በዓለማችን እያጋጠመ ላለው የውልደት መጠን መቀነስ ወንዶች ተጠያቂ ናቸው?

በአሁኑ ወቅት በበርካታ የዓለም አገራት ውስጥ ልጆችን የመውለድ መጠን እየቀነሰ በመምጣቱ ሰው ዘሩን የመተካት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

በምድራችን ከፍተኛው የሕዝብ ብዛት ባለቤት ሆና ለዘመናት የቆየችው ቻይና በታሪኳ አይታው በማታውቀው ሁኔታ የዜጎቿ ዘር የመተካት ሒደቷ እያሽቆለቆለ ነው።

በላቲን አሜሪካ ደግሞ በርካታ ሀገራት የውልደት መጠናቸው እየቀነሰ ይገኛል።

በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካም የውልደት መጠን ከተጠበቀው በላይ እየቀነሰ ነው። ይህ ማለት ሰዎች የሚወልዱትን ልጅ ቁጥር እየቀነሱ ነው ማለት ነው። በአንዳንድ ሀገራት የውልደት መጠኑ ወደ ዜሮ እየወረደ ይገኛል።

ኢሳቤል ኮሎምቢያ ውስጥ ኑንሳ ማድሬስ የተባለ ድርጅት አላት። ልጅ መውለድ አልፈልግም በሚል ከአጋሯ ጋር በመጣላቷ ምክንያት ነው ይህን ድርጅት ያቋቋመችው።

ለኢሳቤል ልጅ አለመውለድ ምርጫ ነው። ለሌሎች ደግሞ ተፈጥሯዊ አጋጣሚ ነው። አንዳንዶች በምርጫቸው ልጅ አንወልድም ይላሉ። ሳይንቲስቶችን ይህን ክስተት “ሶሻል ኢንፈርቲሊቲ” (ማኅበራዊ መካንነት) ይሉታል።

በቅርቡ የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው ወንዶች ቢመርጡትም ባይመርጡትም ከሴቶች በበለጠ ለውልደት ማሽቆልቆል ምክንያት እየሆኑ ነው። ለዚህ ደግሞ በተለይ ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወንዶች ምክንያት ናቸው ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2021 በኖርዌይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነገር ግን ልጅ የሌላቸው ወንዶች 72 በመቶ ሲሆኑ፣ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ግን 11 በመቶ ናቸው።

ሮቢን ሀድሊ በሰለሳዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለ ነው አባት የመሆን ፍላጎቱ እጅግ የበረታው። ዩኒቨርሲቲ ባይገባም በሰሜናዊ እንግሊዝ በአንድ ዩኒቨርሲቲ በፎቶግራፈርነት ሥራ ተቀጥሮ ይሠራ ነበር።

በ20ዎቹ ዕድሜው አግብቶ ከሚስቱ ጋር ልጅ ለማፍራት ብዙ ቢሞክሩም አልተሳካለትም። ጥንዶቹ ባለመስማማታቸው ተለያዩ።

በዕዳ የገነባውን ቤት ከፍሎ ባለመጨረሱ እንደፈቀደው እየወጣ መዝናናት አልቻለም። ጓደኛ የማፍራት አቅሙም እንዲሁ ተዳከመ። ጓደኞቹ እና የሥራ አጋሮቹ ልጆች ሲያፈሩ እሱን ግን ብቻውን ቀረ።

“ልደት ስጠራ እና አራስ ለመጠየቅ ስሄድ ነው የበለጠ የሚሰማኝ። ብዙውን ጊዜ ሐዘን ይሰማኝ ነበር” ይላል።

ከዚህ የሕይወቱ ልምድ በመነሳት ልጅ ስለሌላቸው ወንዶች መፅሐፍ ፅፏል። ምጣኔ ሀብት፣ ተፈጥሮ፣ የሁኔታዎች አለመመቻቸት እና የፍቅር ጓደኛ መረጣ የተወሰኑ ምክንያቶች መሆናቸውን እያጣቀሰ ያስረዳል።

ትምህርት ላይ ያለ ሕፃን

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

በፈቃደኝነት ልጅ አልባ የሚሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ልጅ ለመውለድ የሚያስችል አቅም ማጣት እና ትክክለኛ የፍቅር ጓደኛ አለማግኘት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ነገር ግን ዋነኛው ምክንያት ወዲህ ነው ይላሉ የፊንላንድ የሕዝብ ጥናት ተቋም ባለሙያ የሆኑት አና ሮትኪርች። አና ላለፉት 20 ዓመታት በፊንላንድ እና በአውሮፓ የውልደት መጠንን ሲያጠኑ ቆይተዋል።

ከእስያ ሀገራት በመቀጠል ፊንላንድ በርካታ ልጅ አልባ ልጆች ያሉባት ሀገር ናት። ነገር ግን በ90ዎቹ እና 2 ሺዎቹ የውልደት ማሽቆልቆልን በመግታት እና ለሕፃናት ምቹ የሆነች ሀገር በመባል ስትደነቅ ነበር።

በወሊድ ወቅት ለወላጆች የሚሰጠው እረፍት ከፍተኛ ነው፤ ሕፃናትን መንከባከብ ቀላል ነው፤ ወንዶች እና ሴቶች እኩል የቤት ውስጥ ሥራ ይሠራሉ።

ነገር ግን ከአውሮፓውያኑ 2010 በኋላ የወሊድ መጠን በአንድ ሦስተኛ አሽቆልቁሏል።

ፕሮፌሰር አና እንደሚሉት በአንድ ወቅት ልክ እንደ ትዳር ልጅ መውለድ ትልቅ የሕይወት እመርታ ነበር። አሁን ግን ይህ ባሕል እየቀዘቀዘ መጥቷል።

“በሁሉም የኑሮ ደረጃ ያሉ ሰዎች ሕፃናት ማሳደግ ማለት እርግጠኛ ባለሆኑበት ሕይወት ተጨማሪ ኃላፊነት ማምጣት እንደሆነ ያስቡታል” ይላሉ።

በፊንላንድ ሀብታም የሚባሉ ሴቶች ሳይፈቅዱ ልጅ አልባ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ፕሮፌሰሯ ያስረዳሉ። በሌላ በኩል ገንዘብ የሌላቸው ወንዶች ልጅ አልባ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው።

በቀድሞው ጊዜ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ናቸው ቀድሞው ቤተሰብ በመመሥረት ልጅ የሚያፈሩት።

ሴቶች የትዳር አጋር ሲመርጡ ከራሳቸው ገቢ ጋር የሚቀራረብ ወንድ ስለሚፈልጉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወንዶች በገቢ ምክንያት ልጅ አልባ ይሆናሉ።

ሮቢን ሀድሊ 40ኛ ዕድሜውን ሊደፍን ሲቃረብ ነው የአሁኑ ሚስቱን የተዋወቃት። ሚስቱ አበረታትታው ትምህርቱን ገፍቶበት አሁን የዶክትሬት ድግሪውን ጨብጧል።

ልጅ ለመውለድ በወሰኑበት ወቅት ዕድሜያቸው በ40ዎቹ ውስጥ ነበር።

በዓለማችን ከሚገኙ ሀገራት 70 በመቶ በሚሆኑት ሴቶች ከወንዶች የተሻለ በትምህርት እየላቁ መጥተዋል ይላል አንድ ጥናት። በተለይ በአውሮፓ የዩኒቨርሲቲ ድግሪ የሌላቸው ወንዶች ልጅ የማፍራት ዕድላቸው ዝቅ ያለ ነው።

በርካታ ሀገራት ወንዶች በውልደት መጠን ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ በተመለከተ ብዙ መረጃ የላቸውም። ምክንያት የወሊድ መጠን የሚመዘገበው ከሴቶች ነውና።

ነገር ግን በርካታ ሰዎች ወንዶች የውልደት ምጣኔ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ መጠናት አለበት ይላሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)