ሩሲያ ጉግል ዓለማችን ካላት አጠቃላይ ገንዘብ በላይ ቅጣት እንዲከፍል ወሰነች

የሩሲያው ፍርድ ቤት የሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዩቲዩብ ላይ እንዳይታዩ በመታገዳቸው ጉግል ሁለት አንዲሲሊዩን ሩብል እንዲከፍል ወስኖበታል።

አንዲሲሊዮን 36 ዜሮዎች ያሉት ቁጥር ነው።

ጉልግ በሩሲያው ፍርድ እንዲከፈል የተፈረደበት ገንዘብ በዶላር ሲመነዘር $20,000,000,000,000,000,000,000,000,000,000,000 ነው።

ሁለት ትሪሊዮን የሚያወጣ ሀብት አለው የሚባለው ጉግል ምንም እንኳ ከዓለማችን እጅግ ሀብታም ኩባንያዎች አንዱ ቢሆንም፣ ይህን ገንዘብ የመክፈል አቅም የለውም።

ይህ ቁጥር የዓለማችን አገራት ጠቅላላ ያልተጣራ ምርት (ጂዲፒ) በላይ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እንደሚለው የዓለማችን ጂዲፒ 110 ትሪሊዮን ነው።

የሩሲያ መንግሥት ዜና ወኪል የሆነው ታስ እንደዘገበው ገንዘቡ እንዲህ ሊጋነን የቻለው ቅጣቱ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ነው።

ታስ እንደዘገበው የክሬምሊኑ ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ “ይህ ቁጥር እንዴት እንደሚጠራ እንኳን አላውቀም” ሲሉ አምነው ነገር ግን “የጉግል ኃላፊዎች ትኩረት እንዲሰጡት” ጠይቀዋል።

ጉልግ የተጣለበትን ቅጣት በተመለከተ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ቢቢሲ ለጠየቀውም ማብራሪያ ምላሽ አልሰጠም።

የሩሲያው የበይነ መረብ ዜና ገጽ አርቢሲ እንዳስነበበው ጉግል ቅጣቱ የተላለፈበት 17 የሩሲያ የዜና ጣቢያዎች ዩቲዩብ ላይ ይዘታቸውን እንዳያስተላልፉ እገዳ ስለተጣለባቸው ነው።

ይህ የይዘት ቁጥጥር የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2020 ቢሆንም፣ ከሁለት ዓመታት በኋላ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ስትጀምር ነው ሁኔታዎች የተካረሩት።

በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ምዕራባዊያን የነዳጅ ኩባንያዎች ከሩሲያ መውጣት ጀምረዋል። ኩባንያዎቹ የወጡት ሩሲያ በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት ንግዳቸውን በነፃነት ማካሔድ ስላልቻሉ ነው።

የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን በአውሮፓ ሀገራት ሲታገዱ ሞስኮ በበኩሏ የመልስ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች።

በ2022 በሩሲያ የጉግል ወኪል ኩባንያ መክሰሩን ሲያስታውቅ ጉግል ደግሞ በሩሲያ ማስታወቂያን ጨምሮ ሌሎች የንግድ ሥራዎችን ማከናወን ማቆሙን አስታውቋል።

ነገር ግን የጉግል ምርቶች ሙሉ በሙሉ ሩሲያ ውስጥ አገልግሎት መስጠት አላቆሙም።

በአሜሪካው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ውጥረት በገንዘብ ቅጣቱ ምክንያት እንደ አዲስ አገርሽቷል።

በአውሮፓውያኑ ግንቦት 2021 የሩሲያ የመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ ድርጅት ጉግል የሩሲያ ሚድያዎች በዩቲዩብ እንዳይተላለፉ እያደረገ ነው ሲል መውቀሱ አይዘነጋም።

በዩቲዩብ ላይ ይዘታቸው ከታገደባቸው ጣቢያዎች መካከል መንግሥታዊዎቹ አርቲ እና ስፑትኒክ ይገኙበታል።

ሐምሌ 2022 ሩሲያ ጉግል ላይ የ21.1 ቢሊዮን ሩብል (301 ሚሊዮን ዶላር) ቅጣት ማስተላለፏ ይታወሳል። ቅጣቱ የተላለፈው በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተወሰኑ ይዘቶች “እንዳይተላለፉ” በማድረጉ ነው።

ሩሲያ የፕሬስ ነፃነት የላትም የሚል ወቀሳ ይቀርብባታል። በሀገሪቱ ነፃ እና ገለልተኛ የሚባሉ መገናኛ ብዙኃን እንቅስቃሴ እንዲሁም ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የተገደበ ነው።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)