ብሊንከን ሩስያ በዩክሬን ላይ እየፈጸመችው ላለው ጥቃት ቻይና ድጋፍ እንዳታቀርብ አስጠነቀቁ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩስያ በዩክሬን ላይ እየፈጸመችው ላለው ጥቃት እያቀረበች ካለችው ድጋፍ ቻይና እንድትቆጠብ አስጠነቀቁ።

ቻይና ለጥቃቱ የሚሆኑ ቁሶችን እያቀረበች ነው ሲሉ የወነጀሉት ብሊንከን፣ይህንን ካላቆመች አገራቸው እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቀዋል።

ቻይና ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ “በአውሮፓ ደኅንነት ላይ የተጋረጠውን ስጋት እያቀጣጠለች እና እየረዳች” መሆኑን በቤጂንግ በነበራቸው ቆይታ ከባለስልጣናቱ ጋር መነጋገራቸውን ብሊንከን ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አገራቸው በቻይና ላይ እርምጃ እንደምትወስድ ቢናገሩም ምን እንደሆነ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ብሊንከን በቤይጂንግ ቆይታቸው በአንዳንድ ሁኔታዎች መሻሻል መታየቱን ጠቅሰው ለዚህ ዋቢ ያደረጉትን ፌንታኒል የተሰኘው አደንዛዥ እፅ ወደ አሜሪካ እንዳይደርስ ለማስቆም ባለስልጣናቱ ያደረጉትን ጥረት አወድሰዋል።

በመላው አሜሪካ የሕዝብ ጤና ቀውስ እየፈጠረ እንደሆነ በዋይት ሃውስ የተነገረለት ፌንታኒል አደንዛዥ እፅ ዋነኛ ምንጩም ቻይና መሆኗ ይነገራል።

ብሊንከን በተጨማሪ ቻይና ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት በመጠቀም ከእስራኤል ጋር ያለው ጦርነት የበለጠ እንዳይሰፋ በማድረግም ረገድ በመካከለኛው ምስራቅ “ገንቢ ሚና” መጫወት እንደምትችል አጽንዖት ሰጥተዋል።

በአስር ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው ይህ ጉብኝታቸው በሁለቱ ተቀናቃኝ ኃያል አገራት መካከል ያለውን ውጥረት በማርገብ ወደ ዲፕሎማሲ እና ውይይት ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት አካል ነው ተብሏል።

በሁለቱ አገራት መካከል ዋነኛ ውጥረት መነሻ ሆኖ የቆየው ቻይና ታይዋንን እንደ አንድ ግዛቷ መመልከቷ ሲሆን በቅርቡ አሜሪካ ለታይዋን ካካሄደችው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በአምስት የምዕራባውያን የመከላከያ ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል ቻይና ማስታወቋ ይታወሳል።

እንዲሁም ባለፈው ዓመት አሜሪካ ቻይና የላከችው የስለላ ፊኛ ነው በሚል መትታ መጣሏን ተከትሎ የአገራቱ ውጥረት ተጋግሎ ነበር።

በቅርብ ቀናት ውስጥ ደግሞ ባለቤትነቱ የቻይና የሆነው የቪዲዮ መተግበሪያ ቲክቶክ በአሜሪካ ያለው ድርሻ እንዲሸጥ ወይም እንዲታገድ የሚያስገድድ ሕግ ፓርላማው አውጥቷል።

ብሊንከን ከቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር በነበራቸው ውይይት የቲክቶክ ጉዳይ እንዳልተነሳ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ጂንፒንግ በበኩላቸው በኅዳር ወር ከአሜሪካ አቻቸው ጆ ባይደን ጋር ከተገናኙ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል “አንዳንድ አዎንታዊ መሻሻል አሳይተዋል” ብለዋል።

አሜሪካ ለቻይና ዕድገት አዎንታዊ አመለካከት ማሳየት ከቻለች የሁለቱ አገራት ግንኙነት “ሊረጋጋ፣ ሊሻሻል እና ወደፊት ሊራመዱ ይችላሉ” ያሉት ፕሬዚዳንት ጂንፒንግ “ተፎካካሪዎች ሳይሆኑ አጋር መሆን አለባቸው” ሲሉም አክለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ( ቢቢሲ ዜና )