ሐማስ እንዴት የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ለሰዓታት የዕዝ ጣቢያዋን መቆጣጠር ቻለ?

ሐማስ በእስራኤል ይዞታ ላይ ጥቃት አድርሶ ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ ሰዎችን የገደለበት ዕለት አንድ ዓመት ሞላው።

እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከ41ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ገድላለች። ከእነዚህ ውስጥ 16ሺህ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው።

ያቺ ክፉ ቀን በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 (መስከረም 26/2026 ዓ.ም.) ቅዳሜ ቀን ነበር የዋለችው።

ሐማስ እንዴት በጥብቅ የሚጠበቀውን የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ገብቶ ያን የመሰለ መብረቃዊ ጥቃት ሊያደርስ ቻለ? ዛሬም ድረስ ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።

ቢቢሲ በዚያች ዕለት ከጋዛ ጋር በምትዋሰን የእስኤራል ወታደራዊ ቀጠና ምን እንደሆነ ያዩ ሰዎችን አነጋግሯል።

የድንበሩ የዕዝ ጣቢያ ‘ናሓል ኦዚ’ ተብሎ ይጠራል።

በዚያች ዕለት ማለዳ የሐማስ ወታደሮች ይህን ወታደራዊ ጣቢያ ተቆጣጠሩት። 60 የእስራኤል ወታደሮቸን ገደሉ። ሌሎቹን ደግሞ አፍነው ወሰዱ።

የእስራኤል መከላከያ እስከ አሁን በዚያች ዕለት ማለዳ ስለሆነው ነገር የተብራራ ምርመራ አድርጎ የተብራራ መግለጫ አላወጣም።

ቢቢሲ ይህን መረጃ ያገኘው ቤተሰብ የተገደሉባቸው ሰዎች ከተሰጣቸው ማብራሪያ በመነሳት ነው።

በዕለቱ እዚያ የነበሩ፣ ነገር ግን ከሞትም ከእገታም በተአምር ያመለጡ ሰዎችን አነጋግሯል።

ከዚህ በተጨማሪ ጥቃቱ ሲካሄድ ከመገደላቸው በፊት የድምጽ መልዕክት የተዉ ዜጎችን እና ወታደሮችን ለማካተት ተሞክሯል።

እነዚህን መረጃዎች ቀጣጥሎ በመስፋት ቢቢሲ የሚከተለውን ውጤት አግኝቷል፦

  • ከመስከረም 26 በፊት አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች በዚያ የጦር ጣቢያ የነበሩ የእስራአል ወታደሮች ተመልክተው ሪፖርት ቢያደርጉም ቸል ተብሏል።
  • የካሜራ እንቅስቃሴዎችን የምትከታተለው ሴት ወታደር ብቻ ሳትሆን ሌሎች ወታደሮችም አጠራጣሪዎቹን እንቅስቃሴዎች ቀደም ብለው መመልከታቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል።
  • ከጥቃቱ ዕለት በፊት በነበሩ ጥቂት ቀናት ሐማስ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎቹን ድንገት ማቆሙን ወታደሮች መስክረዋል። ይህም ግራ መጋባትን ፈጥሮ ነበር።
  • በድንበር አካባቢ የነበሩ ብዙዎቹ የእስራኤል ወታደሮች አልታጠቁም ነበር።
  • ብዙዎቹ የቅኝት መሣሪያዎች አይሠሩም ነበር ወይም በሐማስ እንዳይሠሩ ተደርገዋል።
  • አንዱ የሚነሳው ጥያቄ ለምን በድንበር አካባቢ ባለ የጦር ጣቢያ ወታደሮች እንዳይታጠቁ ሆኑ የሚል ነው። አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሪፖርት ቢደረጉም ቸል ሊባሉ እንዴት ቻሉ? አጋዥ ኃይል እስኪመጣ ድረስ ለምን ረዥም ሰዓት ወሰደ?

ከሌሊቱ 10፡ 00 ሰዓት

ሻሮን በዚያች ዕለት በናሃል ኦዚ የጦር ማዘዣ ጣቢያ ፈረቃዋን ጀመረች። ጣቢያው ከጋዛ ድንበር በአንድ ኪሎ ሜትር ይርቃል።

ሻሮን የቀጠናው ሙሉ ሴቶች ብቻ ያሉበት የወታደሮች ቡድን አባል ናት። የእነዚህ ሴቶች ሥራ ቀጥታ በካሜራ በድንበር አካባቢ ያሉ እንቅስቃሴዎችን መከታተል እና መተንተን ነው።

የእነዚህ ሴቶች ሥራ በፈረቃ ሲሆን፣ 24 ሰዓት ሙሉ የካሜራ ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በዚያች ማለዳ አንዳቸውም አልታጠቁም ነበር።

ጄኔራል ኢዝራኢል ዚቭ የቀድሞ የእስራኤል መከላከያ አባል ነው። ለቢቢሲ እንደሚናገረው፣ ድንበር አካባቢ ወታደር ያለ መሣሪያ ትጥቅ ታይቶ እና ተሰምቶ አያውቅም።

የሐማስ ወታደሮች ሁልጊዜም ከድንበር ማዶ ይንቀሳቀሳሉ። ከዚያች ዕለት ቀደም ብሎ በነበሩ ጥቂት ቀናት ግን ሁሉም ነገር ፀጥ አለ።

“በጣም አስፈሪ ነበር ፀጥታው። ምንም እንቅስቃሴ ማየት አቆምን” ይላል በወቅቱ የነበረ አንድ ወታደር። “የሆነ ልክ ያልሆነ ነገር ያለ ይመስል ነበር፣ ድንበሩ እንዲህ ፀጥ ረጭ ሊል አይችልማ።”

የቀድሞ የእስራኤል ወታደራዊ መኮንን ግን እነዚህ ግራ የሚያጋቡ ምልክቶች ቸል የተባሉት የእስራኤል መከላከያ ሐማስን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚንቀው ነው።

“ንቀት ነው ጉድ የሠራቸው። ሐማስ ጥቃት ለማድረስ አይደፍርም፤ ማድረስ ቢፈልግም አቅም የለውም” የሚል ከፍተኛ ንቀት የነበረ ይመስለኛል” ይላል።

ነገሩን በአጭር ሲገልጽ እንዲህ ይላል “በመስከረም 25 ማታ [የጥቃቱ ዕለት ዋዜማ] ወዲያ ማዶ ድመት አለች ብለን ተኛን። መስከረም 26 ስንነቃ ግን ነብር ሆና ጠበቀችን።”

ከንጋቱ 11፡30

ጎላኒ የምትባለው የእስራኤል ወታደራዊ ቡድን አባላት በጂፕ መኪና ቅኝት ለማድረግ ተዘጋጁ፤ ድንበር አካባቢ።

ይህ ሁልጊዜ ጎህ ከመቅደዱ በፊት የሚደረግ የድንበር ጠባቂ ወታደር አታካች ሥራ ነው። ያን ዕለትም ይህንኑ ነበር ያደረጉት።

ድንገት ፀረ ታንክ ሚሳኤል ስጋት መኖሩ ተነገረ። ስለዚህ የስላለ ቅኝቱ ይቅር ተባለ።

ሺሞን ማልካ የ21 ዓመት ወታደር ስትሆን የዚች ጋንታ አባል ናት። ቅኝት ማድረግ የተለመደ ነው ግን ደግሞ ስጋት አለ ዛሬ ይቅር መባልም አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ነው ትላለች።

ጄኔራል ዚፍም በዚህ ይስማማል። የፀረ ታንክ ሚሳኤል ስጋት ካለ ወታደሮች እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ያለ ነገር ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ነገር ግን ሐማስ ይህን በመረዳቱ ዕድሉን ተጠቀመበት”

የጎላኒ ቡድን አባላት በዚያው ባሉበት እንዲረጉ ከተነገራቸው በኋላ ሻሮን በካሜራ የሐማስን እንቅስቃሴዎች ተመለከተች። ነገር ግን ሁሌም የሚያደርጉት ነገር ስለሆነ ብዙም ትኩረት አልሰጠችውም።

“እነሱም በፈረቃ ስለሚቀያየሩ የፈረቃ ልውውጥ ነበር የመሰለኝ” ትላለች።

ከማለዳው 12፡ 20

ሐማስ ድንገት ሮኬት መተኮስ ጀመረ። ነገር ግን ሻሮን እንደምትለው ይህ ነገር በጣም ያልተመለደ አይደለም። ሐማስ ሁልጊዜም ሮኬት ይተኩሳል። ያ ማዘዣ ጣቢያ ደግሞ ከሮኬት ጥቃት መሸሸጊያ አለው።

“በተመልዶ 5 ደቂቃ ይተኩሱና ይቆማል። ያን ዕለት ግን ለምን እንደሆነ አላውቅም አላባራም” ትላለች።

ከማለዳው 12፡30

ሻሮን በዚህች ደቂቃ የሐማስ ወታደሮች ወደ ድንበሩ ሲጠጉ በካሜራ ተመለከተች። በራዲዮ ይህንኑ መልዕክት አስተላለፈች።

“ለሁሉም ጣቢያ ተረኞች፣ አራት የሐማስ ወታደሮች ወደ አጥሩ እየተጠጉ ነው፤ ኮፒ ” ብላ ዘጋችው – የራዲዮ መገናኛዋን።

ሌላኛዋ የሴቶች ቡድን አባል ሮኒ ኤሼል፣ ድምጽዋ ይቆራረጣል፤ እንዲህ ስትል መለሰች፣ “ሁለት የታጠቁ ሰዎች ወደ ድንበር በሩጫ እየተጠጉ ነው – እደግመዋለሁ ሁለት የታጠቁ. . . ”

ከማለዳው 6፡40

በናሃል ኦዝ ማዘዣ ጣቢያ ሮኬት ፍንዳታ ደረሰበት።

አንድ የእስራኤል ወታደር ከሐማል ጣቢያ በስናይፐር የሐማስ ወታደርን ለመግደል ሞከረ። አልሰመረም።

ወደ ሐማል ጣቢያ በፒጃማ ጭምር የደረሱ የእስራኤል ወታደሮች ነበሩ። ሆኖም ዘግይተዋል።

አንድ የሐማስ ታጣቂ የቅኝት ካሜራዎች ላይ አከታትሎ ተኮሰ። በዚህን ጊዜ ሐማል የሚገኘው የካሜራ ሲስተም ጨለመ።

ይህ ማለት ስለሚሆነው ነገር የእስራኤል ወታደሮች ማየት አይችሉም።

በናሃል ኦዚ ጣቢያ ፊኛ የመሰለ የቅኝት መሣሪያ አለ። ብልሽት ገጠመው። ነገር ግን ማንም ግድ አልሰጠውም። ነገ እሑድ ይሠራል ተብሎ ተተወ።

ይህ ሐማስን ከመናቅ የመጣ እንደሆነ ጄኔራሉ ይናገራሉ።

በድንበር የቅኝት ጣቢያ ሻሮን ትጮኻለች። ድምጽዋ እንደማልቀስም እያደረገው ነው።

አለቃችን ዝም እንድንል ተቆጣን። ምክንያቱም መጯጯህ ስለነበረ ትላለች።

በዚያው ቅጽበት የሐማስ ታጣቂዎች በወታደሮቹ ላይ መተኮስ ጀመሩ።

ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት

ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ልክ ጠዋት 1፡00 ሰዓት ማንም ያላሰበው ነገር ተከሰተ።

የሐማስ ታጣቂዎች በሐማል የዕዝ ጣቢያ ደረሱ።

“ተነሺ፤ አሸባሪዎቹ ደጅ ናቸው” ሻሮን የተባለችውን ታስታውሳለች።

የቅኝት ሴት ወታደሮች ቶሎ ይዞታቸውን ትተው ወደ ቢሮው እንዲመለሱ ተነገራቸው።

ከጠዋቱ 1፡20

ሐማል በጣቢያው የሚገኝ ወታደራዊ ሳሎን ነው። ፍንዳታን መቋቋም የሚችል በር ያለው፣ መስኮት አልባ የቅኝት ስክሪኖች የተደረደሩበት ክፍል ነው።

ልክ 1፡20 ሲሆን የሐማል ክፍል የቦምብ መሸሸጊያ ጥቃት ደረሰበት።

በዚያች ክፍል አራት የእስራኤል የቅኝት ባልደረባ የሆኑ ሴቶች ተሸሽገው ነበር። መሣሪያም ታጥቀው ነበር። የሚችሉትን ያህል ሐማሶች ላይ ተኮሱ።

ከእነርሱ በቅርብ ርቀት የነበሩ 10 ወታደሮች መሸሽ ቻሉ። ከሸሹት ሌላ ግን ሁሉም በሐማስ ተገደሉ። የተወሰኑት ደግሞ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

በዚህ ቅጽበት ከጋዛ ድንበር ብዙ ተዋጊዎች ወደ እስራኤል ድንበር እየተሻገሩ ነበር።

በዚህ ጊዜ ሻሮን እንደምታስታውሰው ተሸሽገው ከነበሩት ውስጥ ድጋፍ እንዲደርስላቸው በተደጋጋሚ መልዕክት እየላኩ ነበር።

አንዲያውም አለቃዬ “የምንፈልገው የሚያድነን እንጂ ተጨማሪ ኃይል አይደለም” እያለ ሲጮኽ ሰምቼዋለሁ ትላለች።

ይህም የጥቃቱ መጠን ከፍተኛ መሆኑን ከመረዳት የመጣ ነው።

ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት

ዚክ የሚባለው የእስራኤል ድሮን ደረሰ። ነገር ግን ማን ሐማስ ማን የእስራኤል ወገን እንደሆነ ለመለየት ተቸገረ።

ይህም ጥቃቱን አዘገየው።

ይህ በእንዲህ ሳለ ሐማስ ሐማል ጣቢያ ላይ የተኩስ እሩምታ ከፈተ። የታጠቁት የእስራኤል ወታደሮች የአጸፋ ተኩስ ከፈቱ። ጥረታቸው ሐማስ ወደ ክፍሉ ዘልቆ እንዳይገባ ለማድረግ ነው።

ይህ የተኩስ ልውውጡ ለአራት ሰዓታት ዘለቀ።

ነገር ግን የሐማስ ወታደሮች ቁጥር ከእስራኤሎቹ የላቀ ነበር።

ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት

የጎላኒ ቡድን አባላት ምግብ መግቢያ ክፍል ገብተው ተደበቁ።

የቁጥር አለመመጣጠን ነበር። ለ25 የእስራኤል ወታደሮች 150 የሐማስ ወታደሮች ይደርስ ነበር።

ጄኔራል ዚቭ እንዲህ ይላሉ። “ሐማስ ጥራት እንደሌለው ያውቃል፤ ስለዚህ ብዛት ላይ አተኩሮ ነው የመጣው።”

የ19 ዓመቷ ናዓማ ሌቪ ያን ቀን ገና በዚያ ማዘዣ ለመገኘት ገና ሁለተኛ ቀኗ ነበር።

ሐማሶች ያዟት። በቪዲዮ በተቀረጸው ቅጽበት “በፍልስጤም ጓደኞች አሉኝ” እያለች ስትለምናቸው፤ ፊቷ በደም ተሸፍኖ ይታያል።

ከዚህ በኋላ የሐማስ ወታደሮች እየጎተቱ መኪና ላይ ሲጭኗትም ይታያል።

ይህ ቪዲዮ በተለይ ለናአማ እናት የሚረሳ አይደለም።

“ቁስሏ፣ ፊቷ ላይ የነበረው ደም፣ የምትለምናቸው ነገር ሁሉም የሚረብሽ ነው ትላለች” እናት ዶክተር አይለት ሌቪ።

ከረፋዱ 5፡00

ሐማል የተሰኘው መሸሸጊያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ ተቋረጠ።

ይህ ማለት በኤሌክትሪክ ሲስተም የሚሠራው በር ለሐማስ ታጣቂዎች ክፍት ሆነ ማለት ነው።

የሐማስ ታጣቂዎች ዕድሉን ተጠቀሙበት። ወደ ሐማል መሸሸጊያ ክፍል የተኩስ እሩምታ ከፈቱ። የእጅ ቦምብ ወረወሩ።

ጄኔራል ዚቭ እንደሚሉት ያን ጊዜ የድንበር ወታደሮቹ ብቸኛ መሸሸጊያቸው ሐማል መደበቂያ ነበር። አሁን ግን ሲስተሙ በሙሉ ፈራረሰ እና ለአደጋ ተጋለጡ።

የእስራኤል መከላከያ ለሟች ቤተሰቦች እንዳመነው “አሸባሪዎቹ ተቀጣጣይ ነገር ወደ ሐማል ወርውረው እሳት አስነሱ።”

ቀትር፡ 6፡30

ሐማል መደበቂያ ክፍል ውስጥ የነበሩት ሻሮን እና ሰባት ባልደረቦቿ በሽንት ቤት መስኮት በኩል አመለጡ።

ከዚያ ድምጻቸውን አጥፍተው ሌሎች ባልደቦቻቸው እስኪወጡ ጠበቁ። ማንም ብቅ አላለም።

ሻሮን በዚያ የቅኝት ቡድን ውስጥ ከነበሩ ተረኞች የተረፈች ብቸኛዋ ሴት ሆነች።

ከእርሷ ሌላ የተረፉት በዚያ ቀን ፈረቃቸው ሆነው ያልመጡ ሴቶች ናቸው።

ከቀኑ 7፡00 ሰዓት

የእስራኤል ወታደሮች አካባቢውን ተቆጣጠሩ።

ሟች እና ቁስለኛ መቆጠር ተጀመረ።

ሐማስ 1200 ሰዎችን ገደለ። ከእነዚህ መካከል 300 የሚሆኑት ወታደሮች ናቸው።

251 ሰዎችን ደግሞ ታጣቂዎቹ አግተው ወደ ጋዛ ወሰዱ።

እስራኤል የበቀል እርምጃዋ ዛሬም አላባራም። ባለፉት 12 ወራት 41ሺህ ፍልስጤማውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ የሐማስ ወታደሮች እንደሆኑ ማንም ተጨባጭ መረጃ የለውም።

እስከ ዛሬ ያልተመለሰ ሌላም ጥያቄ አለ። እንዴት የሐማስ ወታደሮች አይደፈሬ የሚባለውን የእስራኤል ድንበር ጥሰው መግባት ቻሉ? ከገቡስ በኋላ ለዚህ ሁሉ ሰዓት ጥቃት ሲሰነዝሩ የእስራኤል መከላከያ የት ነበር?

ለዚሁ ሁሉ ተጠያቂውስ ማን ነው?

ለዚህ ሁሉ ቀውስ መቋጫ ይኖረው ይሆን? ወይስ ያቺ ቅዳሜ የ3ኛው ዓለም ጦርነት መነሻ ትሆን ይሆን?

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)