በጉራጌ ዞን “ከፋኖ ጋር በተያያዘ” ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸው ተነገረ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ከሰኔ 2016 ዓ.ም. ወዲህ ከ100 በላይ የአማራ ብሔር ተወላጆች “በሽብር” ተጠርጥረው ሲታሰሩ ስጋት ያደረባቸው ነዋሪዎች ደግሞ አካባቢውን ለቀው መሸሸታቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

በዞኑ አበሽጌ ወረዳ ከሰኔ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ‘ፋኖ ናችሁ፤ የፋኖ ክንፍ ናችሁ፤ ፋኖን በገንዘብ ትደግፋላችሁ’ በሚል የፀጥታ ኃይሎች ድብደባ እና እንግልትን ጨምሮ “ማንነትን የለየ” እስር እየፈጸሙ መሆናቸውን በመግለጽ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአካባቢው የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በቁጥጥር ስር የሚገኙት ነዋሪዎች “በመሳሪያ ዝውውር እና እገታ” ወንጀሎች ተጠርጥረው የተያዙ ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አብሸጌ ወረዳው ካሉት 30 ቀበሌዎች እና ማዘጋጃዎች 16ቱ በአብዛኛው የአማራ ብሔር ወላጆች እንደሚኖሩባቸው የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ግን ከፋኖ ጋር በተያያዙ ክሶች ምክንያት “እየተሳደድን ነው” ይላሉ።

በተለይም ከዞኑ እና ከወረዳው መቀመጫ ወልቂጤ ከተማ በ42 ኪ.ሜ በምትርቀው ዳርጌ እና 30 ኪ.ሜ ገደማ በምትርቀው ዋልጋ የቀበሌ ከተሞች ላይ ‘የአማራ ብሄር ተወላጆች’ ማንነታቸው ተለይቶ እንደታሰሩ የታሳሪ ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“ከባለሀብት እስከ ቀን ሠራተኛ፤ ከፖለቲከኛ እስከ ወጣት፤ ከባጃጅ ሹፌር እስከ ሞተረኛ ድረስ” የእስሩ ሰለባዎች እንደሆኑ አንድ አካባቢውን ለቀው የወጡ ነዋሪ ተናግረዋል።

“እነሱ ፋኖ የሚሉት አማራ ሆኖ መሳሪያ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን ሰው በሙሉ ነው” ሲሉ እስሩ ማንነት ተኮር ነው ሲሉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።

በአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ እስር በአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ “አልፎ አልፎ” ነበር የሚሉት ነዋሪዎች፤ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ወዲህ ግን “ትጥቅ ፍቱ በሚል” በስፋት እስር እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በግብርና ሥራ ላይ ኑሯቸውን እንደመሠረቱ የተናገሩ አንድ ነዋሪ በአካባቢው “በሸኔ” ታጣቂዎች ስጋት ምክንያት ማኅበረሰቡ በመንግሥት ይሁንታ እና “ሕጋዊ ፈቃድ” መሳሪያ እንደታጠቀ ጠቁመው፤ “እኛ እንጠብቃችኋለን” በሚል መሳሪያ እንዲፈቱ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ለነዋሪው በስብሰባ ላይ የመሳሪያ ማስረከቢያ ቀነ ገደብ ቢሰጥም ቀኑ ሳይደርስ ግን ማኅበረሰቡን “ፋኖ ነው” የሚል ስም በመስጠት እስር እና ወከባ መጀመሩን ገልጸዋል።

“የመጨረሻው ቀን ሳይደርስ ማሰር ተጀመረ። እነሱ [መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች] በሌሊት እየገቡ ማሰር ጀመሩ። በአንድ ቀን አምስት፤ ስድስት ሰው መያዝ ተጀመረ። ከዚያ ግማሹ መሸሽ ጀመረ። እኔ መሳሪያ የለኝም ብሎ የተዘናጋውንም በመያዝ በዚያው ቀጠለ” ሲሉ ስለ እስሩ ተናግረዋል።

ቤተሰባቸው የታሰረባቸው አንድ ነዋሪ “ሊጠብቁን ነው ያልናቸው የፀጥታ ኃይሎች በደል ፈጽመውብናል” ይላሉ።

“በሌሊት ወደ ቤት እየገቡ መደብደብ፣ ማፈን እና ብዙ ነገር ማድረግ ጀመሩ። ‘ይሄን ያህል መሳሪያ አምጡ፤ ይሄ አላችሁ ይሄን አምጡ [አሉ]’። [መሳሪያ] ያለው ሲሰጥ ወስደው ያስራሉ። በወቅቱ [ሌሊት] እየገቡ ሲደበድቡ የሕግ አካል ያልመሰላቸው ሰዎች የጠፉ አሉ” ሲሉ ስለነበረው ሁኔታ ተናግረዋል።

“በሌሊት ገብተው እየደበደቡ ‘አንተ ፋኖ፤ ፋኖን ትደግፋለህ’” እያሉ እንዳሰሯቸው የሚናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ 16 እናቶችም እስከ ልጆቻቸው ከሁለት ሳምንታት በላይ ታስረዋል ብለዋል።

“ባለቤትሽን አምጪ፤ ወንድምሽን አምጪ፤ እህትሽን አምጪ በሚል ነፍሰ ጡር፣ ህጻናት የያዙ [ሴቶች] ታስረው ነበር” ሲሉ እስሩ የሁሉንም ቤት ያንኳኳ እንደነበር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መስከረም 15/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአካባቢው 11 ሴቶች “በባለቤቶቻቸው ምትክ” ከ20 ቀናት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እንደታሰሩ አስታውቆ ነበር።

ሰዎቹ ሲያዙም ሆነ ከታሰሩ በኋላ “ከባድ ድብደባ” እንደተፈጸመባቸው የሚናገሩት ነዋሪዎች፤ በዚህም የጤና እክል የገጠማቸውም አሉ ብለዋል።

በእስር ላይ የሚገኙ ቤተሰባቸው “ልዩ ኃይል” ብለው በጠሯቸው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአደባባይ እንደተደበደቡ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ በድብደባው “ለሽንት ኢንፌክሽን” ህመም እንደተጋለጡ ተናግረዋል።

“በባለቤቱ እና በልጆቹ ፊት፤ በኖረበት ማኅበረሰብ ፊት ገበያ ላይ ለአምስት ለስድስት እየተረባረቡ ነው የቀጠቀጡት” ሲሉ አንድ ነዋሪ ስለ ድብደባው ተናግረዋል።

“እስር ቤት ውስጥ ተደብድቦ ዓይኑ የጠፋ፣ እግራቸው እጃቸው የሰለሉ ሰዎች አሉ” ሲሉ አንድ ነዋሪ የእስሩ ሕጋዊነትን እንደሚጠራጠሩ ጠቁመው፤ “ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ነው” ይላሉ።

መሳሪያ የሌላቸው ሰዎች መሳሪያችሁን አምጡ እየተባሉ ወከባ ሲደርስባቸው “ላለመታሰር” ከ100 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር እየከፈሉ ነውም ብለዋል።

“ማንነትን የለየው” እንግልት ምክንያቱ አካባቢውን በቅርብ ኪሎ ሜትሮች በሚያዋስነው የኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ሰኔ 8/2016 ዓ.ም. በሙሽሮች ላይ ተፈጽሟል የተባለው ጥቃት ነው ብለዋል።

“እዚያ [ኖኖ ወረዳ] ሄዳችሁ አግዛችኋል፤ ጎረቤት ክልል ገብታችሁ ሁከት ትፈጥራላችሁ፤ እዚህ የተደራጀ ፋኖ አለ፤ እሱን ትደግፋላችሁ የሚል ነው” ሲሉ አንድ ነዋሪ የእስሩ ዋነኛ ነው ምክንያት ያሉት ተናግረዋል።

ይህንንም ኢሰመኮ መስከረም አጋማሽ ላይ ባወጣው ሪፖርት የጠቆመ ሲሆን፤ ከወረዳው በማዕከላዊ አትዮጵያ እና ኦሮሚያ ክልሎች ባሉ ግጭቶች ተሳትፈዋል፤ ድጋፍ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ 71 ሰዎች ከሐምሌ 28/2016 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።

የመንግሥት ኃይሎች “በሰዎች ጥቆማ” እስሩን ስለመፈጸማቸው የተናገሩት ነዋሪዎች በወልቂጤ (አይሪሽ አዳራሽ) እና ዋልጋ ‘የልዩ ኃይል ካምፕ’ ከ100 እስከ 200 እንደሚደርሱ ሰዎች መታሰራቸውን ተናግረዋል።

የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ አንድ ነዋሪ የታሰሩ ሰዎች ከ140 በላይ (በወልቂጤ 90 ሰዎች እና ዋልጋ ከ50 በላይ ሰዎች) እንደሚሆኑ ጠቁመው እስሩ አሁንም እንዳላቆመ ገልጸዋል።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 13 እና 14/2017 ዓ.ም. ሁዳድ አንድ እና ከታ ከሚባሉ ቀበሌዎች 30 ሚደርሱ ሰዎች መታሰራቸውን ጠቁመው በአጠቃላይ በወረዳው የታሰሩ ሰዎች ቁጥር ከ200 እንደሚሻገር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአበሽጌ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ መቶ አለቃ ፀጋዬ አምድሳ “ጽንፈኛ” ያሏቸውን ኃይሎች “በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ በፋኖ አደረጃጀት እና በእገታ” ወንጀሎች በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ኃላፊው በአካባቢው እየተካሄደ ስላለው እስርም ሆነ ለቀረቡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምላሽ እንዲሰጡ ቢቢሲ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካም።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው አስተዳደር “በሕብረተሰቡ ጥቆማ ጽንፈኛ” የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረል።

በወልቂጤ የታሰሩት 90 ሰዎች ከ22 ቀናት በኋላ ወልቂጤ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ ፖሊስ በኦሮሚያው ጥቃት “በሽብር” ጠርጥሮ እንዳሰራቸው መናገሩን አንድ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ የቢቢሲ ምንጭ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ለሦስት ወራት ያህል ታስረው እስካሁን የጊዜ ቀጠሮ (ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ) ላይ መሆናቸውን ቢቢሲ የተረዳ ሲሆን፤ ፖሊስ የቴክኒክ ማስረጃ (የስልክ ልውውጥ) እንደሚያቀርብ ለፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ቢናገርም እስካሁን አለማቅረቡ ታውቋል።

ፖሊስ እስካሁን ታሳሪዎችን ለመጠርጠር የሚያበቃ ማስረጃ ይዞ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሚያሳይ ማስረጃም ቢሆን አለማቅረቡን የተናገሩት ምንጩ፤ ‘አካባቢው ላይ ባለው የፀጥታ ችግር ጠርጥረናቸዋል’ የሚል ጥቅል ውንጀላ ብቻ ማቅረቡን ተናግረዋል።

ነዋሪዎች እና ቤተሰቦች ግን በተጠረጠሩበት ወንጀል ያልተሳተፉ “ገበሬዎች” ናቸው ሲሉ ክሱን ውድቅ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ‘ተፈላጊ’ የተባሉ ሰዎች ቤት እና ንብረት እየታሸገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አንድ ጉዳዩን በቅርበት አውቃለሁ ያሉ የአካባቢው ምንጭ እስሩ እና ወከባው “ማኅበረሰቡ በተለየ መንገድ እንዲፈራ፣ እንዲጠነቀቅ፣ አካባቢው የሚያሰጋው እንደሆነ ለማመልከት ነው” ብለው ያምናሉ።

ሌላ ነዋሪ “. . . ሥራችንን ለማበላሸት ነው። አሁን የሥራ ወቅት ነው፤ የአዝመራ ወቅት ነው። [ግን] ሥራ አልተሠራም። ያደረጉት ነገር ለማዳከም፤ ለማበሳጨት ነው” ሲሉ ጫናውን ይገልጻሉ።

“በአብዛኛው ገበሬዎች ናቸው” ሲሉ የታሰሩ ሰዎችን ማንነት የተናገሩ አንድ ነዋሪው፤ በዓመት ከ15 ሺ እስከ 20 ሺ ኩንታል የሚያመርቱ “ኢንቨስተሮች” ናቸው ብለዋል።

“ባዶ እጁን ሁሉ የወጣ አለ። የነበራቸውን ነገር ለማዳበሪያም ለምንም ማሳቸው ላይ አውጥተውት ነበር። አሁንም ቦታው ላይ ሰላም ስለሌለ፤ ሰውም እየተሳደደ ስለሆነ ተመልሶ ለመግባት አስጊ ስለሆነ ሁለት አባወራ፤ ሦስት አባወራ አንድ ቤት እየኖረ ነው” ሲሉ አንድ ሸሽተው የወጡ ነዋሪ ያሉበትን ሁኔታ ተናግረዋል።

“አሁን በቆሎ ተነስቶ ሽምብራ የሚዘራበት [ወቅት] ነበር” ያሉት ነዋሪው፤ “ከመሞት ይሻላል” በሚል ሀብት እና ንብረታቸውን ጥለው እንደሸሹ ገልጸዋል።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ “ማንኛውም ቤት የተዘጋ ነው የምታገኝው፤ አብዛኛው መንግሥት የፀጥታ መዋቅር ብቅ ሲል እየደነበረ ጫካ እገባ ነው ያለው” ብለዋል።

ከኅዳር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ጉራጌ ዞን ከክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ በኮማንድ ፖስት እየተመራ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ የተነሱ ጉዳዮች ላይ ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጡ ወደ ሚመለከታቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር ለቀናት በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካም።

*ለዚህ ዘገባ ቢቢሲ አምስት ቤተሰቦቻቸው የታሰሩባቸው እና በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችን ያነጋገረ ሲሆን፣ ሁሉም ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈቀዱም።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)