ሄዝቦላህ ለተገደሉበት መሪው ተተኪ ይፋ ሲያደርግ እስራኤል ዒላማ እንደምታደርጋቸው ዛተች

የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ባለፈው መስከረም በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉበትን መሪውን ሐሳን ናስራላህን እንዲተኩ ናይም ቃሴምን መምረጡን ይፋ አደረገ።

ከእስራኤል ጋር ወደ ግልጽ ጦርነት የገባው ሄዝቦላህ መሪውን ጨምሮ በርካታ አመራሮቹ ደቡባዊ ቤይሩት ውስጥ በእስራኤል በተፈጸመ የአየር ጥቃት የተገደሉበት መስከረም 17/2017 ዓ.ም. ነበረ።

ከጥቃቱ ከተረፉት ጥቂት የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት የ71 ዓመቱ ቃሴም በመሪነት የተመረጡት በሄዝቦላህ ሹራ ምክር ቤት አማካኝነት መሆኑን አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎ የእስራኤል መንግሥት ባስተላለፈው መልዕክት አዲሱ መሪ አዲስ አካሄድን ካልመረጡ በመሪነት የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ይሆናል ሲል ዝተዋል።

ናይም ቃሴምን ወደ ከፍተኛው የአመራር ቦታ የመጡት ከ30 ዓመት በፊት የሄዝቦላህ ዋና ፀሐፊ በነበሩት እና በእስራኤል የአየር ጥቃት በተገደሉት በአባስ አል ሙሳዊ የቡድኑ ምክትል መሪ በመሆን ነው።

ሐሳን ናስራላህ የመሪነት ቦታው ሲረከቡ ቃሴም በምክትልነት ቦታቸው ላይ በመቆየት ባለፈው ዓመት ድንበር ዘለል ግጭቶች ከእስራኤል ጋር ሲካሄድ የሄዝቦላህ ግንባር ቀደም ቃል አቀባይ በመሆን ከውጭ መገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ሐሳን ናስራላህ ከተገደሉ ከሳምንት በኋላ መሪነቱን ይረከባሉ ተብለው የነበሩት ከፍተኛ የቡድኑ ባለሥልጣን ሐሼም ሳፌዲንም በእስራኤል በተፈጸመ የአየር ጥቃት ተገድለዋል።

እስራኤል ቤይሩት አየር ማረፊያ አቅራቢያ መስከረም 24 ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የሄዝቦላህ ባለሥልጣናት ከሳፌዲን ጋር ያላቸው ግንኙነት መቋረጡን የገለጹ ሲሆን፣ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ የእስራኤል ባለሥልጣናትን በመጥቀስ የአየር ጥቃቱ ዒላማ ሳፌዲን ነበሩ ብለው ዘግበዋል።

ናስራላህ ከተገደሉ በኋላ ቃሴም መስከረም ማብቂያ ላይ በሊባኖስ የተኩስ አቁም እንዲደረስ የሚደረገውን ጥረት ቡድናቸው እንደሚደግፍ የገለጹበትን ጨምሮ ሦስት ጊዜ በቴሌቪዥን የተላለፈ ንግግር አድርገዋል።

አዲሱ የሄዝቦላህ መሪ የናስራላህን ያህል ተጽእኖ የመፍጠር ግርማ አላቸው ብለው በርካታ ሊባኖሳውያን አያስቡም።

ናይም ቃሴም በመሪነት መሰየማቸውን ተከትሎ የእስራኤል መንግሥት በይፋዊ የአረብኛ የኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት በቡድኑ የመሪነት ቦታ ላይ የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ብቻ ሊቆዩ እንደሚችሉ ዝቷል።

“[ቃሴም] እንደቀደሙት የሐሳን ናስራላህ እና የሐሼም ሳፌዲንን ዱካ የሚከተል ከሆነ በሽብርተኛው ድርጅት ታሪክ በመሪነት ቦታው ለአጭር ጊዜ የቆየው ግለሰብ ይሆናል” ብሏል።

ጨምሮም የሄዝቦላህ ያለው ወታደራዊ ኃይል ካልፈራረሰ በስተቀር በሊባኖስ ውስጥ መፍትሄ አይኖርም በማለት የእስራኤልን ዓላማ ገልጿል።

እስራኤል እና ሄዝቦላህ በጋዛ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ለአንድ ዓመት ያህል ድንበር ተሻጋሪ የከባድ መሳሪያ ግጭቶች እና የአየር ድብደባ ሲያካሂዱ ከቆዩ በኋላ ነው ወደለየለት ጦርነት የገቡት።

እስራኤል በሄዝቦላህ የሚሳዔል፣ የሮኬት እና የድሮን ጥቃቶች ምክንያት ከሰሜናዊ ግዛቶቿ የተፈናቀሉ ዜጎቿን ለመመለስ እና ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ በሚል አንድ ወር ያለፈው የአየር እና የእግረኛ ሠራዊት ጥቃት በሊባኖስ ውስጥ እያካሄደች ነው።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ባለው በአንድ ዓመት ውስጥ ቢያንስ 2 ሺህ 464 ሊባኖሳውያን ሲገደሉ ወደ 12,000 የሚጠጉት ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሳባቸው የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተመሳሳይ ጊዜ ሄዝቦላህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች እና ድሮኖችን በመጠቀም በእስራኤል ላይ ጥቃት የፈጸመ ሲሆን፣ ቢያንስ 59 እስራኤላውያን በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል እና በወረራ በያዘችው የጎላን ተራሮች አካባቢ መገደላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)