በምሥራቅ ወለጋ የጦር መሳሪያ አስረክቡ የተባሉ የአማራ ተወላጆች ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናገሩ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ ባለው የታጣቂዎች ጥቃት ምክንያት በመንግሥት ፈቃድ የግል የጦር መሳሪያ የታጠቁ የአማራ ተወላጆች መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ በመጠየቃቸው በአካባቢው አዲስ ውጥረት ነግሷል።

በዞኑ ጊዳ አያና ወረዳ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች “በመንግሥት ይሁንታ ታጠቅነዋል” የሚሉትን መሳሪያ አስረክቡ መባላቸውን ተክትሎ ስጋት ላይ መውደቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ ጠቅሰው፤ በተለይ ከሦስት ዓመት በፊት ኅዳር 24/2014 ዓ.ም. በተፈጸመ ጥቃት “ጭፍጨፋ” መፈጸሙን ያስታውሳሉ።

የሰሜኑ ጦርነት መቀስቀቀሱን ተከትሎ በአካባቢው የነበረው መከላከያ ሠራዊት ቦታውን ለቆ ሲወጣ ራሳቸውን እንዲከላከሉ በመንግሥት እንደተነገራቸው የሚገልጹት ነዋሪዎች፤ በመንግሥት ተፈቅዶልን መሳሪያ ታጥቀናል ይላሉ።

“የሸኔ ታጣቂ በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው ቀጠናዎች ውስጥ አንዱ ምሥራቅ ወለጋ ነው። በዚያን ሰዓት [በሰሜኑ ጦርነት] እስከ መንግሥት መሥሪያ ቤት አቤቱታ ቀርቦጎ፤ መንግሥት ‘የሚደርስልህ አካል የለም፤ ገዝተህ ራስህን ተከላከል’ ብሎ በሰጠው ፈቃድ መሠረት [መሳሪያ] ገዝተን ቤተሳባችንን ስንከላከል ቆይተናል” ሲሉ ሌለ ነዋሪ ተናግረዋል።

“በየአካባቢው ሰላሙ ሲጠፋ ሕዝቡ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ መሳሪያ እየገዛ ታጠቀ” የሚሉት ሌላ ነዋሪ፤ “መሞታችን ካልቀረ እያለ ሰዉ በሬውን እየሸጠ፤ አንድ ለሁለት መሳሪያ እየገዛ፤ ራሱን መከላከል ጀመረ” ሲሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ መሳሪያ እንዴት መታጠቅ እንደጀመረ ያብራራሉ።

በሰፈራቸው ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመው ሰው “ተገድሎ ቤቱ ሲቃጠል” በማየታቸው መሳሪያ ለመግዛት እንደወሰኑ የሚናገሩ ሌላ ነዋሪ ነዋሪ፤ በመንግሥት ይሁንታ ቤተሰባቸውን ለመጠበቅ ካላቸው የቁም እንስሳት መካከል የተወሰኑትን ሸጠው መግዛታቸውን ተናግረዋል።

በሬ እና ቀለባቸውን ሸጠው በ2013 ዓ.ም. “ራሳቸውን ለመከላከል” ‘ሙሉ ትጥቅ’ በ150 ሺህ ብር እንደታጠቁ የሚናገሩ ሌላ ነዋሪም፤ መሳሪያቸውን በአካባቢው ባለሥልጣናት “ተመዝግቦ፤ ሕጋዊ አድርገናል” ይላሉ።

“ይሄው ሦስት ዓመቱ ነው። ሕጋዊ አድርጎ ለመንግሥት እያገለገለ ነበር” የሚሉት ነዋሪ በበኩላቸው ከሰሞኑን በወረደው ትዕዛዝ ከመንግሥት ጋር ውጥረት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።

“[መሳሪያውን] አስመዝግቦ እያገለገለበት፤ እየወጣ እየወረደ፤ ከወረዳ እስከ ክልል እየጠበቀ” ነበር ሲሉም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት ፀጥታ የአካባቢያቸውን ሰላም ሲያስከብሩ እንደነገር ገልጸዋል።

ነዋሪዎች ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት በጠሩት ስብሰባ መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ሆኖም ትዕዛዙ “ማንነትን የለየ ነው” ያሉት ነዋሪዎች በአካባቢው የሚኖሩ እና ታጠቁ “የኦሮሞ ማኅበረሰብ አባላት ትጥቅ ፍቱ አልተባሉም” በማለት ትጥቅ ማስፈታቱ በእነሱ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

“እነሱን ዛሬ [ትጥቅ] አውርዱ ያላቸው የለም። እነሱ ጠቅለው የመንግሥት ሚሊሻ ሆነዋል። ልብስም [የደንብ ልብስ] ለብሰዋል፤ መታወቂያም ተሰጥቷቸዋል። አሁን አውርዱ የሚባለው ብሔር የለየ ነው” በማለት ስጋት እንዳደረባቸው ተናግረዋል።

“ሽብሩ ከመጣ ዘንድሮ አራት ዓመቱ ነው” የሚሉት እና ዕድሜያቸው በመግፋቱ መሳሪያ እንዳልታጠቁ የሚናገሩ አንድ ነዋሪ፤ አማራጭ ማጣታቸውን ተናግረዋል።

“ለምንስ ኦሮሞ ይሞታል? ለምንስ አማራ ይሞታል? ኢትዮጵያዊ ነን እባካችሁ እንኑር። አትኖሩም ካላችሁ ደግሞ መንገዱን ክፈቱልን እና እንውጣ። እናት፣ አባት ደካማዎች አሉን፤ መንገዱን ክፈቱልን እንውጣ” ብለው መጠየቃቸውን የሚናገሩት ነዋሪው፤ ከመንግሥት ኃይሎች ማስፈራሪያ እና ዛቻ እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታጣቂዎች በቅርብ ርቀት እንደሚገኙ የጠቆሙት ነዋሪው፤ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የተከሰተውን በማሰብ የደኅንነት ስጋታቸውን ለፀጥታ ኃይሎች ሲያሳውቁ፤ “አያገባንም አሉን” ይላሉ።

“እዚሁ ታጣቂዎች ቁጭ ብለዋል እንዴት አድርገን ነው [መሳሪያ] የምንሰጣችሁ? ስንል ‘የሚያገባን ነገር የለም’ [አሉን]። እንዲህ ተብሎ ከአንድ የጦር መኮንን ይሄ ቃል ይሰነዘራል?” ሲሉ በተሰጣቸውን ምላሽ ማዘናቸን ተናግረዋል።

“ብሔር እና ብሔሩ በመጠኑም ቢሆን ተቀራርቦ ነበር፤ የተፈናቀለውም ሕዝብ ወደ ቤቱ ገብቶ ነበር” ሲሉ በድጋሚ ውጥረት ስለመንገሱ የሚናገሩት ነዋሪው፤ “እግዚአብሄር አምላክ ምን እንዳመጣብን እንጃ” ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

አካባቢው እንዳልተረጋጋ እና ሰላም እንዳልሰፈነበት የሚናገሩት ሌላ ነዋሪው፤ ውሳኔውን “ሴራ” ነው ይሉታል።

“የእኛ ትጥቅ ከወረደ በኋላ፤ የሸኔ ወታደሮች ክፍተቱን ተጠቅሞ ገብቶ በንጹሃን ላይ ጭፍጨፋ እንዲያደርጉ በቀጥታ የተሠራ ሴራ ይመስላል” በማለት ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ ውሳኔው “የኦሮሚያን ሚሊሻ ለማስታጠቅ ነው” ያሉ ሲሆን፤ በአካባቢው መንግሥታዊ የሚሊሻ አደረጃጀት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

እስከ ማክሰኞ ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም. መሳሪያ እንዲያስረክቡ ቀን እንደተቆጠላቸው እንደነበር የሚናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ ማኅበረሰቡ “‘ሁለት ጊዜ አልሞትም አንድ ጊዜ ነው የምሞተው፤ ከእነ ትጥቄ ነው መሞት ያለብኝ’ ብሎ ሸሽቶ ጫካ ነው ያለው” ብለዋል።

የሁለት ዓመት ህጻን ልጃቸውን ጨምሮ ቤተሰባቸውን ይዘው እንደወጡ የሚናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ “ሴቶች፣ ህጻናቶች፣ አረጋዊያን በውርጭ ነው ያደሩት፤ ጫካ ውስጥ ነው ያሉት” በማለት ያሉበትን ሁኔታ ተናግረዋል።

“ዛሬ አይደለም የሞትነው፤ ከሞትን ቆይተናል። የፈለገውን ዋጋ እንከፍላለን እንጂ ትጥቃችንን አንሰጥም ብለን ወስነን ነው ተቀመጥነው” ሲሉ አካባቢው ባለ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሽገዋል ያሏቸው መንግሥት ኃይሎች ሊያጠቋቸው እነደሚችሉ ተናግረዋል።

እሳቸውን ጨምሮ ስጋት ያደረባቸው መሳሪያ የታጠቁ እና ያልታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤታቸው መውጣታቸው ያረጋገጡ ሌላ ነዋሪ፤ የመንግሥት ኃይሎች ትጥቅ ለማስፈታት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ጥሪ እያደረጉ ነው። . . . መንግሥትን መዋጋት አትችሉም፤ እጅ ብቻ ብትሰጡ ነው የሚሻለው’ የሚል ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይሰጣሉ” ብለዋል።

ነዋሪዋቹ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት የቀረበውን ትጥቅ የመፍታት ትዕዛዝ የተቃወሙት በመንግሥት ላይ በማመጽ ሳይሆን፣ በአካባቢው አሁንም ጥቃት የሚፈጽሙባቸው ታጣቂዎች በመኖራቸው ለቤተሰቦቻቸው ደኅንነት በመስጋታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

“በአካባቢው ሙሉ ለሙሉ ሰላም እና ደኅንነት ሳይወርድ፣ ታጣቂዎቹ ከዛሬ ነገ መጥተው ይጨርሱናል በሚል ስጋት ውስጥ ባለንበት ሁኔታ እኛን ለይቶ ትጥቅ ለሞት አሳልፎ መስጠት ነው” የሚሉት ነዋሪ በመንግሥት ስር ሆነው አካባቢያቸውን ለመጠበቅ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ግማሸ ክፍለ ዘመን ያህል በአካባቢው መኖራቸውን የሚናገሩ አንድ ነዋሪ ከአንዶዴ ዲቾ ቀበሌ በተጫማሪ 1954 እስከ 1961 ዓ.ም. ከወሎ የሰፈሩ የአማራ ተወላጆች ይኖሩባቸዋል ባሏቸው ጉቱ ጊዳ ወረዳ መጋሎ፣ አቤዶጎሮ ወረዳ ቱሉጋና፣ ኪረሙ ወረዳ ሃሮ አዲስ ዓለም በተባሉ አካባቢዎች ላይ መሳሪያ ፍቱ በሚል ጫና እተደረገ ነው ይላሉ።

ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ስብሰባ በተደረገበት አንገር ጉቴ ከተማ ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች 120 መሳሪያን እንዳስፈቱም ተናግረዋል።

መሳሪያውን “ሌሊት እንደተኙ ከበባ በመፈጸም፤ በማንገራገር” እንደተቀበሏቸው ሌላ ነዋሪ ገልጸዋል።

“እኛ መኖር እንፈልጋለን። [አካባቢው ላይ] አትኖሩም ከተባለ ደግሞ ያለምንም ደም መፋሰስ ያሻግሩን እና ረሃቡ ይግደለን” ሲሉም ተማጽነዋል።

ቢቢሲ በአካባቢው ስላለው ውጥረት ኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንዲሁም ከምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪዎች እና ከአንዶዴ ዲቾ ቀበሌ አስተዳዳሪ ምላሽ ለማግኘት ለሁለት ቀናት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የክልሉ ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለ ‘ሚሊሻ’ ብቻ መሳሪያ መታጠቅ እንደሚችል፤ ከዚህ አደረጃጀት ውጪ “መሳሪያ ታጥቆ መገኘት ያስጠይቃል። . . . ከዚህ ውጪ የሆነው ሕገ ወጥ ነው” በማለት ለአሜሪካ ድምጽ ሰሞኑን ተናግረዋል።

አሁን ትጥቅ እንዲፈቱ የታዘዙት በጊዳ አያና ወረዳ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ‘ጋችና ሲርና’ በተባለው የአካባቢ ሚሊሻ አደረጃጀት ውስጥ እንዲገቡ እንዳልተጠየቁ ጠቁመው፤ ለሁለት ወረዳዎች 100 ሚሊሻ ብቻ እንደተፈቀደ ተናግረዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)