ለ67 ቀናት በሩሲያ ባሕር ጀልባ ላይ ሲንሳፈፍ የቆየው ግለሰብ በሕይወት ተገኘ

አንድ ሩሲያዊ ከሁለት ወር በላይ ኦኾትስክ በተባለው የምስራቅ ሩሲያ ባሕር ጀልባ ላይ ሲንሳፈፍ ከቆየ በኋላ በሕይወት መትረፍ ችሏል።

የሩሲያ ባለስልጣናት እንዳሉት ሚካኤል ፒቹጊን የተባለው የ46 ዓመት ግለሰብ የተገኘው በዓሳ አጥማጅ ቡድኖች አሰሳ ሲሆን አብረውት የነበሩት ሁለት ቤተሰቦቹ ግን ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተነግሯል።

ግለሰቡ ከመነሻው አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተገኘ ሲሆን፣ ከቤቱ የወጣው በነሐሴ ወር መጀመሪያ አካባቢ ነበር ተብሏል።

ግለሰቡ በሕይወት ሲገኝ አብረውት የነበሩት ወንድሙ እና የ15 ዓመት የወንድሙ ልጅ አስከሬንም ተሳፍረውባት ከነበረችው አነስተኛ ጀልባ አንድ ላይ መገኘቱ ተገልጿል።

የፒቹጊን ባለቤት እንደተናገረችው ሦስቱ ግለሰቦች ወደ ውቅያኖሱ ያመሩት ዓሳ ነባሪ ለመመልከት ሲሆን ቢያንስ ለሦስት ሳምንት የሚሆን ስንቅ ይዘው እንደነበር ገልጻለች።

ባለቤቱ እንደምትለው በሕይወት ለመትረፉ ምናልባት የባሏ የሰውነት ግዝፈት አስተዋጽዖ አድርጎ ሊሆን ይችላል።

ወደ ጉዞው ከመሄዱ በፊት ፒቹጊን 100 ኪሎ ግራም የሚመዝን ክብደት የነበረው ሲሆን ከ67 ቀናት የባሕር ላይ ቆይታ በኋላ ሲመለስ ግን ከግማሽ በላይ ቀንሷል።

“እስካሁን ምን እንደተፈጠረ ያወቅነው ነገር የለም። የተረዳነው በሕይወት መትረፉን ብቻ ነው። ተዓምር የሚመስል ነገር ነው” ብላለች ባለቤቱ ለሩሲያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን።

በዚሁ ጉዞ ከሦስቱ ሰዎች በተጨማሪ የፒቹጊን ሴት ልጃቸውም ለመካተት አቅዳ አንደነበር ባለቤቱ የገለጸች ሲሆን፣ ነገር ግን ሃሳቧን ቀይራ ከጉዞው ቀርታለች።

የግለሰቦቹ መጥፋት ከተነገረ ጊዜ ጀምሮ መንግሥት በሄሊኮፍተር የታገዘ አሰሳ ሲያካሂድ ቆይቷል።

ቢሆንም ምንም ፍንጭ የሚሆን ነገር አልተገኘም ነበር። ነገር ግን ባለፈው ሰኞ፣ ጥቅም 4/ 2017 ዓ.ም ዓሳ አጥማጆች በሚንቀሳቀሱበት ኦኾትስክ ባሕር ላይ ሦስቱን ሰዎች የጫነችው ጀልባ እየተንሳፈፈች ተገኘች።

ወዲያውኑ ፒቹጊን ዓሳ አጥማጆቹን ተመልክቶ እባካችሁ እርዱኝ የሚል ድምጽ አሰማቸው።

በዚህ ጊዜ ከ46 ዓመቱ ሚካኤል ፒቹጊን በተጨማሪ የ49 ዓመቱ ወንድሙ ሰርጌይ እና የወንድሙ ልጅ አስክሬን አብሮት ጀልባ ውስጥ ነበር።

የፒቹጊኒ መትረፍ ተዓምር የሚያሰኝ መሆኑን እማኞች ተናግረዋል። ምክንያቱም እጅግ የሚቀዘቅዘው የምስራቅ ሩሲያ ባሕር ከምግብ እጥረት ጋር ተዳምሮ ይህንን ያክል ጊዜ ሰዉ በሕይወት ይቆይበታል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም።

አካባቢውን የሚያውቁት ሰዎች እንደሚሉት ምናልባት ፒቹጊን ከተትረፈረፈው ዓሳ እያጠመዱ አቅማቸው እስኪዳከም ድረስ ራሳቸውን ለማትረፍ ተመግበው ሊሆን ይችላል።

በዚህም ምክንያት ሕይወታቸው መትረፍ ችሏል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ፒቹጊን አሁን ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እያደረገ ሲሆን በማገገም ላይ ይገኛል።

ዓቃቤ ሕግ ጀልባዋ እክል ስለተገኘባት የወንጀል ክስ ለመመስረት እየተሰናዳ ሲሆን ሌሎች መርማሪዎች ደግሞ ችግሩ የተከሰተበትን ሁኔታ ለመመርመር እየሠሩ ነው።

አንድ ባለሙያ እንደሚሉት እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች ሲያጋጥሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 1960 በተመሳሳይ አራት የሶቭየት ሕብረት ወታደሮች በትንሽ ጀልባ ውስጥ ሆነው ደብዛቸው ከጠፋ ከ49 ቀናት በኋላ ተገኝተዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)