መካከለኛው ምሥራቅን ወደ ከባድ የጦርነት አፋፍ ያደረሰው የዘመናት መገዳደል እና የጨነገፉ ተስፋዎች

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመሣሪያ ድምጽ የማይሰማበት፣ ሞት የሌለበት እና ፀጥታ የሰፈነበት ሕይወት ያልማሉ። አንድ ዓመት የዘለቀው ጦርነት ያሳየው ግን አስከፊ የፖለቲካ፣ የስትራቴጂ እና የሃይማኖት ልዩነቶች የሠላም ህልሞች እየመከኑ መሆናቸውን ነው። አሁንም ጦርነት የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካን እየቀረጸ ነው።

ለዓመታት ያልተፈታው ግጭት ሐማስን ለጥቃት አነሳስቷል። ድንበር ጥሶ የፈጸመው ጥቃት ደግሞ ለእስራኤላውያን እጅግ የከፋው ቀን ሆኖ ተመዝግቧል።

አንድ ሺህ 200 ገደማ ሰዎች (በአብዛኛዎቹ የእስራኤላውያን ሲቪሎች) ተገድለዋል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወደ ዋይት ሐውስ ደውለው “ከሆሎኮስት [የአይሁዶች ፍጅት] ወዲህ በታሪካችን እንዲህ ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት አይተን አናውቅም” ሲሉ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተናግረዋል። እስራኤልም ጥቃቱን የኅልውናዋ ስጋት አድርጋ መጠነ ሰፊ የበቀል ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ላይ ማካሄድ ከጀመረች አንድ ዓመት ሆነ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ብዙ አስከፊ ቀናትን እንዲያሳልፉ አድርጋለች። በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ወደ 42 የሚጠጉ ሰዎች (አብዛኞቹ ሲቪሎች ናቸው) ተገድለዋል። አብዛኛው የጋዛ ክፍል ፈራርሷል። ፍልስጤማውያንም እስራኤልን በዘር ማጥፋት ወንጀል ከሰዋል።

አሁን ጦርነቱ ተስፋፍቷል። ሐማስ ጥቃቱን ከፈጸመ ከ12 ወራት በኋላ መካከለኛው ምሥራቅ መጠነ ሰፊ እና የከፋ ጦርነት አፋፍ ደርሷል።

ሞት በቀኝም ግራም

አሁን ብዙ ግምቶችን እና ብዥታዎች ተቀርፈዋል። የመጀመሪያው የፍልስጤማውያንን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ሳይቀበሉ የፍልስጤምን ጉዳይ መቆጣጠር እንደሚችሉ ቤንያሚን ኔታንያሁ ማመናቸው ነበር።

ሆኖም ምኞት ብቻ ነበር። ፍልስጤም ከእስራኤል እኩል አገር ሆና መቆሟን ኔታንያሁ በፖለቲካ ሕይወት ዘመናቸው በሙሉ ተቃውመዋል። እንደ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ምዕራባውያን ወዳጆቻቸውም ጠቅላይ ሚንስትሩን እንደሚያሳምኑ ያምኑ ነበር።

ኔታያሁ የአሜሪካንን የሠላም ዕቅድንም ውድቅ አድርገዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን “ታላቁ ድርድር” ያሉትን ሃሳብ አቀረቡ። እስራኤል ለፍልስጤም የአገርነት ዕውቅና ትሰጣለች። ቴል አቪቭ በበኩሏ በአረቡ ዓለም ተሰሚነት ካላት በሳዑዲ አረቢያ ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ዕውቅና ታገኛለች። ሳዑዲዎች ደግሞ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የፀጥታ ስምምነት ይደርሳሉ።

ነገር ግን የባይደን ዕቅድ በፍጥነት ተጣለ። ኔታንያሁ ባለፈው የካቲት ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠት ሐማስን “በትልቁ መሸለም ነው” አሉ። በጠቅላይ ሚንስትሩ ካቢኔ ውስጥ ካሉት ጽንፈኛ ብሔርተኞች አንዱ የሆኑት ቤዛሌል ስሞትሪች ደግሞ ሐሳቡን ለእስራኤል “የኅልውና ስጋት” ይሆናል አሉ።

የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ጋዛ ውስጥ በሕይወት እንዳለ ይገመታል። እሱም የራሱ ሐሳብ ነበረው። ከዓመት በፊት “አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ” ተብለው የሚጠሩትን እና በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች እስራኤልን ለማሽመድመድ ጦርነት ውስጥ እንደሚገቡ ተስፋ አድርጎ ነበር። ነገር ግን ተሳስቷል።

ሲንዋር ጠላትን ለማስገረም በሚል መስከረም 26 እስራኤልን ለማጥቃት የያዘውን ዕቅድ በምሥጢር ነበር የያዘው፤ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ሲንዋር ዕቅዱን ኳታር በግዞት ለሚገኘው የድርጅቱ የፖለቲካ አመራር እንኳን ላያካፍል ይችላል። በቀላሉ ሊደረስበት የሚችል የስልክ ግንኙነት እና የላላ የደኅንነት ፕሮቶኮሎች ነበራቸው ሲሉ አንድ ምንጭ ተናግረዋል።

እስራኤል ጦሯን ወደ ጋዛ ማሰማራቷን እና አሜሪካ የጦር መርከቦቿን በቀጣናው ዝግጁ ማድረጓን ተከትሎ ኢራን ወደ መጠነ ሰፊ ጦርነት ለመግባት እንደማትፈልግ በግልጽ ተናግራለች።

ሐሳን ናስራላህ እና የኢራን ከፍተኛ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሌላ ዕቅድ አወጡ። የጋዛ ጦርነት እስኪቆም የእስራኤልን ሰሜናዊ ድንበር በሮኬት መደብደብ የሚል። በአብዛኛው ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ ቢያደርጉም እስራኤል ከ60 ሺህ በላይ ሰዎችን ከድንበር አካባቢ አስወጣች። የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ በሊባኖስ ደንበር በኩል ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ይሆናል።

እስራኤል ከሄዝቦላህ የሚደርስባትን ጥቃት እንደማትታገሥ ግልጽ አድርጋለች። በቡድኑ የጦርነት ልምድ እና ከኢራን በሚጎርፍለት ሚሳኤል እስራኤል ፈተና ይገጥማታል ተብሎ ነበር።

ከቀናት በፊት ግን እስራኤል ጥቃት ሰነዘረች። ከእስራኤል መከላከያ ኃይልም (አይዲኤፍ) ሆነ ከስለላ ተቋሙ ሞሳድ በኩል የኢራን አጋር በሆነው ቡድን ላይ ይህን ያህል ጉዳት በፍጥነት ሊደርስ እንደሚችል ያመነ አልነበረም።

እስራኤል ፔጀሮች እና ዎኪ ቶኪዎችን በማፈንዳት የሄዝቦላህን ግንኙነቶች ከማኮላሸት ባለፈ መሪዎቹን ገደለች። በዘመናዊ ጦርነት ታሪክ በጣም ኃይለኛ የሚባለውን የቦምብ ጥቃቶች ጀመረች። እስራኤል በመጀመሪያው ቀን ብቻ እስራኤል 600 የሚጠጉ ሊባኖሳውያንን ገደለች። አብዛኞቹ ሲቪሎች ናቸው።

አጋሮቼ እስራኤልን በማዳከም ያስፈራራሉ ያለችው ኢራንም ያለባትን ክፍተት አይታለች። ዋነኛው ደግሞ ከቀናት በፊት በቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስረላህን እና የቡድኑን ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸው ነው።

ናስረላህ ኢራን ወዳጆቿ እና ወኪሎቿ ናቸው የሚባሉት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙት አጋሮቿ ስብስብ የሆነው “አክሲስ ሆፍ ሬዚዝታንስ” ዋነኛው ሰው ነበሩ። በዚህም ምክንያት መገደላቸው ለስብስቡም ሆነ ለኢራን ትልቅ ጉዳት ነው።

ጥቃቱ የኢራን የአጋሮች ስብስብ እስራኤልን ለመከላከል እና ለማስፈራራት የነበራትን ስትራቴጂ አጠናክሮታል በሚለው እምነት ላይ ትልቅ ክፍተትን ፈጥሯል።

እስራኤል ጦርነቱን ድንበር ዘለል አድርጋዋለች። ዓላማው ሄዝቦላህን ተኩስ እንዲያቆም እና ከድንበር እንዲርቅ ለማስገደድ ከሆነ አልተሳካላትም። የደቡብ ሊባኖስ ጥቃት እና ወረራ ደግሞ ኢራንን አላስበረገጋትም።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢራን መጠነ ሰፊ ጦርነት እንዳይነሳ መፈለጓ ለእስራኤል የበለጠ የልብ ልብ የሰጠ ነው ብላ የደመደመች ይመስላል። ምላሽ ከሰጠች እስራኤልም ምላሽ ትሰጣለች። ለሃይማኖታዊው መሪ እና ለኢራን አብዮታዊ ዘብ አጣብቂኝ የፈጠረ አማራጭ ሆኗል።

ባለፈው ሳምንትኢራን በባሊስቲክ ሚሳዔሎች እስራኤል ላይ ትቃት ሰነዘረች።

ኪቡትዝ ክፋር ኦዝ የእስራኤልን ድንበር ከጋዛ ሰርጥ ለመጠበቅ ከተወጠረ የሽቦ አጥር አቅራቢያ የምትገኝ መንደር ናት። ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዒላማዎች አንዱ ያደረጋት ክፋር ኦዝን ነው። ስልሳ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። ወደ ጋዛ ከተወሰዱት 19 ታጋቾች መካከልም ሁለቱ ከምርኮ ካመለጡ በኋላ በእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል። ከመንደሯ የተወሰዱ አምስት ታጋቾች አሁንም ጋዛ ውስጥ ይገኛሉ።

ከጥቃቱ ከሦስት ቀናት በኋላ አካባቢው የውጊያ ቀጠና እያለ ነበር የእስራኤል ጦር ጋዜጠኞችን ወደ ስፍራው የወሰደው። በሐማስ የተገደሉት የእስራኤል ዜጎች ከቤታቸው ፍርስራሾች ውስጥ እየወጡ ነበር። ከእስራኤል ወታደሮች ወደ ጋር በኪቡትዝ ሲፋለሙ የተገደሉ የሐማስ ተዋጊዎች አስከሬንም በየቦታው ወድቆ ይታይ ነበር።

የሞቱት ቢቀበሩም ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ብዙም ለውጥ የለም። ሰዎች ወደ ቤታቸው አልተመለሱም። የተገደሉ እና የታገቱ ሰዎችን ስም ዝርዝር ከያዘ ፖስተር ጋር የፈራረሱት ቤቶች እንዳሉ ናቸው።

ከቤተሰቦቹ ጋር ከጥቃቱ የተረፈው ዞሃር ሽፓክ ዕድለኛ ያልሆኑትን ጎረቤቶቹን ቤት ለቢቢሲ አሳይቷል። አንደኛው ቤት ላይ መስከረም 26 በሐማስ የተገደሉ የወጣት ጥንዶች ትልቅ ፎቶ ተሰቅሎበታል። በቤቶቹ ዙሪያ ያለው መሬት ተቆፍሯል። ዞሃር እንደሚለው ከሆነ የወጣቱ አባት የልጁን ጭንቅላት ለማግኘት ለሳምንታት መሬቱን ሲቆፍር አሳልፏል። የወጣቱ አስከሬን የተቀበረው ያለ ጭንቅላቱ ነበር።

ሕይወታቸውን ወደ ቀደመው ሁኔታ ስለመመለስ ለማሰብ ጊዜው በጣም ገና መሆኑን ዞሃር ተናግሯል።

“አሁንም በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ነን። አሁንም እዚሁ ነን። አሁንም በጦርነት ውስጥ ነን። ጦርነቱ እንዲቆም ብቻ ሳይሆን በድል እንዲጠናቀቅ እንፈልጋለን። የጦር ሠራዊት ድልን አይደለም። የጦርነት ድልም አይደለም።”

“ለእኔ ድል እዚህ ጋር መኖር መቻሌ ነው። ከልጆቼ፣ ከልጅ ልጆቼ ጋር በሠላም መኖር ነው። እኔ በሠላም አምናለሁ” ብሏል።

ዞሃር እና ሌሎች በርካታ የክፋር ኦዝ ነዋሪዎች የግራ ዘመሙን የእስራኤል ፖለቲካ ይጋራሉ። የእስራኤል ብቸኛ የሠላም ዕድል የሚወሰነው ለፍልስጤማውያን ነፃነታቸውን በመፍቀድ ነው ይላሉ። እንደ ዞሃር እና ጎረቤቶቹ ያሉ እስራኤላውያን ኔታንያሁ ለመስከረም 26 ዓይነቱ ጥቃት ተጋላጭ እንዲሆኑ በማድረግ ከባድ ኃላፊነት ያለባቸው አጥፊ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው ብለው ያምናሉ።

“ከአጥሩ ማዶ የሚኖሩትን ሰዎች አላምንም። እኔ ሠላም እፈልጋለሁ። ወደ ጋዛ የባሕር ዳርቻ መሄድ እፈልጋለሁ። ሆኖም ግን አላምናቸውም። አንዳቸውንም አላምናቸውም።”

የጋዛ እልቂት

የሐማስ መሪዎች በእስራኤል ላይ የተፈጸመው ጥቃት እስራኤልን አስቆጥቶ በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ በሕዝባቸው ላይ ጥፋት ያመጣ ስህተት መሆኑን አይቀበሉም። ለዚህ ሁሉ ውድመት እና ሞት ተጠያቂ የሚያደርጉት የእስራኤልን ወረራ ነው።

ኢራን እስራኤል ላይ ሚሳዔሎችን ከማስወንጨፏ ከአንድ ሰዓት በፊት ከጋዛ ውጪ ካሉት የሐማስ ከፍተኛ መሪ አንዱ የሆኑት ኻሊል አል-ሀያን ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር። ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም አባላቱ ሠላማዊ ሰዎችን ዒላማ አድርገዋል መባሉን ክደዋል። የፍልስጤማውያንን ችግር የዓለም የፖለቲካ አጀንዳ ለማድረግ ጥቃቱ አስፈላጊ እንደነበርም አስምረውበታል።

“በዓለም ላይ ምክንያት ያለው እና መመለስ ያለበት ጥያቄ ያለው ሕዝብ እንዳለ ለመንገር ማንቂያ ደወል መኖሩ አስፈላጊ ነበር። ጠላት ለሆነችው እስራኤል ደግሞ ሽንፈት ነበር” ብለዋል።

እስራኤል ጉዳቱ ተሰምቷት ነበር። መስከረም 26 እስራኤል ጦሯን ወደ ጋዛ ድንበር አሰማራች። ቤንያሚን ኔታንያሁ “ከባድ የበቀል እርምጃ” እንደሚኖር ተናገሩ። የሐማስን ወታደራዊ እና የፖለቲካ ክንፍ በማስወገድ ታጋቾቹን ለመመለስ የሚያስችል የጦርነት ዕቅድ ነደፉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሁሉን ድል” መጎናጸፍ ይቻላል በማለት አጥብቀው መናገራቸውን ቀጥለዋል። ያ ኃይል በመጨረሻ በሐማስ ለአንድ ዓመት ተይዘው የነበሩትን እስራኤላውያን ነፃ ያወጣል።

የታጋቾቹ ዘመዶች እና የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸው ግን የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን መለቀቅ በመቃወም በመንግሥታቸው ውስጥ ያሉ ጽንፈኛ ብሔርተኞችን ለማስደሰት እየሠሩ ነው ሲሉ ይከሳሉ። ከእስራኤላውያን ሕይወት ይልቅ የራሳቸውን የፖለቲካ ህልውና ያሰቀድማሉም ይሏቸዋል።

ኔታንያሁ እስራኤል ውስጥ ብዙ የፖለቲካ ጠላቶች አሏቸው። ባለፉት ቀናት በሊባኖስ የፈጸሙት ጥቃት የደጋፊያቸውን ቁጥር በተወሰነ መልኩ ጠግኖታል። አወዛጋቢ ሆነውም ቆይተዋል። የጋዛው ጦርነት ግን ለአብዛኞቹ እስራኤላውያን አወዛጋቢ አይደለም። ከመስከረም 26 ወዲህ አብዛኛዎቹ እስራኤላውያን በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ ለሚደርሰው ስቃይ ልባቸውን አደንደነዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ጦርነቱ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን የጋዛ ሰርጥ “ሙሉ በሙሉ እንዲከበብ አዝዣለሁ” ብለዋል ።

“መብራት፤ ምግብ እና ነዳጅ አይኖርም። ሁሉም ነገር አይገባም… እኛ ከሰው እንስሳት ጋር እየተዋጋን በመሆኑ ተመሳሳይ ምላሽ እንሰጣለን።”

ከዚያን ወዲህ ግን በዓለም አቀፍ ጫና ምክንያት እስራኤል ክልከላዋን ለማላላት ተገድዳለች። በቅርቡ በተካሄደው በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ የተገኙት ኔታንያሁ፤ “ጋዛውያን የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ሁሉ አግኝተዋል” ብለዋል።

ማስረጃዎች ግን ይህንን አያሳዩም። ከጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት “በጋዛ ያለው አሰቃቂ የሰው ልጅ ስቃይ እና ሰብአዊ ጥፋት” እንዲያበቃ የሚጠይቅ መግለጫ ተፈራርመዋል።

“ከሁለት ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን እንደመጠለያ፣ ምግብ፣ ውሃ፣ ንጽህና መጠበቂያ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ኤሌክትሪክ እና ነዳጅ – ያሉ መሠረታዊ ፍላጎቶች የላቸውም። መውጫ በሌለበት ሁኔታ ሰዎች በተደጋጋሚ ጊዜ በግዳጅ ተፈናቅለዋል።”

በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስካሁን ወደ 42 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ብሏል። ኮሪ ሼር እና ጃሞን ቫን ዴን ሆክ የተባሉ የዩናይትድ ስቴትስ የትምህርት ተቋማት የሳተላይት ምሥሎች ደግሞ 58.7 በመቶ የሚሆኑት ሕንፃዎች ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል ብለዋል።

መፈናቀልም ደርሷል። ሲቪሎች በተደጋጋሚ ጊዜ በእስራኤል በመከላከያ ሠራዊት ከሰፈሩበት ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ታዘዋል።

የሰዎች እንቅስቃሴ ተጽዕኖም ከጠፈር ሊታይ ይችላል።

በማዕከላዊ ራፋህ የሚገኙ ድንኳኖች እንዴት እንደጨመሩ እና እንደቀነሱ የሳተላይት ምሥሎች ያሳያሉ። ይህን መሰሉ ሁኔታ በጋዛ ሰርጥ ተደጋግሞ ታይቷል።

እነዚህ የመፈናቀል ማዕበሎች የጀመሩት ጥቅምት 2/2016 ዓ.ም. ነው። በወቅቱ የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኙ ነዋሪዎች ለራሳቸው “ደኅንነት” ሲሉ ወደ ደቡብ እንዲሄዱ አዟቸዋል።

በጦሩ የተጋሩ ከ130 በላይ የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሁፎችን ቢቢሲ ቬሪፋይ ተመልክቷል። በዚህም የትኞቹ የውጊያ ቀጠናዎች እንደሆኑ፣ መውጫ መንገዶችን እና ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ያለባቸውን በዝርዝር ለይቷል።

በድምሩ ወደ 60 የሚጠጉ የመልቀቂያ ትዕዛዞች የወጡ ሲሆን፣ የጋዛ ሰርጥን ከ80 በመቶ በላይ ይሸፍናሉ።

በብዙዎቹ ማስጠንቀቂያዎች ላይ የማይነበቡ ቁልፍ ዝርዝሮች ነገሮች እና ከጽሑፉ ጋር የማይጣጣሙ ድንበሮች መቀመጣቸውን ቢቢሲ ቬሪፋይ ለይቷል።

የእስራኤል የመከላከያ ኃይል በደቡባዊ ጋዛ የሚገኘውን አል-ማዋሲ የባሕር ዳርቻን ሰብአዊ ቀጠና አድርጎ ሰይሟል። ነገር ግን ስፍራው ከቦምብ ድብደባ አላመለጠም። ቢቢሲ ቬሪፋይ በአካባቢው 18 የአየር ጥቃቶችን የሚያሳይ ምሥል ተንትኗል።

በድንገት ከሰመ ተስፋ

እስራኤል የሰሜን ጋዛ ሕዝብ አካባቢውን እንዲለቅ ካዘዘች በኋላ በሳላ አል-ዲን ጎዳና ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰዎች ጎርፍ እንደነበር የሳተላይት ምሥሎች አሳይተዋል። የሰሜን እና የደቡብ ጋዛ አውራ መንገድ በሆነው ሳላህ አልዲን ሲፈስ ከነበረው ሕዝብ መካከል አንዷ ኢንሳፍ ሐሰን አሊ ናት። ባለቤቷ እና ሁለት ልጆቿም አብረዋት ነበሩ። ከብዙ ቤተሰቦች በተለየ ሁኔታ ሁሉም በሕይወት ተርፈዋል።

እስራኤል ጋዛ ውስጥ ጋዜጠኞች በነፃነት ተንቀሳቅሰው እንዲዘግቡ አትፈቅድም። በጋዛ የሚገኝ ታማኝ የሆነ ፍልስጤማዊ ወገንተኛ ያልሆነ ጋዜጠኛ ኢንሳፍ አሊን እና ልጇን ቃለ መጠይቅ እንዲያደርግልን አድርገናል።

በእስራኤል ጦር በተሰጠ ትዕዛዝ ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች ጋር ወደ ደቡብ ጋዛ ሲሄዱ ስላጋጠማቸው አስፈሪ ሁኔታ አስከሬን በየቦታው ነበር በማለት ትገልጻለች።

“በሳላህ አል-ዲን ጎዳና ላይ እየተጓዝን ነበር። ከፊት ለፊታችን የነበረ መኪና ተመታ። እየነደደ ነበር … በመኪናው በግራ በኩል ሰዎች ተገድለዋል። በቀኝ በኩል ደግሞ እንስሳት እንኳን ሳይቀሩ በቦምብ ተመትተዋል።

“በቃ አለቀልን። ቀጣዩ ሮኬት ለእኛ ነው አልን።”

ኢንሳፍ እና ቤተሰቧ ከጦርነቱ በፊት መካከለኛ የሚባል ኑሮ ነበረው። ከዚያን ወዲህ በእስራኤል ትዕዛዝ 15 ጊዜ ተፈናቅለዋል። ልክ እንደሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጋዛዊያን ተቸግረዋል፣ ብዙ ጊዜ ተርበዋል፣ በአል-ማዋሲ አሸዋ ላይ በድንኳን ውስጥ ኖረዋል።

እባቦች፣ ጊንጦች እና መርዛማ ትሎች ድንኳኖቹን ሲወሩም መውጣት ነበረባቸው። በአየር ድብደባ ከሞት የተረፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ንጽህና በሌለው አካባቢ ከረሃብ፣ ከበሽታ እና ከአቧራ ጋር ይጋፈጣሉ።

ኢንሳፍ ስላለፈው ሕይወቷ እና ስላጣቻቸው ሰዎች እያሰበች አለቀሰች።

“ሕይወታችን ቆንጆ ነበር፣ በድንገት ግን ሁሉም ነገር ከሰመ። ልብስ፣ ምግብ የለንም። ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች አልነበረንም። ያለማቋረጥ የሚደረገው መፈናቀል በልጆቼ ጤና ላይ ከባድ ጉዳት አደረሰ። የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና ታማሚ ሆኑ።”

የእስራኤል የቦምብ ጥቃት የጀመረችበት የመጀመሪያዎቹ ወራት “በጣም አስፈሪ” ሆኖ ተሰምቷቸዋል እንነበር ኢንሳፍ ገልጻለች።

“ማንኛዋም እናት ተመሳሳይ ነገር ይሰማታል። ውድ የሆነ ነገር ያለው እና በማንኛውም ጊዜ ከእጄ ሊወጣ ይችላል ብሎ የሚፈራ ማንኛውም ሰው ይህንኑ ያስባል። ወደ ቤት በሄድን ቁጥር በቦምብ ይደበድባል። ከቤተሰባችን አንድ ሰው ይገደላል።”

ኢንሳፍ እና ቤተሰቦቿን ጨምሮ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ጋዛዊያን ሕይወታቸው ትንሽም ቢሆን ሊሻሻል የሚችለው የተኩስ አቁም ስምምነትን ከተደረሰ ነው። ግድያው ከቆመ ዲፕሎማቶች ወደ ሰፊው ጥፋት የሚደረገውን ጉዞ ለማስቆም ዕድል ሊኖራቸው ይችላል።

ጦርነቱ እየገፋ ከሄደ እና አዲሱ የእስራኤላውያን እና የፍልስጤማውያን ትውልድ አሁን አንዱ ስለሌላው ወገን የሚሰማውን ጥላቻ እና ጭካኔ ማስቀረት ካልቻለ ብዙ አደጋዎች ወደፊት ይመጣሉ።

የኢንሳፍ የ11 ዓመት ልጅ የሆነው አናስ አዋድ ባየው ነገር ክፉኛ ተጎድቷል።

“ለጋዛ ልጆች ምንም ተስፋ የለም። አብሬያቸው የተጫወትኳቸው ጓደኞቼ ሰማዕትነት ከፍለዋል። አብረን እንጫወት ነበር። ፈጣሪ ምህረቱን ይስጣቸው። ቁርአን የምቀራበት መስጂድ በቦምብ ተደብድቧል። ትምህርት ቤቴ ተደብድቧል። የመጫወቻ ሜዳው… ሁሉም ነገር ፈራርሷል። ሠላም እፈልጋለሁ። ከጓደኞቼ ጋር ተመልሼ መጫወትን እመኛለሁ። ድንኳን ሳይሆን ቤት ቢኖረን እመኛለሁ።

“አሁን ጓደኞች የሉኝም። ሕይወታችን በሙሉ ወደ አሸዋነት ተቀይሯል። ወደ ጸሎቱ ስፍራ ስሄድ ጭንቀት እና ማመንታት ይሰማኛል። ሁሉም ነገር ትክክል አይመስለኝም” ብሏል።

እናቱ እየሰማችው ነበር።

“የሕይወቴ በጣም አስቸጋሪው ዓመት ነው። የተበታተኑ አስከሬኖችን ጨምሮ ማየት የማይገባቸውን ዕይታዎች አይተዋል። እርግጥ ነው ቤቶቻችን አሁን ክምር አሸዋ ሆነዋል። ሆኖም ግን የምንመለስበትን ቀን ተስፋ እናደርጋለን።”

ሕጉ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት እስራኤልን እና ሐማስን አውግዘዋል። “ሁለቱም አካላት ባለፈው አንድ ዓመት ያደረጉት ድርጊት ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግን እና እናከብራቸዋለን የሚሉትን ዝቅተኛውን የሰብዓዊነት መመዘኛዎች እንዳፌዙበት ይቆጠራል” ብለዋል።

ሁለቱም ወገኖች የጦርነትን ሕግ ጥሰዋል የሚለውን ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል። ሐማስ ጦሩ የእስራኤልን ሲቪሎች እንዳይገድሉ ትዕዛዝ ማስተላለፉን አስታውቋል። እስራኤል በበኩሏ ፍልስጤማውያን ሲቪሎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከመኖያቸው እንዲወጡ ማስጠንቋን እና ሐማስ ግን እንደ ሰብአዊ ጋሻ እንደተጠቀመባቸው ገልጻለች።

በደቡብ አፍሪካ የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ የተመሠረተባት እስራኤል ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቀርባለች። የፍርድ ቤቱ ዋና ዐቃቤ ሕግ በተለያዩ የጦር ወንጀሎች ምክንያት ለሐማሱ ያህያ ሲንዋር እና ለእስራኤሎቹ ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ዮአቭ ጋላንት የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ጠይቋል።

ወደ ማይገመት አቅጣጫ ማምራት

የመስከረም 26ቱ ጥቃት በአውሮፓ በአይሁዶች ላይ የተፈጸሙ የዘመናት አሰቃቂ ድርጊቶች እና በናዚ ጀርመን የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስታውስ ነው። በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ እስራኤላዊው ፀሐፊ እና የቀድሞ ፖለቲከኛ አቭራሃም በርግ ጥቃቱ በአገሩ ላይ ያለውን ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ተጽዕኖ ገልጾታል።

“እኛ አይሁዶች የእስራኤል መንግሥት ከአይሁዶች ታሪክ አንፃር የመጀመሪያው እና ምርጡ የአደጋ መከላከያ ሥርዓታችን እንደሆነ እናምናለን። ከዚህ በኋላ የዘር ማጥፋት፣ እልቂት እና ጅምላ ጭፍጨፋ የለም። በድንገት ግን ሁሉም ነገር ተመልሶ መጥቷል።”

ያለፈው መንፈስ ፍልስጤማውያንንም አሰቃይቷል። ታዋቂው የፍልስጤም ፀሐፊ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ራጃ ሸሃዴህ እስራኤል ሌላ ናክቅ (ጥፋት) ለመፈጸም እንደምትፈልግ ያምናሉ።

“ዋት ዳዝ ኢዝራኤል ፊር ፈሮም ፓለስታይን?” በሚለው መጽሐፋቸው “ጦርነቱ እየገፋ ሲሄድ እያንዳንዱን ቃል ከልባቸው ማለታቸውን እና ህጻናትን ጨምሮ ስለሲቪሎች ደንታ እንደሌላቸው ለማየት ችያለሁ። በእነሱም ሆነ በአብዛኞቹ እስራኤላውያን ዓይን ሁሉም ጋዛውያን ጥፋተኞች ነበሩ” ብለዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ እስራኤል ሕዝቦቿን ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት ማንም ሊጠራጠር አይችልም። ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደራዊ ወረራ ስር ለዘላለም ያለ መብት መኖርን ይመርጣሉ ብሎ ማንም ሰው ራሱን የሚያሞኝም አይኖርም።

ከበርካታ ትውልዶች ግጭት በኋላም እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን እርስ በእርስ መጋጨትን ለምደዋል። አብሮ መኖርንም ለምደውታል። የተኩስ አቁም ሲደረስ እና የአዲሱ ትውልድ መሪዎች ሲመጡ እንደገና ወደ ሠላም የመሄድ ዕድሎች ይኖራሉ።

ይህ ግን በቅርቡ የሚሆን አይመስልም። በቀሪዎቹ ወራትም ሆነ በአውሮፓውያኑ 2025 አዲስ ፕሬዝዳንት ወደ ዋይት ሐውስ ከገባ በኋላም እርግጠኝነት የለም።

ሐማስ እስራኤልን ካጠቃ በኋላ ለወራት የነበረው ፍርሃት ጦርነቱ ሊስፋፋ እና ሊባባስ ይችላል የሚለው ነው። እስራኤል በሄዝቦላህ እና በሊባኖስ ላይ ያደረሰችውን አውዳሚ ጥቃት ተከትሎ የተፈራው በፍጥነት ደረሰ።

መካከለኛው ምሥራቅ በጦርነት አፋፍ ላይ ነው ለማለት ጊዜው ዘግይቷል። እስራኤል ከኢራን ጋር ተፋጣለች። ተፋላሚ ወገኖቹ ቢገቡበትም እስካሁን በቀጥታ ያልተሳተፉ አገራት ወደ ጦርነት ላለመግባት ይፈልጋሉ።

እስራኤል ከቀናት በፊት ኢራን ለሰነዘረችባት የባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት አሁንም የአጸፋ ምላሽ አልሰጠችም። ምላሹ ጠንከር ያለ እንደሚሆን ተጠቁሟል። ፕሬዝዳንት ባይደን እና አስተዳደራቸው ከኢራን ጋር ወደለየለት ጦርነት እንዳይገባ የሚያስችል መንገድ ለመጠቆም እየሞከሩ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት ጆ ባይደን እና አስተዳደራቸው ለእስራኤል የሚሰጡትን ድጋፍ እየጨመሩ ቢሆንም የመውጫ መንገዱን ያስተካክላሉ የሚል ተስፋ የለም።

ከእስራኤል የሚወጡት ምልክቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ኔታንያሁ፣ ጋላንት፣ የመከላከያ ኃይሉ ጄኔራሎች እና የስለላ ተቋማቱ የበላይ እንደሆኑ ያምናሉ። ነገር ግን መስከረም 26 ለሁሉም ኪሳራ ያስከተለ ነበር። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በስተቀር ሁሉም ዋና ዋና የደኅንነት እና የጦር አዛዦች ይቅርታ ጠይቀዋል፤ የተወሰኑትም ከሥልጣናቸው ተነስተዋል።

ከሐማስ ጋር ጦርነት ለመግጠም አላሰቡም ነበር። ከሂዝቦላህ ጋር የሚደረገውን ጦርነት ማቀድ የጀመሩት በአውሮፓውያኑ 2006 ያደረጉት የመጨረሻው ጦርነት በአሳፋሪ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው። ሄዝቦላህ ፈጽሞ ሊያገግም በማይችልበት መልኩ ድብደባ ደርሶበታል።

እስካሁን የተመዘገቡት የእስራኤል ድሎች ታክቲካዊ ናቸው። ወደ ስትራቴጂካዊ ድል ለመድረስ ጠላቶቿን በማስገደድ ባህሪያቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ ትፈልጋለች። ሄዝቦላህ በተዳከመበት ሁኔታም ቢሆን መዋጋት እንደሚፈልግ እያሳየ ነው። በደቡብ ሊባኖስ ያደረገችው የምድር ጦር ወረራ እስራኤል በአየር ኃይል እና በስለላ ያላትን የበላይነት ሊያስቀረው ይችላል።

ኢራን ለእስራኤል አጸፋ በሌላ የባለስቲክ ሚሳዔሎች ምላሽ ከሰጠች ሌሎች አገራት ወደ ጦርነቱ ሊገቡ ይችላሉ። በኢራቅ የሚገኙ የኢራን አጋሮች የአሜሪካን ካምፖችን ሊያጠቁ ይችላሉ። ከኢራቅ በመጣ ሰው አልባ አውሮፕላን ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።

ሳዑዲ አረቢያም ጉዳዩን በስጋት እየተከታተለች ነው። ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ስለወደፊቱ ያላቸውን አመለካከት በግልጽ አስቀምጠዋል። ለእስራኤል እውቅና ለመስጠት ቢያስቡም ይህ የሚሆነው ፍልስጤማውያን ዕውቅና ካገኙ እና ሳዑዲ አረቢያ ከአሜሪካ የፀጥታ ድጋፍ ካገኘች ብቻ ነው።

እስራኤል በሐሳን ናስራላህ ላይ የፈጸመችው ግድያ እና በኢራን ላይ የደረሰው ስትራቴጂካዊ ጉዳት እና “የአክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስን” ምሥል ይበልጥ እየገለጠው ነው። የመካከለኛው ምሥራቅን በኃይል መቅረጽ የሚቻል ከሆነ ሥርዓትን ለማስፈን እና የእስራኤልን ጠላቶች ለማጥፋት ይህ በትውልድ አንድ ጊዜ የሚገኝ ዕድል ነው።

መካከለኛው ምሥራቅን በኃይል ለማስተካከል ለመጨረሻ ጊዜ የተሞከረው አልቃይዳ በአውሮፓውያኑ መስከረም 2001 በአሜሪካ ላይ ካደረሰው ጥቃት በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እና የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር በ2003 ኢራቅን ለመውረር ሲዘጋጁ ነበር።

የኢራቅ ወረራ መካከለኛው ምሥራቅን ከጽንፈኝነት አላጸዳም። ይልቁንም ሁኔታውን የበለጠ የከፋ አደረገው።

ይህንን ጦርነት ለማስቆም ለሚፈልጉ ሰዎች ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በጋዛ የተኩስ አቁም ማድረግ መሆን አለበት። ይህም ነገሮችን ለማቀዝቀዝ እና ለዲፕሎማሲ ዕድል ለመስጠት ብቸኛው መንገድ ነው። በጋዛ የተጀመረው ጦርነትም ማብቂያውም እዚያው ሊሆን ይችላል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)