ለሩሲያ የጦር መሳሪያ የሚያቀርቡት አገራት እነማን ናቸው?

ሁለት ዓመት ያለፈው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የከባድ መሳሪያ ተተኳሾችን በየዓመቱ ወደ ጦር ግንባር እየላከች ትገኛለች።

ሩሲያ የዩክሬንን መሠረተ ልማቶች ያወደሙ አብዛኞቹ የጦር መሳሪያዎቿን ከውጭ አጋሮቿ እንደምታገኝ ይነገራል።

ምዕራባውያን አገራት ማዕቀብ በመጣል የሩሲያን የጦር መሳሪያዎች ማምረት አቅም ለማሽመድመድ ቢሞክሩም ቻይና፣ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያዎችን በመለገስ እየረዷት ነው ይባላል።

የኢራን ድሮኖች እና ሚሳዔሎች

ኢራን በቅርቡ 200 የሚሆኑ የአጭር ርቀት ተወንጫፊ ባሌስቲክ ሚሳዒሎችን ለማቅረብ ከሩሲያ ጋር ስምምነት ፈጽማለች በሚል ተከሳለች። 120 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚጓዙት እና 150 ኪሎ ግራም አረሮችን መሸከም የሚችሉት ሚሳዔሎች ፋዝ-360 የሚል መጠሪያ አላቸው።

እነዚህን ሚሳዔሎች የሚተኩሱ በርካታ የሩሲያ ወታደሮች በኢራን ውስጥ መሠልጠናቸውን የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ገልጿል። እነዚህ ወታደሮቹም በመጪው ኅዳር አካባቢ በዩክሬን ውስጥ እንደሚሰማሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ገልጸዋል።

ፋዝ-360 ሚሳዔሎች ሩሲያ ወደ ድንበሯ ቅርብ የሆኑትን የዩክሬን ከተሞችን እና የኃይል ማመንጫዎች ያሉ ዒላማዎችን እንድትመታ የሚያስችሏት ሲሆን፣ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎች ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ጥልቅ የሆኑ ስፍራዎችን ትመታባቸዋለች ተብሏል።

“ፋዝ-360 በአንጻራዊነት በቅርብ ርቀት ላይ ያሉ ዒላማዎችን ለመምታት ተመራጭ ናቸው” ሲሉ በለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ የጦርነት ጥናት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ማሪና ሚሮን ተናግረዋል።

“ሩሲያ የሯሷ የሆኑ የእነዚህ ተመሳሳይ ሚሳኤሎች የሏትም” ሲሉ ዶክተር ማሪና ያስረዳሉ።

ሩሲያ በምላሹ ለኢራን ወታደራዊ ቴክኖሎጂን ልትሰጥ እንደምትችል ገልጸው ምናልባትም የኑክሌር ቴክኖሎጂን ሊጨምር ይችላል ይላሉ።

ኢራን ለሩሲያ ሚሳዔሎችን በመስጠት የከሰሷት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን አዳዲስ ማዕቀብ ጥለውባታል።

ከተጣሉት ማዕቀቦች መካከል የኢራን አየር መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውሮፓ አገራት የሚያደርጋቸውን በረራዎች መገደብ እንዲሁም በዚህ ስምምነት ተሳትፈዋል በተባሉ ኢራናውያን ላይ የጉዞ እና የንብረት እገዳን ያካትታል።

ኢራን ራስ መር ናቸው የሚባሉትን ፋዝ-360 ሚሳዔሎች ለሩሲያ ሰጥታለች መባሉን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።

የዩክሬን መንግሥት እና የምዕራባውያን የስለላ ኤጀንሲዎች ኢራን ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ሻሂድ-136 የተባሉትን ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ለሩሲያ እያቀረበች ነበር ብለዋል።

ሻሂድ-136 ከጫፉ ላይ አረር የተገጠመለት ሲሆን፣ ጥቃት እንዲፈጽም ትዕዛዝ እስኪሰጠው ድረስ በዒላማው ላይ ሲያንዣብብ የሚቆይ ነው።

የሩሲያ ኃይሎች እነዚህን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በአንድ ጊዜ በከፍተኛ ቁጥር መንጋ በሚባል ሁኔታ የዩክሬን አየር መቃወሚያን ለማወናበድ በከፍተኛ ቁጥር ያሰማራሉ።

ሩሲያ የምታሰማራቸው የድሮን መንጋዎች የዩክሬን አየር መቃወሚያዎች የበለጠ ፈንጂዎችን የሚሸከሙ እና የከፋ ጉዳት በሚያደርሱት ክሩዝ እና ባሊስቲክ ሚሳዔሎች እንዳይቀለበሱ ሽፋን ለመስጠት ነው።

የኢራን መንግሥት በበኩሉ ለሩሲያ የሰጣቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቂት እንደሆኑ እና ይህም ከጦርነቱ በፊት የተሰጡ መሆናቸውን ገልጿል።

ነገር ግን አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ኢራን በተደጋጋሚ ለሩሲያ ድሮኖችን ትልካለች ሲሉ ይከሳሉ፤ የአውሮፓ ኅብረት በሚመለከታቸው ሰዎች እና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

ተተኳሾች እና ሚሳዔሎች ከሰሜን ኮሪያ

የአሜሪካ የመከላከያ መረጃ ተቋም ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ባወጣው ዘገባ ሰሜን ኮሪያ፣ ለሩሲያ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ የመድፍ ተተኳሾችን መስጠቷን ነው።

መድፍ የዩክሬን እና የሩሲያ ኃይሎች በጦር ግንባሮች ላይ የሚጠቀሙት ዋነኛው የጦር መሳሪያ ነው። የጠላት መሳሪያዎች እና እግረኛ ወታደሮች እንዳይገስግሱ መከላከል እንደሚያስችል ይነገርለታል።

በዩናይትድ ኪንግደም ተቀማጭነቱን ያደረገው ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ የተሰኘ የጥናት ተቋም ከቅርብ ወራት ወዲህ ከተተኳሽ አንጻር የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን ላይ 5 ለ 1 ብልጫ እንዳገኙ ነው።

ተቋሙ እንደሚለው በዚህ ብልጫ የተነሳ ሩሲያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሰፊ የዩክሬን ምሥራቃዊ ግዛቶችን መቆጣጠር የቻለችው።

ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የዩክሬን የስለላ መኮንኖች ከባድ በተባለው የአየር ጥቃት ላይ በኻርኪቭ ግዛት የተተኮሱ ሰሜን ኮሪያ ሠራሽ ሁለት ዓይነት አጭር ርቀት ባሌስቲክ ሚሳዔሎችን ቁርጥራጮች ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት አንደኛው ህዋሶንግ-11 ወይም ኬኤን 23 እንደሚባልም አክለው ገልጸዋል።

ይህ ባለስቲክ ሚሳኤል 500 ኪሎ ሜትር የሚመዝኑ ተወንጫፊዎችን መያዝ የሚችል እና ከ400 እስከ 690 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ የሚችል ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የሚደረጉ የባለስቲክ ሚሳዔሎች ንግድ ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

የዩክሬን የስለላ ድርጅት እንደሚለው ሰሜን ኮሪያ 50 ሚሳዔሎችን ወደ ሩሲያ እንደላከች ስታስታውቅ አሜሪካ ደግሞ ሩሲያ የሰሜን ኮሪያ ሚሳዔሎችን በመጠቀም ዘጠኝ ጥቃቶችን በዩክሬን ላይ እንደፈጸመች ባለፈው ዓመት በነበረ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ገልጻለች።

እንደ አሜሪካ የመከላከያ መረጃ ኤጀንሲ ከሆነ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ድርድር የጀመሩት በአውሮፓውያኑ 2022 ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ ሚሳዔሎችም በቀጣዩ ዓመት ለሙከራ ጥቅም ላይ ውለዋል።

ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ሩሲያ እነዚህን የጦር መሳሪያዎች ወደ ዩክሬን ማስወንጨፍ እንደጀመረች ኤጀንሲው አክሎ ገልጿል።

“ህዋሶንግ-11 ሚሳዔሎች ሩሲያ ራሷ ካሏት እንደ እስካንደር ከተሰኙት አጭር ርቀት ሚሳዔሎች በበለጠ ርካሽ ናቸው” የሚሉት ዶክተር ሚሮን፣ ሩሲያ እነዚህን ሚሳኤሎች መጠቀም የጀመሩት ዋጋውን አስልታ ነው ይላሉ።ሰሜን ኮሪያ ሰራሹ ህዋሶንግ- 11 ሚሳኤል ቁርጥራጭ

“ሩሲያ እንደ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ካሉ አገራት ጋር የጦር መሳሪያ ስምምነቶች ማድረግ መቻሏ ለምዕራቡ ከዓለም እንዳልተገለለች እና አጋር እንዳላት አመልካች ነው” በማለት ያስረዳሉ።

እንደ ህዋሶንግ-11 ያሉ ባሌስቲክ ሚሳዔሎች ዒላማቸውን ለመምታት የሚወርዱበት ፍጥነት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለማክሸፍ እና ለመቀልበስ አስቸጋሪ ናቸው።

ይሁን እንጂ የዩክሬን የስለላ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሰሜን ኮሪያ የመጡት አብዛኞቹ ሚሳዔሎች ዒላማቸውን መምታት አልቻሉም። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቅሱት የኤሌክትሪክ ችግሮችን ነው።

ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ጦር መሳሪያ ልካለች መባሏን የማትቀበለው ሲሆን፣ ሩሲያም ይህንኑ አጣጥላለች። የዩክሬን የስለላ መኮንኖች የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ለሩሲያ ጦር ወግነው እየተዋጉ ማየታቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ዩክሬን በሩሲያ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ጣቢያ ላይ ባስወነጨፈችው የሚሳዔል ጥቃት ስድስት የሰሜን ኮሪያ መኮንኖችን መገደላቸውን እንዲሁም ሦስት መቁሰላቸውን የዩክሬን ጋዜጦች ዘግበዋል።

ከዚህ ቀደምም የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በዩክሬን እየተዋጉ ነው የሚል ውንጀላ ቀርቦ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “እርባና የሌለው” በማለት ክሱን አጣጥለውታል።

የቻይና ጥምር ጥቅም ያላቸው ግብዓቶች

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት ቻይና ለሩሲያ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ በመስጠት ወሳኝ ስፍራ አላት ሲሉ ይከሳሉ።

እንደ ኮምፒውተር ቺፕስ ያሉ ለሌሎች የሲቪል ተግባራት ግብዓት የሚውሉ፤ ነገር ግን የጦር መሳሪያ ለማምረት የሚያገለግሉ “ሁለት ጥቅም ያላቸው ግብዓቶችን” ቻይና እያቀረበች ነው ሲሉ አገራቱ ከሰዋታል።

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ካርኒጌ ኢንዶውመንት ፎር ኢንተርናሽናል ፒስ ተቋም (ሲአይአይፒ) በበኩሉ ቻይና በየወሩ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ሚሳኤል እና ታንኮችን የመሳሳሉ ጦር መሳሪያዎች ማምረት የሚያስችሉ ሁለት ጥቅም ያላቸው ግብዓቶችን ለሩሲያ መላኳን አስፍሯል።የቻይና የኮምፒውተር ግብዓቶች የምስሉ መግለጫ, ኔቶ እንደሚለው የቻይና የኮምፒውተር ግብዓቶች ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ምርት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው

ሲአይአይፒ እንደሚገልጸው ሩሲያ 70 በመቶ የማሽን መሳሪያ ግብዓቶችን እንዲሁም 90 በመቶ እንደ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ያሉ የማይክሮ ኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎችን የምትገዛው ከቻይና መሆኑን ነው።

ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2023 ሁለት ጥቅም ያላቸውን 89 በመቶ ግብዓቶችን ከቻይና ማስመጣቷን ይኸው ተቋም ገልጿል። ከጦርነቱ በፊት ጀርመን እና ኔዘርላንድንስ አብዛኛውን ግብዓት ያቀርቡ የነበሩ ሲሆን፣ ሆኖም በእነዚህ የወጪ ንግድ ግብዓቶች ላይ ማዕቀብ መጣላቸውን ተከትሎ ቻይና ክፍተቱን ሞልታለች ተብሏል።

ቻይና በጦርነቱ ገለልተኛ አካል መሆኗን በመግለጽ በጦር መሳሪያ ምርት ላይ አላት እየተባለ የሚቀርብባትን ክስ አጣጥላለች። ለሩሲያ ገዳይ የጦር መሳሪያዎችን እንደማታቀርብ እና የምትሸጣው ግብዓቶች ጥንቃቄ የተሞላበት ነው ብላለች።

ሮይተርስ በበኩሉ ሩሲያ በቻይና ጋርፒያ-3 የተሰኘ ረጅም ርቀት የሚጓዝ ድሮን ለማምረት ፋብሪካ ማቋቋሟን ዘግቧል።

የቻይና መንግሥት በምላሹ ይህን መሰል ፕሮጀክት እንደማያውቅ እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ላይ ያለው የወጪ ንግድ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሆነ መናገሩን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)