በእስራኤል እና በኢራን ግጭት ላይ የሩሲያ እና የቻይና አቋም ምንድን ነው?

እስራኤል በኢራን መስከረም 21/2017 ዓ.ም. ለተወነጨፉት 200 ሚሳዔሎች ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ነው በሚል ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ከቀናት በፊት ፈጽማለች።

ኢራን እነዚህን ጥቃቶች የፈጸመችው እስራኤል በጋዛ እና በሊባኖስ ሕዝብ ላይ እያደረሰች ላለው ጥቃት እንዲሁም የሐማስ እና የሄዝቦላህ መሪዎች ግድያ አጸፋዊ ምላሽ መሆኑን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ካለው የተቀናጀ ጥቃት ጋር በተያያዘ በኢራን የሚደገፈው ታጣቂው ቡድን ሄዝቦላህ በእስራኤል ሰሜናዊ ድንበር ላይ ሮኬቶችን ያስወነጭፋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል ያለው ግጭት ወደ ሁለንተናዊ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል ያንዣበበው ስጋት በዓለም ታላላቅ አገራት መካከል ባለው ግንኙነትም ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል።

እስራኤል በጋዛ ላይ ለምትፈጽመው ጥቃት በጦር መሳሪያ እየደገፈቻት ያለችው አሜሪካ አሁንም አጋሯ መሆኗን በይፋ አሳውቃለች።

የአሜሪካ ዋነኛ ተፎካካሪ ኃያላኑ ሩሲያ እና ቻይናስ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ላይ ያላቸው አቋም ምን ይመስላል? ምንስ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ?

ሩሲያ እና ኢራን፡ በጠላቴ ጠላት ላይ የተመሰረተው ወዳጅነት

ሩሲያ እና ኢራን አጋር አገራት አልነበሩም። ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግንኙነታቸው እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን “የስትራቴጂካዊ አጋርነት” ስምምነት ላይ ለመድረስ የጀመሩትን ግንኙነት ለማጠናቀቅ በሂደት ላይ ናቸው።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከአቻቸው የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን ጋር ከሁለት ሳምንታት በፊት ሲገናኙ በዓለም ክስተቶች ላይ ስለያዟቸው የአቋም ተመሳሳይነት ተናግረዋል። ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ጦርነት ኢራን አጋርነቷን አሳይታለች።

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ኢራንን የባለስቲክ ሚሳዔሎችን እና አጥቂ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ለሩሲያ አቅርባለች ሲሉ ከሰዋታል።

ምንም እንኳን አንድ ኢራናዊ የፓርላማ አባል የጦር መሳሪያዎቹ የተሰጡት ወደ ኢራን በሚገቡ ምግቦች ልውውጥ ነው ቢሉም ኢራን የባለስቲክ ሚሳዔሎችን ለሩሲያ አቅርባለች የሚለውን በይፋ ውድቅ አድርጋለች።

ከዓመታት ማዕቀብ በኋላ የኢራን አየር ኃይል ተዳክሟል። ሩሲያ በቅርቡ አንድ ቀለል ያለ አጥቂ አውሮፕላን ሳትልክ እንዳልቀረች ወታደራዊው መጽሔት ‘ጄንስ ዲፌንስ’ አስታውቋል።

ኢራን ለላከችላት የጦር መሳሪያዎች ሩሲያ በምላሹ ከእስራኤል ጥቃት ማግስት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢራንን አስመልክቶ የሚያወጣቸውን ውሳኔዎችን እንደምታግድ፣ እንዲሁም ማንኛውንም የኃይል እርምጃ እንደምትቃወም ይጠበቃል።

በተጨማሪም በቅርቡ በጦር ግንባሮች ድል እያደረገች ላለችው ሩሲያ የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ምዕራባውያን ትኩረታቸውን እንዲሁም ድጋፋቸውን ከዩክሬን እንዲያዞሩ ለማድረግ ይረዳታል።

ነገር ግን የእስራኤል ጥቃት በኢራን ውስጥ ባሉ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ለሩሲያ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ምዕራባውያኑ ከባባድ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች የጣሉባት ሩሲያ ነዳጇን ለመሸጥ የምትጠቀምባቸው ማስተላለፊያዎች የተወሰኑ ሲሆኑ፣ አንደኛው በኢራን በኩል ወደ ሕንድ የሚሄድ ነው።

ኢራን ከመካከለኛው ምሥራቅ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የሊባኖሱን ሄዝቦላህ እንዲሁም የጋዛውን ሐማስ ትደግፋለች። ሩሲያም ብትሆን ከሐማስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እየፈጠረች የሚመስል ሲሆን፣ የቡድኑ የከፍተኛ አመራሮቹ ልዑካን ቡድን ሞስኮን ጎብኝተው ነበር።

ምንም እንኳን ሩሲያ ኢራን ከእስራኤል በላይ ብትፈልጋትም ከሁለቱም አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለመጠበቅ እየጣረች ትገኛለች።

እስራኤል በበኩሏ ሩሲያ በዩክሬን እያደረገችው ያለውን ጦርነት እንዲሁም ከኢራን ጋር ያላትን ቁርኝት ብትነቅፍም ዩክሬን የጠየቀችውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ውድቅ አድርጋለች።

ሩሲያ ለኢራን በጥብቅ የምትወግን ከሆነ እስራኤል በምላሹ የጦር መሳሪያ ወደ ዩክሬን መላክ ልትጀምር እንደምትችል ሩሲያ ልትገምት ትችላለች። ነገር ግን ይህንን ለማድረግ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት የእስራኤልን አቅም ሊገድበው ይችላል።

ሌላኛው ኢራን እና ሩሲያን የሚያስተሳስራቸው አዘርባጃን ያለችበት የደቡባዊው የካውካሰስ ግዛቶች ናቸው። ይህ ስፍራ በማዕቀብ ውስጥ ላለችው ሩሲያ ቁልፍ የንግድ እና የኃይል ማዕከል ሆኖላታል።

በግዛቱ ውስጥ የበለጸገች እና በሕዝብ ብዛቷ የምትታወቀው አዘርባጃን ከሩሲያ እና ከኢራን ጋር ድንበር ትጋራለች። አዘርባጃን ሁለቱን አገራት የሚያገናኙ የመንገድ፣ የባቡር እና የመርከብ ትራንስፖርቶችን ለማሻሻል የሰሜን-ደቡብ የትራንስፖርት ኮሪደር ፕሮጀክትን ለመሥራት ተስማምታለች።

ሆኖም አዘርባጃን ከእስራኤል ጋር የጠበቀ ወታደራዊ ግንኙነት አላት። ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንዲሁም ሌሎች የረቀቁ የጦር መሳሪያዎችን ለእስራኤል መከላከያ ስታቀርብ ቆይታለች።

በተጨማሪም ባለፈው ዓመት አዘርባጃን አወዛጋቢውን እና ራስ ገዙን የናጎርኖ-ካርባካህ ግዛት ከአርሜኒያ በኃይል ወደ ራሷ ጠቅልላ አስገብታለች። ከጦርነቱ በፊት ከእስራኤል ወደ አዘርባጃን የሚላኩ የጦር መሳሪያዎች ቁጥር ማሻቀባቸውን አሶሼትድ ፕሬስ የበረራ ክትትል መረጃዎችን በመተንተን ዘግቧል።

እስራኤል በኢራን ላይ ለምታካሂደው ስለላ አዘርባጃን ወታደራዊ ተቋማቷን እንድትጠቀምባቸው ፈቅዳለች በማለት ኢራን ትከሰላች። አዘርባጃን ግን ይህንን ውንጀላ አስተባብላለች።

ስለዚህ እስራኤል በኢራን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ከአዘርባጃን ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ ጫና ያሳድር ይሆን ወይ? የሚለውን ሩሲያ በጥንቃቄ ማጤን አለባት። በዚህ ግጭት ዙሪያ ሌላኛው ጉዳይ ሩሲያ ቻይና የምትይዘው አቋም እና የምትወስደውን እርምጃ በቅርበት ትከታተላለች።

ሩሲያ ቴክኖሎጂ በተለይም ለጦር መሳሪያ ግብዓቶች እና ለኤሌክትሮኒክስ ገቢ ንግድ እንዲሁም በፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አንጻር በቻይና ላይ ጥገኛ ናት።

ስለዚህም በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው ቀውስ ላይ ቻይና ያላት ስጋትን እንዲሁም አቋምን የምትገልጽ ከሆነ ሩሲያም ይህንኑ መከተሏ የማይቀር ነው።

ቻይና እና ኢራን፡ ወደ ግጭት ሳትገባ ድጋፍ መስጠት

ቻይና እና ኢራን ዲፕሎማሲያዊ ሽርክና እና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስርን ጨምሮ ለረጅም ጊዜ የቆየ የጠበቀ አጋርነት አላቸው።

እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ቻይና ድጋፏን እንደምትቀጥል ይጠበቃል። ቻይና ወደ ግጭት እንዳትገባ ርቀቷን በመጠበቅ ለአጋሯ ኢራን የትርክት ድጋፍ ማድረጓ የማይቀር ነው።

ኢራን በእስራኤል ላይ መስከረም 21 ያስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በምላሻቸውን ኢራንን አልጠቀሷትም።

እስራኤል በሊባኖስ ላይ የፈጸመችውን ወረራ አንስተው አገራቸው የሊባኖስን ሉዓላዊነት መጣስ እንደምትቃወም ገልጸዋል። “በመካከለኛው ምሥራቅ ለተነሳው ለዚህኛው ዙር ብጥብጥ ዋነኛው መንስዔ የጋዛ ጥቃት ነው” ሲሉ መልሰዋል።

ቻይና በተደጋጋሚ የጋዛ ጦርነት እንዲቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሪ ስታደርግ የነበረ ሲሆን፣ ፍልስጤማውያን እና ሊባኖስን በዲፕሎማሲ እንዲሁም በሰብዓዊ እርዳታ ትደግፋለች።

በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለው ፍጥጫ ከጠነከረስ የቻይና ምላሽ ምን ይሆን?

ቻይና በእስራኤል ውስጥ በተለይም በመሠረተ ልማት እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰች ሲሆን፣ ይሄኛው ዙር የጋዛ ግጭትም ከተነሳ በኋላ አላቆመችም።

ከኢራን ጋር የበለጠ ብትወግን እስራኤልን እንደ ኢኮኖሚያዊ አጋር የማግለል ስጋት ይኖረዋል የሚል አቋምም ሊኖራት ይችላል።

እስራኤል በዚህኛው ዙር አጸፋዊ ጥቃቷ የኢራን የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት አልፈጸመችም። ሆኖም ግን የአሁኑ እርምጃዋ ለወደፊት በእነዚህ ተቋማት ላይ ጥቃት አትፈጽምም የሚለውን አያሳይም።

ቻይና ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ ስትሆን 90 በመቶ የሚሆነው የኢራን ድፍድፍ ነዳጅ ለቻይና እንደሚላክ ኤስ ኤንድ ፒ የተሰኘው የፋይንስ መረጃ ተቋም ሪፖርት ያሳያል።

እስራኤል እወስደዋለው በምትለው አጸፋዊ ጥቃት የኢራንን የነዳጅ መሠረተ ልማቶችን የምትመታ ከሆነ ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድር ቻይናም የእስራኤልን ድርጊት ጠንከር ባለ መልኩ እንደምታወግዝ ይጠበቃል።

አሜሪካ በኢራን ላይ ማዕቀቦችን ብትጥልም ቻይና ከኢራን ነዳጅ በመግዛት ቀጥላለች። በተጨማሪም በኢራን እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ተቋርጦ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲቀጥል የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ቻይና ባለፈው ዓመት አሸማግላለች።

በተጨማሪም ቻይና በኢራን ላይ ያላትን ተጽእኖ እንድትጠቀም አሜሪካ መጠየቋን ባለሥልጣናቱን ዋቢ አድርገው የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ባለስልጣናቱ በቀይ ባሕር መርከቦች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጽያን ኢራን እንድትቆጣጠራቸው ቻይና እንድታደርግ ጠይቀዋል ተብሏል።

ምንም እንኳን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተጨማሪ ጥያቄዎች ቢኖሯቸውም ኢራን እና ቻይና የአዛዥ እና ታዛዥ ግንኙነት የላቸውም። በተጨማሪም ቻይና እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ በተለይም ከአሜሪካ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ እንደማትቀበል የታወቀ ነው።

ቻይና ይህንን ዕድል አሜሪካን ለመተቸት እና ከዓለም አቀፉ ደቡብ አገራት (ግሎባል ሳውዝ) ጎን በመሆን የፍልስጤማውያንን አገር የማግኘት መብት በመደገፍ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዋን ለማሳደግ ትጠቀምበታለች።

ቻይና ይህንን የታዛቢነት ሚናዋን ይዛ መቀጠሏ ጋር ያለባት ስጋት ኢምንት ነው። ነዳጅ ከፈለገችም ፊቷን ሳዑዲ አረቢያን ወይም ሩሲያን ወደመሳሰሉ ከፍተኛ ነዳጅ ላኪዎች ማዞር ትችላለች።

ቻይና በኢራን እና በእስራኤል መካከል ስላለው ውጥረት የምትለውን ነገር በቀጣዮቹ ቀናት የምንሰማ ቢሆንም በግጭቱ የመሳተፍ ዕድሏ አነስተኛ ነው።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)