በደቡብ አፍሪካ አንድ ህንጻ ተደርምሶ በርካቶች መውጫ ማጣታቸው ተነገረ

በደቡብ አፍሪካ በግንባታ ላይ ያለ አንድ ህንጻ ተደርምሶ አራት ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ በርካቶች መውጫ ማጣታቸው ተነገረ።

በህንጻው ውስጥ መውጫ ያጡ 51 ሰዎችን ህይወት ለመታደግ የነፍስ አድን ርብርብ መጀመሩም ተገልጿል።

በዌስተርን ኬፕ ግዛት በምትገኘው ጆርጅ ከተማ በደረሰው የህንጻ መደርመስ አደጋ 24 ግለሰቦችን ከፍርስራሹ በማውጣት ወደ ሆስፒታል መውሰድ ተችሏል።

ህንጻው ሰኞ እለት በተደረመሰበት ወቅት 75 ሰራተኞች ነበሩ።

በባህርዳርቻዋ ከተማ የደረሰውን ክስተት መንስኤ ለማጣራት ምርመራ ተጀምሯል ተብሏል።

ህንጻው በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 8 ሰዓት ገደማ እንደተደረመሰ የዌስተርን ኬፕ አስተዳዳሪ አላን ዊንዴ ገልጸዋል።

ከኬፕታውን በስተምስራቅ 450 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ከተማ ውስጥ ከደረሰው የመደርመስ አደጋ ሰዎችን በህይወት ለመታደግ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ወደ ስፍራው ሲጣደፉ ታይተዋል።

ከፍራስራሾቹ ውስጥ ማውጣት ተችሎ ከነበሩት 22 ሰዎች መካከል ሁለቱ ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል። በኋላም ሌሎች ሁለት በደረሰባቸው ጉዳቶች ምክንያት ህይወታቸው እንዳለፈ ተዘግቧል።

“በዚህ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች መጽናናትን እየተመኘን እየተጠባበቁ ላሉ ቤተሰቦች በሃሳብ ከናንተ ጋር ነን” ሲሉ የከተማዋ ከንቲባ አንድ ቫን ዋይክ ተናግረዋል።

ከ100 የሚበልጡ የነፍስ አድን ሰራተኞች ከአነፍናፊ ውሾች ጋር ተሰማርተው ከህንጻው ፍርስራሽ ሰዎችን ለማውጣት ሌሊቱን ሙሉ ሲሰሩ ነበር ተብሏል።

ይህንን ስራ ለማገዝ ዘመናዊ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ተነግሯል።

በፍርስራሹ ውስጥ ተቀብረው ከሚገኙ ሰዎች ውስጥ ከተወሰኑት ጋር ንግግር ማድረግ እንደተቻለ ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

ህንጻው ሙሉ በሙሉ ተደርምሶ ፍርስራሾች ብቻ የሚታዩበት ፎቶዎች ወጥተዋል።

“አንድ ግለሰብ በህንጻው ላይ ሲሰራ አየሁ ከዚያም ህንጻው ሙሉ በሙሉ ሲደረመስ አየሁ። በጣም ደንግጫለሁ። በጣም ያሳዝናል “ ሲሉ ቴሬሳ ጄይ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለሮይተርስ መናገራቸው ተዘግቧል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )