በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል ለመፍጠር ሞክረዋል የተባሉት ጳጳስ ተወግዘው ተለዩ…..
ጣሊያናዊው ሊቀ ጳጳስ እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ጠንካራ ተቺ የሆኑት ካርሎ ማሪያ ቪጋኖ በቫቲካን ተወግዘው መለየታቸውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስታወቀች።
ከሊቀ ጳጳሱ ጋር ለዓመታት የዘለቀ ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ ገብተው የቆዩት ካርሎ ማሪያ ቪጋኖ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ክፍፍልን በመፍጠር ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸውን ነው ውግዘት የገጠማቸው።
የ83 ዓመቱ አክራሪ ወግ አጥባቂ የሆኑት ጳጳስ ከዚህ ቀደም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራኒሲስን በኑፋቄ ከመክሰሳቸው በተጨማሪ በስደተኞች፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ላይ ያላቸውን አቋም በመተቸት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ጠይቀው ነበር።
ሊቀ ጳጳስ ቪጋኖ ከአውሮፓውያኑ 2011 እስከ 2016 በዋሽንግተን የጳጳሱ መልዕክተኛ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ የቤተክርስቲያኗ ቀደምት አባት ነበሩ።
ሊቀ ጳጳስ ቪጋኖ በ2018 (እአአ) ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በአሜሪካው ካርዲናል ስለተፈጸመው ጾታዊ ጥቃት እንደሚያውቁ እና ምንም እርምጃ እንዳልወሰዱ በመግለጽ ከከሰሱ በኋላ ተደብቀው ነበር። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ግን ያቀረቡትን ክስ ውድቅ አድርጋዋለች።
ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሊቀ ጳጳስ ቪጋኖ ከአሜሪካ የሴራ ንድፈ ሃሳብ አራማጆች ጋር በመሆን በስፋት የሚታወቁትን የሴራ ጭብጦች ሲያነሱ ቆይተዋል።
በዚህም የኮቪድ ክትባቶችን በመተቸት እና በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች ቡድኖች አማካይነት ይካሄዳል የሚባለውን “ሉላዊነት” እንዲሁም “ፀረ-ክርስቲያን” የሆነ ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው የሚለውን ሃሳብ ሲያራምዱ ነበር ተብሏል።
አርብ ዕለት ከቫቲካን የጳጳሱ ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ እንደተባለው ሊቀ ጳጳስ ቪጋኖ፣ ለፖፕ ፍራንሲስ ለመታዘዝ ፈቃደኛ አለመሆናቸው በይፋ የሚናገሯቸው ነገሮች ምስክር ናቸው ብሏል።
ከቫቲካን የወጣው መግለጫ “ብጹዕነታቸው ሊቀ ጳጳስ ካርሎ ማሪያ ቪጋኖ የቤተክርስቲያኗ ሕግ ጥሰው ክፍፍልን በመፍጠር ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል” በማለት ጳጳሱ ተወግዘው ከቤተከርስቲያኒቱ መለየታቸውን አመልክቷል።
ውሳኔው በኢሜይል የተገለጸላቸው ጳጳሱም በቫቲካን የተላለፈባቸውን ውሳኔ በሚመለከት በኤክስ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ “ለተከሰስኩበት ጥፋት የተጠቀሰው ጉዳይ አሁን ተመዝግቧል፤ ይህም እኔ ያልኩት ሙሉ በሙሉ የካቶሊክ እምነትን አረጋግጧል” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ቪጋኖ ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ክፍፍልን በመፍጠር እና የፖፕ ፍራንሲስን ሕጋዊነት ባለመቀበል የተከሰሱ ሲሆን፣ በወቅቱም በኤክስ ላይ በሰጡት ምላሽ የቀረበባቸውን ክስ “እንደ ክብር” እንደሚመለከቱት አሳውቀው ነበር።
አክለውም አርጀንቲናዊውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስን የቀደመ ስም በመጠቀም “የጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮን ቅሌቶች፣ ስህተቶች እና ኑፋቄዎች እምቢ፣ አልቀበልም በማለት አውግዣለሁ” ብለዋል።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ላይ ባላቸው አቋም፣ ስለስደተኞች መብት መከበር በሚያራምዱት አመለካከት እና የካፒታሊዝምን ከመጠን ያለፈ ድርጊቶችን ከማውገዛቸው ጋር በተያያዘ ከባህላዊ የካቶሊክ መሪዎች ጋር ተቃርነዋል።
ባለፈው ዓመት ሌላኛው እጅግ ወግ አጥባቂ የፖፕ ፍራንሲስ ተቺ የሆኑት የቴክሳሱ ጳጳስ ጆሴፍ ኢ ስትሪክላንድ ላይ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ከመንበራቸው ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የማባረር ውሳኔ አሳልፈውባቸው እንደነበር ይታወሳል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ (ቢቢሲ)