።

ወንጀለኞች ዳርክ ዌብን የሚመርጡት ማንነታቸውን ስለሚደብቅላቸው ነው። የተጠቃሚዎች አድራሻ ስለማይታወቅ ወንጀለኞችን ነጥሎ መያዝ እጅግ አዳጋች ነው።

ወንጀለኞች ቴሌግራም የተባለውን የማኅበራዊ ሚድያ ትስስር መድረክን የበለጠ እየመረጡት የመጡ ይመስላል።

‘ኢንቴል471’ የተባለው የሳይበር ደኅንነት ተቋም አጥኚዎች እንደሚሉት “ከቴሌግራም በፊት መሰል ድርጊቶች የሚፈፀሙት በዳርክ ዌብ ነበር” ነገር ግን ዝቅተኛ ለሚባሉ ብዙም የሳይበር ዕውቀት ለሌላቸው ወንጀለኞች “ቴሌግራም እጅግ ተመራጭ መድረክ ሆኖላቸዋል።”

የበይነ-መረብ ጠላፊው ቡድን ‘ኪሊን’ ከወራት በፊት የዩናይትድ ኪንግደምን ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ጠልፎ ካሳ ከጠየቀ በኋላ የደም ምርመራ ውጤቶችን ይለጥፍ የነበው በቴሌግራም ገፁ ነበር።

በስፔን እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሴት ተማሪዎችን ሐሰተኛ ፎቶ (ዲፕፌክ) የሚያሠራጨው ቡድን ክፍያ ሳይቀር ይቀበል የነበረው በቴሌግራም አማካይነት ነው።

ከዚህ ቀደም በወጡ ዘገባዎች መሠረት መሰል የወንጀል ድርጊቶች በሌሎች ማኅበራዊ ሚድያዎችም ላይ ተስተውለዋል።

እኔ ከገባሁባቸው የቴሌግራም የወንጀለኞች ቻናሎች መካከል አንዳንዶች ስናፕቻት የተባለው የማኅበራዊ ሚድያ ገፅ ነበራቸው። ዕፅ አዘዋዋሪዎች ኢንስታግራም ላይም ይገኛሉ።ስልክ እና ገንዘብ

ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በሌሎች ማኅበራዊ ሚድያዎች ማስታወቂያ የሚሠሩ ገፆች ተጠቃሚዎች ወደ ቴሌግራም ገፃቸው እንዲመጡ ያበረታታሉ።

ባለፈው ጥር የላትቪያ ፖሊስ የዕፅ መዘዋወሪያ ማዕከል ይሆናሉ ያላቸውን የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችን የሚመረምር አዲስ ክፍል አቋቁሞ ቴሌግራም ትልቁ ስጋት ነው ማለቱ ይታወሳል።

ቴሌግራም እንደሚለው “ኢንዱስትሪው በሚጠይቀው መሠረት” የይዘት ቁጥጥር እያደረገ ነው። ነገር ግን በዚህ ሳምንት እንኳ ከዚህ ጋር የሚፃረር ሕፃናት ላይ የሚደርስ ወሲባዊ ጥቃትን የሚያሳይ ምስል ተመልክተናል።

ባለፈው ረቡዕ ቢቢሲ እንደተመለከተው ቴሌግራም ከፖሊስ እና የእርዳታ ድርጅቶች በቀረበለት ጥያቄ መሠረት እኒህን ምስሎች ቢያወርድም መሰል ምስሎችን እየተከታተለ የማጥፋት ሥራ ግን እየሠራ አይደለም።

ናሽናል ሴንተር ፎር ሚሲንግ ኤንድ ኤክስፕሎይትድ ቺልድረን እንዲሁም ኢንተርኔት ዋች ፋውንዴሽን የሚባሉት ድርጅቶች ዋና ዋና ከሚባሉ የማኅበራዊ ሚድያዎች ጋር በመሥራት የጠፉ ሕፃናትን ይፈልጋሉ እንዲሁም ምስሎችን ያስጠፋሉ። ቴሌግራም ግን የዚህ አባል አይደለም።

የፈረንሳይ አቃቤ ሕግ ቴሌግራም ላይ ካቀረበው ክስ አንዱ ሕፃናት ላይ የሚደርስን ፆታዊ ጥቃት ለመቆጣጠር የበኩሉን አልተወጣም የሚለው ነው።

ቴሌግራም ለቢቢሲ በላከው መግለጫ የሕፃናትን ወሲባዊ ምስሎችን ጨምሮ ሕጋዊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ጥረት እያደረገ ነው። መግለጫው አክሎ ባለፈው ነሐሤ ብቻ 45 ሺህ ቻነሎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ይላል።

የቴሌግራም የፕረስ ኦፊስ ከቢቢሲ ተጨማሪ ጥያቄዎች ቢቀርቡለትም እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ቴሌግራም ላይ የሚቀርበው ክስ የይዘት ቁጥጥር አያደርግም የሚል ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ይዘቶች እንዲጠፉና ተጨማሪ ማስረጃ እንዲያቀርብ ከፖሊስ ለሚቀርብለት ጥያቄ ምላሽ አይሰጥም የሚል ነው።

ሲንደር የተባለው የሶፍትዌር ተቋም አጋር መሥራች የሆኑት ብራያን ፊሽማን “ቴሌግራም ላለፉት አስር ዓመታት የአይኤስኤስ ቁልፍ ማዕከል ነበር። የሕፃናት ወሲባዊ ብዝበዛን ችላ ይላል። ከሕግ አካላት የሚቀርብለትን ጥያቄ አይመልስም። ይህ የይዘት ቁጥጥር ጉዳይ ብቻ አይደለም” ይላሉ።

አንዳንድ ሰዎች የቴሌግራም የግል መረጃ ጥበቃ ፖሊሲ የተጠቃሚዎችን መረጃ ተመልክቶ ለፖሊስ እንዳያጋልጥ ያደርገዋል ሲሉ ይከራከራሉ። እንደ ሲግናል እና ዋትስአፕ ያሉ መልዕክት መለዋወጫዎች መሰል ፖሊሲ አላቸው።ቴሌግራም ለዕጽ ንግድ እና ዝውውር ይውላል

ቴሌግራምም “ሲክሬት ቻት” ለሚጠቀሙ ሰዎች ተመሳሳይ ፖሊሲ አለው። ይህም ማለት “ሲክሬት ቻት” ውስጥ የሚከናወን ማንኛውንም ተግባር ሌላው ቀርቶ ቴሌግራም እንኳን መመልከት አይችልም።

እንዲህም ሆኖ እኔ የተጨመርኩባቸው ሕጋዊ ያልሆኑ ቻነሎች “ሴክሬት ቻት” አልነበሩም። ቴሌግራም እኒህን ይዘቶች ተመልክቶ ለፖሊስ መስጠት ይችላል። ነገር ግን በደንብ እና መመሪያዎቹ ላይ ይህን እንደማያደርግ ቃል ይገባል።

የፈረንሳይ ባለሥልጣናት የዱሮቭን ክስ በተመለከተ በለቀቁት መግለጫ ከፈረንሳይ እና ከቤልጂየም ፖሊሶች “ለሚቀርብ ሕጋዊ ጥያቄ ምላሽ አለመስጠት ይታያል” ይላል።

የጀርመንን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ባለሥልጣናትም ቴሌግራም ከመተግበሪያው ላይ መወገድ ስላለባቸው ይዘቶች ለሚቀርብለት ጥያቄ ምላሽ አይሰጥም የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ።

ምንም እንኳ ቴሌግራም በይዘት ቁጥጥሩ ምክንያት በርካታ ጥያቄዎች ቢቀርቡበትም የመሥራቹ በቁጥጥር ሥር መዋል ደግሞ ሌላ አከራካሪ ጉዳይ ሆኗል።

የዲጂታል መብቶች ተከራካሪው አክሰስ ናው የተሰኘው ቡድን እየሆነ ያለው ነገር እንዳሳሰበው ገልጿል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ቴሌግራምን በተደጋጋሚ መውቀሱን በመግለጫው አሳውቋል።

ነገር ግን “ሰዎች በነፃነትና በሰላማዊ መንገድ ሐሳባቸውን የሚገልፁበትን መድረክ ሠራተኛ በቁጥጥር ሥር ማዋል ሳንሱርን የሚያጠናክር እና የሲቪክ መብትን የሚጥስ ነው” ብሏል።

የኤክስ [የቀድሞው ትዊተር] ባለቤት የሆነው ቢሊየነሩ ኢላን መስክ የዱሮቭን መታሰር ወቅሶ የንግግር ነፃነት ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ብሎታል። ቢሊየነሩ ዱሮቭ በፍጥነት እንዲለቀቅም ጠይቋል።

ቴሌግራም ላይ ያሉ ወንጀለኞችም በአብዛኛው በእንግሊዝኛ እና በሩሲያ ቋንቋ ፍሪዱሮቭ የሚል ምስል እያጋሩ ይገኛሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)