ምርጫውን ካማላ ሃሪስ ወይም ዶናልድ ትራምፕ ሊያሸንፉ የሚችሉባቸው 10 ነጥቦች
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይፋዊ የድምፅ መስጫ ቀን ዛሬ ነው። በተለይ ቁልፍ በሚባሉ ግዛቶች በሁለቱ ዕጩዎች መካከል ያለው ልዩኑት አሁንም እጅግ ጠባብ ነው።
ትራምፕም ሆኑ ሃሪስ በሁለት አሊያም በሦስት ነጥብ ልዩነት ምርጫውን ሊረቱ ይችላሉ።
ሁለቱም ዕጩዎች ወሳኝ በሚባሉ ቦታዎች ደጋፊዎቻቸው በነቂስ ወጥተው እንዲደግፏቸው የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳዎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
ከሁለቱ ዕጩዎች አንዱ ይህን ታሪካዊ የተባለ ምርጫ ሊያሸንፉባቸው የሚችሉ 10 ነጥቦችን እነሆ።
በመጀመሪያ የምንመለከተው በ130 ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ምርጫዎች ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ሊሆኑ ስለሚችሉት ትራምፕ እንመልከት።
የትራምፕ ጠንካራ ጎኖች
1 – ሥልጣን ላይ አለመሆናቸው
የመራጮችን ትኩረት እየሳቡ ካሉ ጉዳዮች አንዱ ምጣኔ ሀብት ነው። ምንም እንኳ የሥራ አጥነት ቁጥር ዝቅ ቢልም፤ የአክሲዮን ገበያው ሞቅ ሞቅ ቢልም በርካታ አሜሪካውያን ኑሮ እንደከበዳቸው ይናገራሉ።
የኑሮ ውድነቱ በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ከ1970ዎቹ በኋላ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍ ያለ ሆኗል።
በአወሮፓውያኑ 2024 በበርካታ ሀገራት በምጣኔ ሀብት ምክንያት ሥልጣን ላይ የነበሩ መንግሥታት ወርደዋል። አሜሪካውያንም ለለውጥ የጓጉ ይመስላሉ።
ከአሜሪካ ሕዝብ ሩብ ያክሉ ብቻ ናቸው አሁን ባለው ሁኔታ ደስተኛ እንደሆኑ የሚናገሩት። ሁለት ሦስተኛው ደግሞ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ናቸው።
ምንም እንኳ ሃሪስ ለውጥ ይዤ መጥቻለሁ ቢሉም ተቀባይነታቸው ዝቅ ካለው ጆ ባይደን ጋር ያላቸው ግንኙነት ደንቃራ ሆኖባቸዋል።
2 – ክፉ ዜና የማይበግራቸው
ትራምፕ ካለፈው ምርጫ ወዲህ ብዙ ነገር አይተዋል። በአውሮፓውያኑ ጥር 6 ደጋፊዎቻቸው ወደ ካፒቶል ሂል አቅንተው አመፅ ቀስቅሰዋል። በርካታ ክስ ቀርቦባቸዋል፤ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል። ይህም ሆኖ የትራምፕ ተቀባይነት ከ40 በመቶ ብዙም ንቅንቅ አላለም።
ዲሞክራቶች እና “በፍፁም ትራምፕን አንደግፍም” የሚሉ ሪፐብሊካኖች ሰውዬው አሜሪካንን ለመምራት ብቁ አይደሉም ቢሉም ትራምፕ ግን የፖለቲካ ሴራ ሰለባ ነኝ ይላሉ፤ ደጋፊዎቻቸውም ያምኗቸዋል።
ትራምፕ ይህን ምርጫ ለማሸነፍ ድምፃቸውን ለማን እንደሚሰጡ ያልወሰኑ መራጮችን ማሳመን ነው የሚጠበቅባቸው።
3 – ሕጋዊ ባልሆኑ ስደተኞች ላይ ባላቸው አቋም
ከምጣኔ ሀብቱ ቀጥሎ አነጋጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የስደተኞች ጉዳይ ነው። ዲሞክራቶች ፅንስ የማቋረጥ ጉዳይን አጥብቀው ሲይዙ፤ ሪፐብሊካኖች ደግሞ የስደተኞችን ነገር ተማምነዋል።
የምርጫውን ውጤት የሚጠቁሙ ድምፆች እንደሚያሳዩት መራጮች በስደተኞች ጉዳይ ትራምፕን ይደግፏቸዋል። ከዚህ ቀደም ካሉት ምርጫዎች በተሻለ ከላቲኖዎች የተሻለ ድምፅ እንደሚያገኙም ይጠበቃል።
4 – ዲግሪ የሌላቸው መራጮችን ትኩረት መሳባቸው
ትራምፕ ተረስተናል ብለው በሚያስቡ መራጮች ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አላቸው። በተለይ ቀድሞ ዲሞክራት የነበሩ የተደራጁ ሠራተኞችን ወደ ሪፐብሊካን ፓርቲ በማምጣት ይሞገሳሉ። የአሜሪካን ኢንዱስትሪ በታሪፍ ታድገዋል የሚል ምስጋናም ይቸራቸዋል።
ትራምፕ በተለይ ቁልፍ በሚባሉ ግዛቶች ወደ ገጠራማ እና ከከተማ ወጣ ያሉ ቦታዎች ሄደው ድምፅ ማጋበስ ከቻሉ ከለዘብተኛ እና ድግሪ የጨበጡ ሪፐብሊካኖች ጋር ተዳምሮ ድል ሊያደርጉ እንደሚችል ይታመናል።
5 – በታመሰው ዓለም ጠንካራ ሆነው መታየታቸው
የትራምፕ ተቺዎች የቀድሞው ፕሬዝደንት ከአምባገነን የዓለም መሪዎች ጋር በማበር የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ ይጎዳሉ ሲሉ ይነቅፏቸዋል።
ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዝደንት ተገማች አለመሆናቸውን እንደ ጠንካራ አቋም ያዩታል። እሳቸው ፕሬዝደንት ሳሉ ትልቅ የሚባሉ ጦርነቶች አለመነሳታቸውን ጠቅሰው ምረጡኝ ይላሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን እና እስራኤል የምትለግሰው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በርከታ አሜሪካውያንን ያስቆጣል። አሜሪካ በጆ ባይደን ዘመን ደካማ ሆናለች ይላሉ።
ከመራጮች አብዛኞቹ ትራምፕ ከሃሪስ በላቀ አሜሪካ ጠንካራ እንድትሆን ያግዛሉ የሚል እምነት አላቸው።
የሃሪስ ጠንካራ ጎኖች
1 – ትራምፕን አለመሆናቸው
ምንም እንኳ ትራምፕ የራሳቸው ጠንካራ ጎን ቢኖራቸውም እንደ ከፋፋይ ሰው ነው የሚታዩት።
በ2020 ምርጫ በሪፐብሊካን ታሪክ ትልቁን ድምፅ ማጋበስ ችለዋል። ነገር ግን 7 ሚሊዮን ተጨማሪ ድምፅ ሰጪዎች ምርጫቸው ጆ ባይደን በመሆናቸው ተሸንፈዋል።
ሃሪስ አሁን ከሚጠቀሟቸው መንገዶች አንዱ ትራምፕ ሥልጣን ቢይዙ ምን ይፈጠራል የሚለውን ጉዳይ ነው። “ፋሺስት” ናቸው ሲሉ ጠርተዋቸዋል፤ ዲሞክራሲን አደጋ ላይ ይጥላሉም ብለዋቸዋል። ሀገራቸውን “ከድራማ እና ከግጭት” ለማራቅም ቃል ገብተዋል።
ባለፈው ሐምሌ ሮይተርስ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ከአምስት አሜሪካውያን አራቱ ሀገራቸው ከቁጥጥር ውጪ ሆናለች ብለው ያምናሉ። ሃሪስ ዲሞክራቶች እና ለዘብተኛ ሪፐብሊካኖች ሀገሪቱን ያረጋጋሉ ብለው እንደሚያስቡ ተስፋ አድርገዋል።
2 – ባይደንን አለመሆናቸው
ባይደን ራሳቸውን ከምርጫው ሲያገሉ ዲሞክራቶች የዘንድሮውን ምርጫ እንደተሸነፉ እርግጥ ሆኖ ነበር። ነገር ግን ፓርቲው ሁኔታዎችን አጣድፎ ካማላ ሃሪስ ዕጩው ሆነው እንደሚቀርቡ አሳወቀ። እሳቸውም በአጭር ጊዜ ደጋፊዎችን በማሰባሰብ ጎልተው መውጣት ችለዋል።
መራጮች ጆ ባይደን ዕድሜያቸው ገፍቷል ብለው ሲያማርሩ ነበር። አሁን ሁኔታው ተገልብጦ ዶናልድ ትራምፕ በዕድሜ የገፉቱ ዕጩ ሆነዋል።
3 – ለሴት መራጮች ያላቸው ቅርበት
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕገ-መንግሥታዊ የነበረውን የሴቶች ፅንስ የማቋረጥ መብት መሻሩ ይታወሳል። የዘንድሮው ምርጫው ከዚህ ታሪካዊ ውሳኔ በኋላ የሚደረግ ነው።
ፅንስ የማቋረጥ መብት ሊጠበቅ ይገባል ብለው የሚያስቡ መራጮች ድምፃቸውን ያለማንገራገር ለካማላ ሃሪስ እንደሚሰጡ ግልፅ ነው። ይህ ጉዳይ በአሜሪካ ፖለቲካ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል።
ዛሬ [ማክሰኞ] በሚደረገው ምርጫ ቁልፍ ከሚባሉት ግዛቶች አንዷ የሆነችውን አሪዞናን ጨምሮ 10 ግዛቶች የፅንስ ማቋረጥ መብትን የተመለከተ የድምፅ ያገኛሉ ተብሎ ይታሳባል።
ይህ ለካማላ ሃሪስ ትልቅ ዜና ነው።
ካማላ ሃሪስ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝደንት ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም መራጫችን ሊያነሳሳ ይችላል።
4 – ድምፅ የሚሰጡ መራጮች
ለካማላ ድምፅ ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ኮሌጅ የተማሩ እና ጎልማሳ ሰዎች ከሌሎች በተሻለ በምርጫው ቀን ወጥተው የመምረጥ ባሕል አላቸው።
ዲሞራቶች ብዙውን ጊዜ ድምፅ በሚሰጡ መራጮች ነው የሚደገፉት። ትራምፕ ደግሞ በወጣቶች እና ድግሪ በሌላቸው ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት አላቸው።
ለምሳሌ በ2020 ምርጫ በርካታ የትራምፕ ደጋፊዎች እሳቸውን ለመምረጥ ቢመዘገቡም በምርጫው ቀን ወጥተው ድምፃቸውን አልሰጡም ይላል የኒው ዮርክ ታይምስ መረጃ።
አሁንስ የትራምፕ ደጋፊዎች ወጥተው ድምፃቸውን ይሰጣሉ ወይ የሚለው ትልቁ ጥያቁ ነው።
5 – ብዙ ገንዘብ ማፍሰሳቸው
የአሜሪካ ምርጫ እጅግ ውድ እና ብዙ ገንዘብ እንደሚፈስበት ግልፅ ነው። የ2024 ምርጫ ከቀደምቶቹ እጅግ ብዙ ገንዘብ የፈሰሰበት ሊሆን ተቃርቧል።
ሃሪስ ከትራምፕ የላቀ ብዙ ገንዘብ አፍስሰዋል። ባለፈው ሐምሌ ዕጩ ሆነው ከመጡ በኋላ ከትራምፕ የላቀ ገንዘብ ነው ጥቅም ላይ ያዋሉት። ትራምፕ ካለፈው ጥር ጀምሮ እንኳ ይህን ያህል ገንዘብ አላወጡም ሲል ፋይናንሻል ታይምስ አስነብቧል።
ካማላ ሃሪስ ብዙ ገንዘብ ያወጡት ለማስታወቂያ ሥራዎች ነው።
በተለይ ቁልፍ የሚባሉ ግዛቶች በማስታወቂያ ተጥለቅልቀዋል። ይህ ለሃሪስ የተሻለ ድምፅ ሊያስገኝላቸው ይችላል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)