ሄዝቦላህ ባደረሰው የድሮን ጥቃት 4 የእስራኤል ወታደሮች ተገደሉ

የእስራኤል ጦር ኃይል (አይዲኤፍ) በሰሜናዊ እስራኤል በድሮን ጥቃት አራት ወታደሮች ሲገደሉ 60 ገደማ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አስታወቀ።

አይዲኤፍ እንዳለው ሰባት ወታደሮች ክፉኛ ቆስለው ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።

ጥቃቱ የደረሰው ከሀይፋ 33 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቢኒያሚና ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የወታደሮች ካምፕ ላይ ነው።

ሄዝቦላህ ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስዷል። ዒላማ ያደረገው በአካባቢው ያለውን የአይዲኤፍ ጎላኒ ብሪጌድ የማሰልጠኛ ጣቢያ መሆኑን አሳውቋል።

ጎላኒ ብሪጌድ የተባለው ማሰልጠኛ ጣቢያ በቴል አቪቭ እና ሀይፋ መካከል የሚገኝ ነው።

የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን በመገናኛ ቢሮው በኩል ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን ያደረሰው ሐሙስ ዕለት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ እና በቤይሩት ላደረሰችው ጥቃት ምላሽ እንዲሆን ነው ብሏል።

ቡድኑ እንዳለው በሰሜናዊ እስራኤል የሚገኘውን ጣቢያ የመታው “በድሮን መንጋ” ነው።

ማገን ዴቪድ አዶም አሊያም ኤምዲኤ የተባለው የእስራኤል የአምቡላንስ አገልግሎት በጥቃቱ ምክንያት 61 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቆ ሶስት ግለሰቦች ለሕይወታቸው አስጊ የሆነ አደጋ እንደደረሰባቸው ገልጿል።

ኤምዲኤ እንደሚለው ከቁስለኞች መካከል 37 የሚሆኑት በሄሊኮፕተር እና በአምቡላንስ ወደ ስምንት ሆስፒታሎች ተወስደዋል።

አይዲኤፍ 6 ወታደሮች መሞታቸውን ሲያረጋግጥ ኤምዲኤ ደግሞ 3 ክፉኛ የቆሰሉ፣ 18 መካከለኛ የሚባል አደጋ የደረሰባቸው፣ 31 አነስተኛ ጉዳት የደረሰባቸው እና ዘጠኙ ደግሞ “ድንጋጤ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ብሏል።

የእስራኤል መንግሥት አደጋ ሲደርስ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ምን ላይ እና የት አካባቢ ጥቃት እንደደረሰ ከአይዲኤፍ ሳያረጋግጡ መዘገብ አይችሉም ይላል። ይህን ተከትሎ ጥቃቱ የደረሰው ቢኒያሚና ወታደራዊ ጣቢያ ላይ መሆኑን አይዲኤፍ እስኪያሳውቅ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው።

አንዳንድ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ወታደራዊው ጣቢያ ዝቅ ብለው በሚበሩ እና ከሊባኖስ በተተኮሱ ድሮኖች ነው የተመታቸው ሲሉ ዘግበዋል።

እኒህ ድሮኖች ብዙም በቴክኖሎጂ ያልተራቀቁ መሆናቸው የማስጠንቀቂያ ደወል እንዳይሰማ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም አስብሏል።

ከጥቃቱ በኋላ በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ማኅበራዊ ሚድያዎች እና ድረ-ገፆች ላይ የሚለጠፉ ምስሎች ሄሊኮፕተሮችን ጨምሮ የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪዎች የተገዶኡ ሰዎችን ሰሜናዊ እስራኤል ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ሲወስዱ አሳይተዋል።

አብዛኛዎቹ በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች ሀዴራ ወደሚገኘው ሒሌል የጤና ማዕከል ነው የተወሰዱት፤ የተቀሩት ደግሞ ሀይፋ፣ አፉላ እና ኔታኒያ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ተወስደዋል።

አሁንም በጥቃቱ ምክንያት ምን ያክል ጉዳት እንደደረሰ በውል አይታወቅም። ጥቃቱ ሲደርስ አብዛኛዎቹ ወታደሮች በጣቢያው በሚገኝ ‘ካንቲን’ ውስጥ ነበሩ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)