ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሚቀጥለው ሳምንት ለተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሊሰጡ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቀጣይ ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከአባላት ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እንደሚሰጡ በተወካዮች ምክር ቤት የቢቢሲ ምንጮች ተናገሩ።

በምክር ቤቱ አሠራር መሠረት የሕዝብ እንደራሴዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለአፈ ጉባኤው ጽህፈት ቤት እንዲያስገቡ በአባላት የመልዕክት መለዋወጫ የቴሌግራም ገጽ አማካይነት ተጠይቀው እንደነበር የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።

ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አራት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑ ምንጮች ለጥያቄ ማስገቢያ የተሰጠው ቀነ ገደብ በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ከሰዓት መጠናቀቁን አክለዋል።

አንድ የምክር ቤቱ አባል ጨምሪውም “ተከታታይ ስብሰባዎች ስላሉ የትም እንዳትሄዱ” የሚል ማሳሰቢያ ለአባላት መተላለፉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓመት ሦስት ጊዜ በምክር ቤቱ ቀርበው በአጠቃላይ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄ ምልሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያዝላቸው ፕሮግራም መሠረት የመንግስትን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ አስመልከቶ በዓመት ሁለት ጊዜ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ደንቡ ያትታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅድሚያ የሚቀርቡት የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት በተወካዮች እና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች ዓመታዊ የመክፈቻ ንግግር ላይ በሚደረግ ውይይት ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ በፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ንግግር ላይ በተደረገ ውይይት የመንግሥትን አቋም ለመግለጽ ፓርላማ ቀርበው እንደነበር ይታወሳል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥለው ሳምንት በተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርቡ በኅዳር ወር ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ የተከሰቱ ዐበይት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ሊቀርቡላቸው እንደሚችሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከልም ከአንድ ወር በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ሰንድ አንዱ ነው።

በቀጠናው ውዝግብን ያስከተለው የመግባቢያ ሰነድ ኢትዮጵያ ለጦር ሰፈር እና ለወደብ ግንባታ 20 ኪሎ ሜተር ስፋት ያለው የባሕር ጠረፍ ቦታን በሊዝ እንድታገኝ የሚያደርግ ሲሆን፣ ሶማሊላንድ በበኩሏ ከኢትዮጵያ ዕውቅናን እንደምታገኝ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጰያን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ያስታወቁት ከወራት በፊት ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ገለጻ ነበር። “ከጠብታ ውሃ እስከ ባህር ውሃ” በሚል ርዕስ ባደረጉት ቢዘህ ገለጻ ለኢትዮጵያ ባሕር በር ማግኘት “የህልውና ጉዳይ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ኅዳር ወር በተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የባሕር በርን በተመለከተ “ማንንም የመውረር ፍላጎት የለንም” ካሉ በኋላ “በቢዝነስ ሕግ ግን የማያወላዳ ምርጫ እንፈልጋለን” ብለው ነበር።

ሌላው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው ጉዳይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ ነው። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ‘ሸኔ’ ከሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን ጋር በሁለተ ዙር ተደርጎ የከሸፈው ድርድረም በምክር ቤቱ ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የአገሪቱ ዕዳ የመክፈል አቅም በተወካዮች ምክር ቤት ከሚነሱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የኑሮ ውድነትም በፓርላማ አባላቱ በጥያቄ መልክ ሊነሳ እንደሚችል ይጠበቃል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnn

ምንጭ ( ቢቢሲ )