በሲድኒ በስለት የተወጉት የኦርቶዶክስ ጳጳስ ጥቃት አድራሹን “ይቅርታ ብያለሁ” አሉ…..

ባለፈው ሰኞ በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ በቀጥታ በሚተላለፍ ሰብከት ላይ ሳሉ በስለት ጥቃት የደረሰባቸው አቡነ ማር ማሪ ኢማኑኤል በፍጥነት እያገገሙ እንደሆነ ገልጸው ጥቃቱን እንዳደረሰ ለተጠረጠረው ግለሰብም ይቅርታ እንዳደረጉ ተናግረዋል።

ጳጳሱ በተቀረጸ ድምጽ ባስተላለፉት መልዕክት ህብረተሰቡ እንዲረጋጋም ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት አራት ሰዎች ተጎድተዋል። ፖሊስ ጥቃቱ ሃይማኖታዊ መነሻ ያለው የሽብር ድርጊት ነው ብሏል።

ከክስተቱ በኋላ ጳጳሱ በሚያገለግሉበት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ሁከት ተፈጥሯል።

ጥቃቱን እንዳደረሰ የተጠረጠረ እና ራሱም የተጎዳው የ16 ዓመት ታዳጊ በቁጥጥር ስር የዋለ ቢሆንም እስካሁን ክስ አልተመሰረተበትም። ባለስልጣናት የታዳጊውን እምነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ታዳጊው በአረብኛ ሲጮህ እና “ነብዩ” የሚልበትን ቪዲዮ የሀገሪቱ የስለላ ቢሮ እየመረመረው እንደሆነ የተቋሙ ኃላፊ ተናግረዋል።

አራት ደቂቃ ርዝማኔ ባለው እና በቤተክርስትያኑ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው ድምጽ ላይ ጳጳሱ “ማንም ይሁን ማን” ይህንን ላደረገው ግለሰብ ይቅርታ አድርጌያለሁ ሲሉ ይደመጣሉ።

“እናም ለአንተ ሁልጊዜ እጸልያለሁ። ይህንን እንድታደርግ የላኩህ ማንም ይሁኑ ማን በኃያሉ ኢየሱስ ስም ይቅርታ አድርጌላቸዋለሁ” ብለዋል።

ጨምረውም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ እና ሰዎች ሊጨነቁ እና ሊያሳስባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል።

ፖሊስ የኦርቶዶክስ ጳጳሱ ከዚያ ጥቃት መትረፋቸው ዕድለኛ ያስብላቸዋል ብሎ ነበር።

ይህ እጅግ አሰቃቂ የጥቃት ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰራጨ እና ሁከት ካስከተ በኋላ በመቶዎች የሚቇጠሩ ሰዎች ወደ ቤተክርስትያኑ ተጉዘዋል።

በተፈጠረው አለመረጋጋት ሁለት የፖሊስ መኮንኖች የተጎዱ ሲሆን 10 የፖሊስ ተሽከርካሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአደጋ ጊዜ የጤና ባለሙያዎችም ለደህንነታቸው ሲፈሩ ታይቷል።

ፖሊስ በዚህ ሁከት ላይ የተሳተፉትን ተከታትሎ ለፍርድ እንደሚያቀርባቸው ቃል ገብቷል።

ትላንት ረቡዕ ምሽት ከክስተቱ ጋር በተገናኘ አንድ የ19 ዓመት ወጣት ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ስር አውለዋል።

በከተማዋ ከፍተኛ ስጋት ያንዣበብ ሲሆን ባለስልጣናት እና ዜጎች ተመሳሳይ ጥቃት ይከሰታል የሚል ስጋት ውስጥ ናቸው።

ጳጳሱ በመልዕክታቸው ዜጎች ከፖሊስ ጋር እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።

“የክርስቶስን ተግባር እንድትፈጽሙ እፈልጋለሁ። ጌታችን ክርስቶስ እንድንጣላ በፍጹም አላስተማረንም። መጥፎ ስራ እንድንሰራ አላስተማረንም” ብለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(BBC)