በስፔን ለደረሰው የጎርፍ አደጋ በተሰጠው ምላሽ የተቆጡ ተቃዋሚዎች በንጉሡ እና ንግሥቲቷ ላይ ጭቃ ወረወሩ

ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ለሞቱበት የስፔኑ የጎርፍ አደጋ የተሰጠው ምላሽ በቂ አይደለም ያሉ ተቃዋሚዎች በንጉሡ እና ንግሥቲቱ ላይ ጭቃ ወረወሩ።

ንጉሡ እና ንግሥቲቱ በከፋ የጎርፍ አደጋ የተመታችውን የቫለንሺያ ግዛት ለመጎብኘት በሄዱበት ወቅት ነው የተቆጡ ተቃዋሚዎች ጭቃ እና ሌሎች ነገሮችን የወረወሩባቸው።

ንጉሣውያኑ ጥንዶች፣ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎች መሪዎች ፓይፖርታ የተሰኘችውን ከተማ እየጎበኙ ባለበት ወቅት “ነፍሰ ገዳይ” እና “እፈሩ” የሚሉ ስድቦችን ከተቃዋሚዎች ተሰንዝሮባቸዋል።

ንጉሥ ፌሊፔ እና ንግሥት ሌቲዚያ ፊታቸው እና ልብሳቸው ጭቃ ተለውሶ ጉዳት የደረሰበትን ማኅበረሰብ ሲያጽናኑ ታይተዋል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ የከፋ ነው በተባለው በዚህ ጎርፍ ከ200 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። የነፍስ አድን ሠራተኞች በሕይወት ያሉ ሰዎችን ለመታደግ እንዲሁም አስከሬኖችን ለማውጣት በመሬት ስር ባሉ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እና መተላለፊያ ዋሻዎች ፍለጋቸውን ቀጥለዋል።

ጎርፉን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ አልነበረም በሚል እንዲሁም ለአደጋው የተሰጠው ምላሽ በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ ቁጣ ተፈጥሯል።

ንጉሡ ከመኪናቸው ወርደው በጠባቂዎቻቸው እና በፖሊስ ታጅበው በእግረኛ መንገድ ላይ ሲጓዙ የተቆጡ በርካታ ተቃዋሚዎች ጭቃ ሲወረውሩ፣ ሲዘልፏቸው እና ሲጮሁ የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቷል።

ጠባቂዎቻቸው እና ፖሊሶች ንጉሡን ከበው ቀለበት በመሥራት ከተቃዋሚዎቹ የሚወረወርባቸውን ጭቃ እና ቁሳቁሶች ለመከላከል ሲታገሉ ታይተዋል።

ንጉሡ በበኩላቸው በርካቶቹን ሲያዋሩ እና አልፎ ተርፎም ሲያቅፏቸው ታይተዋል።

ንጉሡ፣ ንግሥቲቱ እና አጃቢዎቻቸው ፊት እና ልብሳቸው ጭቃ መቀባቱን የሚያሳዩ በርካታ ምሥሎች ወጥተዋል።

የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ እና የቫለንሺያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ካርሎስ ማዘን በጉብኝቱ ላይ ንጉሣውያኑ ጥንዶችን ተቀላቅለው የነበረ ቢሆንም የተቃዋሚዎች ቁጣ መጠንከሩን ተከትሎ ከስፍራው በፍጥነት እንዲወጡ ተደርገዋል።

የስፔን መገናኛ ብዙኃን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ቁሳቁሶች እንደተወረወሩባቸው የዘገቡ ሲሆን፣ ቢቢሲ ያረጋገጠው ቪዲዮ ደግሞ መኪናቸው ላይ ድንጋይ ሲወረወርባቸው አሳይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሄዱ በኋላ “ሳንቼዝ የት ነው?” የሚሉ ድምጾች ተሰምተዋል።

“ገና 16 ዓመቴ ነው። እኛ ተጎጂዎችን እየረዳን ነው። መሪዎቹ ግን ምንም እያደረጉ አይደለም። ሰዎች አሁንም እየሞቱ ነው፤ ይህንን መታገስ አልችለም” ሲል ታዳጊው ልጅ እያለቀሰ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሌላ ግለሰብ ደግሞ “እንድንሞት ትተውናል። ሁሉንም ነገር አጥተናል። ገንዘባችንን፣ ንብረታችንን፣ ህልማችንን” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

በኋላ ላይ የፀጥታ ኃይሎች የተቆጣውን ሕዝብ ለመበተን ሲሞክሩ ታይተዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)