በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪውን ጨምሮ በርካታ ሠዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት ንጉሤ ኮሩን ጨምሮ ከ 45 ሰዎች በላይ የሚሆኑ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አርብ ጥቅምት 22/ 2017 ዓ.ም. መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ኦሮምኛ ገለፁ።
ለደህንነታቸው ሲባል ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ ኦሮምኛ እንደተናገሩት የወረዳው አስተዳዳሪ በታጣቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ ከሞቱት ሰዎች መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት በበኩሉ፣ የወረዳ አስተዳዳሪውን ህልፈተ ህይወት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ ግድያውን አረጋግጦ መንግሥት ሸኔ እያለ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መፈጸሙን ገልጿል።
አርብ ማለዳ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መጋጨታቸውን የተናገሩት ነዋሪው፣ የወረዳው አስተዳዳሪ እንዲሁም በርካታ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታጣቂ ቡድኑ በስፋት ወደሚንቀሳቀስበት አካባቢ ትናንት ማለዳ መንቀሳቀሳቸውን አስረድተዋል።
ቡድኑ በስፋት ወደሚንቀሳቀስበት ካራ ተብሎ ወደ ሚጠራው ስፍራ ያቀኑ የመንግሥት ኃላፊዎች እና ታጣቂዎች በተከፈተባቸው ድንገተኛ ጥቃት የወረዳ አስተዳዳሪውን ጨምሮ ከ45 ሰዎች በላይ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ የወረዳው የሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊውን ጨምሮ በርካቶች ደግሞ ቆስለው ወደ ሙከጡሪ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የዐይን እማኞች ጨምረው ለቢቢሲ ኦሮምኛ ተናግረዋል።
የአለልቱ ወረዳ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ “የሕዝብ መሪን በመግደል የሚሳካ ሕልም የለም” ሲል ግድያውን አውግዟል።
ይኹን እንጂ ቢቢሲ የሟቾቹን ቁጥር ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
ጉዳዩን በሚመለከት ለሰሜን ሸዋ ጸጥታ ቢሮ፣ ወረዳ አስተዳደር እንዲሁም ለወጫሌ ወረዳ አስተዳዳር በተደጋጋሚ ቢደወልም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
የሰሜን ሸዋ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አቶ ንጉሡ ኮሩ “ለሕዝባቸው ብልጽግና ቀን ተሌት ይሰሩ የነበሩ” መሆናቸውን ገልጾ የሐዘን መግለጫ አውጥቷል።
መግለጫው አክሎም በወጫሌ ወረዳ ካራ በሚባል አካባቢ የጸጥታውን ሁኔታ ለመከታተል ተሰማርተው ባሉበት መንግሥት ሸኔ ሲል በሚጠራቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች መገደላቸውን ገልጿል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀኑ ላይ ትናንት በሰሜን ሸዋ ዞን ወጫሌ ወረዳ በሁለት ቦታዎች ላይ በፈጸመው ጥቃት 120 የመንግሥት ወታደሮችን መግደሉን አስታውቋል።
በሰሜን ሸዋ ወጫሌ ወረዳ ሁለት ቦታዎች እንዲሁም በካራ፣ ባጮ ፋሉሚ በተባሉ አካባቢዎች ጥቃት ከፍቶ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ የጸጥታ ኃይሎችን መግደሉን ገልጿል።
አቶ ንጉሤ የአለልቱ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩ ሲሆን የወጫሌ ወረዳ አስተዳደር ሆነው የተሾሙት ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።
ወረዳው ያወጣው መግለጫ አቶ ንጉሡ በታጣቂዎች መገደላቸውን እንጂ የታጣቂውን ማንነት በስም ከመግለጽ ተቆጥቧል።
እንደ ወጫሌ ወረዳ መንግሥት ኮሙኑኬሽን መግለጫ ከሆነ አቶ ንጉሡ እና ሌሎች የወረዳው ባለሥልጣናት ከአካባቢው ነዋሪ ጋር በጸጥታ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በርካታ ውይይቶችን ሲያካሄዱ ነበር።
በሰሜን ሸዋ የመንግሥት ኃላፊዎች ከታጣቂዎች በሚደርስባቸው ጥቃት ሲገደሉ ይህ የመጀመርያው አይደለም።
ከዚህ ቀደም የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሳደን ሶዶ አስተዳዳሪ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት ተከፍቶባቸው መገደላቸው ይታወቃል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን የአዳ በርካ ምክትል አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አብዲሳ ቀነኒም አንዲሁ በመኖርያ ቤታቸው አቅራብያ በታጣቂዎች መገደላቸው የታወሳል።
የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የሚያካሂዱት ውጊያ አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ሁለቱን አካላት የገቡበት ግጭት በሰላም እንዲቋጭ የተሞከሩ ድርድሮች ፍሬ አላፈሩም።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)