በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሴቶችን ወደ አመራርነት የማምጣት ሃሳብ ተቃውሞ ገጠመው
አንድ ወር የፈጀው የቫቲካን ጉባኤ ሴቶች በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይበልጥ የመሪነት ሚና እንዲኖራቸው ጥሪ በማቅረብ ተጠናቀቀ።
ጉባኤው አንዳንድ ተራማጆች እንደጠበቁት ሴቶችን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ካህን ሆነው እንዲሾሙ ግን ጥሪ ሳያቀርብ ቀርቷል።
ሲኖዶሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የእያንዳንዱን ካቶሊካዊ አመለካከትን ለመለካት ያለመ የአራት ዓመታት ምክክሩን ያበቃ ሲሆን፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በተለምዶ የጳጳሳት ጉባኤ የሚባለውን ለአንዳንድ ምእመናን ክፍት በማድረግ ከ368 ድምጽ ሰጪዎች ውስጥ ወደ 60 የሚጠጉ ሴቶችን አካተዋል።
ሁሉም የሲኖዶሱ አባላት በእያንዳንዱ 151 የውሳኔ ሃሳቦች ላይ ድምጽ ሰጥተዋል።
ምንም እንኳን ሁሉም የውሳኔ ሃሳቦች የሚፈለገው ሁለት ሦስተኛ ድምጽ በማግኘት ያለፉ ቢሆንም፣ ወንድ ቀሳውስት ባላት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሴቶች የበለጠ የመሪነት ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ የቀረበው ሐሳብ ግን ከፍተኛ “አይሆንም” የሚል ድምጽ ተሰጥቶታል።
በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ ሴቶች ትልቅ ሚና እንዲኖራቸው የሚጠይቁ ተሟጋቾች ሲኖዶሱ ሴቶች ዲያቆን በመሆን እንዲያገለግሉ ሊወሰን ይችላል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። ሲኖዶሱ ግን በዚህ በኩል ወደፊት አልተራመደም።
በሰነዱ መጨረሻ ላይ ግን “ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመሪነት ሚና እንዳይጫወቱ የሚያግድ ምንም ምክንያት ወይም እንቅፋት የለም” ብሏል።
በአሁኑ ጊዜ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወንዶች ብቻ ዲያቆን እንዲሆኑ ትፈቅዳለች። ዲያቆናት ጥምቀትን፣ ሰርግ እና የቀብር ሥነ ሥርዓትን እንዲያስፈጽሙ ቢሾሙም እንደ ካህናት ግን ቅዳሴ እንዲመሩ አይፈቀድም።
ምንም እንኳን የተሐድሶ ቡድኖች ቤተክርስቲያኗ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን በተሻለ መንገድ ትቀበላለች ብለው ተስፋ ሰንቀው ነበረ ቢሆንም፣ ሰነዱ ግን ስለጉዳዩ ሳያነሳ “በጋብቻ ሁኔታቸው፣ ማንነታቸው” የተነሳ “ተገለሉ” በሚል ማጣቀሻ ብቻ አልፎታል።
የተመሳሳይ ፆታ ማኅበረሰብን የሚያገለግሉት እና የሲኖዶስ አባል የነበሩት ታዋቂው አሜሪካዊው የጀስዊት ቄስ ሬቨረንድ ጀምስ ማርቲን አዲሱ ሰነድ ስለጉዳዩ አለማንሳቱ “ምንም የሚያስገርም አይደለም” ብለዋል።
በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ተሐድሶ እንዲደረግ ፈላጊዎች በውሳኔው ቅር ሊላቸው ቢችልም፤ አንዳንድ ወግ አጥባቂዎች ደግሞ ከመጀመሪያው ጀምሮ በጠቅላላ ጉባኤው ደስተኞች አልነበሩም።
ይህ ትልቅ እርምጃ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱም የመጨረሻውን ሰነድ ለ1.4 ቢሊዮን የካቶሊክ እምነት ተከታዮች “ስጦታ ነው” ብለው ጠርተውታል። ብዙ ወግ አጥባቂዎች ግን ይህ የምክክር ሂደት ለብዙኃን መክፈቱን ተቃውመዋል።
የቤተክርስቲያኗን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ የሚገባቸው ወጣት ካቶሊኮች ጭምር እንጂ ካርዲናሎች እና ጳጳሳት ብቻ ሊሆኑ አይገባም ከሚሉት ፖፕ ፍራንሲስ አመለካከት ጋር የሚስማማ ነው። ወግ አጥባቂዎች ቅሬታ ከሚያቀርቡባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)