ፒኤስጂ እና ዶርትሙንድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜን ተቀላቀሉ…..

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች የፈረንሳዩ ፒኤስጂ እና የጀርመኑ ዶርትሙንድ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቀሉ።

ክሊያን ምባፔ ሁለት ጎሎችን ባስቆጠረበት ጨዋታ ፒኤስጂ የመጀመሪያውን ጨዋታ ውጤት ለመቀልበስ ችሏል።

ፓሪስ ላይ በተከናወነው የመጀመሪያው ጨዋታ 3 ለ 2 የተሸነፈው የፈረንሳዩ ክለብ ትናንት በካምፕኑ 4 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል።

በጨዋተው ላይ ቀድሞ ጎል ማስቆጠር የቻለው የባርሳው ራፊንሃ ሲሆን ባለሜዳው ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማሳለፍ ዕድሉን ያሰፋ መስሎ ነበር።

ለፒኤስጂ ተራራ የሚመስለው ጨዋታ የቁልቁለት ጉዞ የሆነለት የባርሴሎናው ተከላካይ ሮናልድ አራውዮ በሠራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ ነው።

ከእረፍት በፊት የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች ኦስማን ዴምቤሌ የቡድኑን ቀዳሚ ጎል አስቆጠረ።

ከእረፈት መልስ ደግሞ ቪቲንሃ ባስቆጠራት ጎል ጨዋታውን ፒኤስጂ 2 ለ 1 ለመምራት ቻለ።

ጆአኦ ካንሴሎ የፈጸመውን ጥፋት ተከትሎ ፒኤስጂ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ክሊያን ምባፔ ለማስቆጠር በቃ።

በጨዋታው መገባደጃ ላይ ምባፔ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋተው በፒኤስጂ 4 ለ 1 አሸናፊነት እንዲተናቀቅ አድርጓል።

በድምር ውጤትም ፒኤስጂ 6 ለ 4 በሆነ ውጤት ባርሴሎናን በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

በጨዋታው የባርሳውን አሰልጣኝ ዣቪ ፈርናንዴዝን ጨምሮ ሌላ የአሰልጣኞች ቡድን አባል በቀይ ከሜዳ እንዲወጡ ተደርገዋል።

ጀርመን ላይ በተካሄደ ሌላኛው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ ቦሪስያ ዶርትሙንድ አትሌቲኮ ማድሪድን በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

በመጀመሪያው ጨዋታ 2 ለ 1 የተሸነፈው ዶርትሙንድ ውጤቱን ቀልብሶ ከ11 ዓመታት በኋላ ነው ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀል ችሏል።

ጁሊያን ብራንድ እና ማትሰን ባስቆጠሯቸው ጎሎች ዶርትሙንድ ጨዋታውን 2 ለምንም በመምራት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ተመልሰዋል።

ከእረፍት መልስ ተጠናክረው የገቡት አትሌቲኮዎች በማሪዮ ሄርሞሶ እና በአንጅል ኮሪያ ጎሎች ጨዋታውን አቻ ለማድርግ ችለዋል።

በ71ኛው ደቂቃ ኒክላስ ባስቆጠራት ጎል ዶርትሙንድ መምራት ቻለ።

ከሦስት ደቂቃ በኋላ ማርሴል ሳቢትዘር ባስቆጠራት ጎል ጨዋተው በዶርትሙንድ 4 ለ 2 የበላይነት ተጠናቋል።

በድምር ውጤት 4 ለ 2 በማሸነፍም ግማሽ ፍጻሜውን ለመቀላቀል በቅቷል።

ከሁለት ሳምንት በኋላ በግማሽ ፍጻሜው ፒኤስጂ እና ቦርሲያ ዶርትሙንድ እንዲጫወቱ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለት ቀሪ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይከናወናሉ።

ባየር ሙኒክ አሊያንዝ አሬና ላይ የእንግሊዙን አርሴናል ያስተናግዳል። ሁለቱ ቡድኖች ኤምሬትስ ላይ 2 አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።

ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በሜዳው ሪያል ማድሪድን ያስተናግዳል። በመጀመሪያው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች 3 አቻ ተለያይተዋል።

 

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(bbc)