የአፍሪካ ዋንጫ፡ ከናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ጨዋታ በፊት ሁለቱ አገራት ውዝግብ ውስጥ ገቡ

ዛሬ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ከሚያደርጉት የአፍሪካ ዋንጫ የግማሸ ፍጻሜ ግጥሚያ በፊት በሁለቱ አገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ተከስቷል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የናጄሪያ ከፍተኛ ኮሚሽን ናይጄሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ካሸነፈች በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ናይጄሪያውያን በጩኸት ከተሞላ የደስታ አገላለጸ እንዲቆጠቡ ጠይቋል።

ይህ ማስጠንቀቂያ የመጣው ናይጄሪያ ደቡብ አፍሪካን አሸንፋ ወደ ፍጻሜው ካለፈች በናይጄሪያውን የደስታ አገላለጽ የተበሳጩ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች መጤ ጥል ጥቃት እንዳይሰነዝሩ በመስጋት ነው።

ሆኖም ደቡብ አፍሪካ ማስጠንቀቂያውን “የተሳሳተ” ስትል አጣጥላዋለች።

“ሱፐር ኤግልስ” እና “ባፋና ባፋና” እየተባሉ የሚጠሩት የናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የረጀም ጊዜ ተፎካካሪዎች ናቸው።

ሆኖም ትላንት የደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ የደቡብ አፍሪካ እና የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድኖች በተጋጠሙ ጊዜ ሁከት ተፈጥሮ አያወቅም ብሏል።

“የተሰጠው ምክር ተገቢ ያልሆነ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ዜጎች መካከል አላስፈላጊ ውጥረት የሚፈጥር ነው” ሲል አክሏል።

ሆኖም ናይጄሪያ ከመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ በኋላ በጉዳዩ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በደቡብ አፍሪካ ከተለያዩ ሀገራት የስራ ዕድል ፈልገው የመጡ ዜጎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት መጤ ጠል ጥቃቶች ይሰነዘራሉ።

የናይጄሪያ የዲፕሎማሲ አገለግሎት ትላንት ባወጣው መግለጫ በኢንተርኔት በተሰራጨ መልዕክት ችላ የማይባሉ ዛቻዎች መኖራቸው ጠቅሷል።

ጨምሮም ናይጄሪያውያን አካባቢያቸውን በጥንቃቄ እንዲከታተሉ፣ ጨዋታውን የት መመልከት እንዳለባቸው ልብ እንዲሉ እና በጩኸት እንዲሁም ጽብን በሚጭር መንገድ ደስታቸውን እንዳይገልጹ አሳስቧል።

የናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ለፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጉት ጨዋታ ዛሬ ምሽት ሁለት ሰዓት በአይቮሪ ኮስቷ ቦኬ ከተማ ይደረጋል። ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ በአዘጋጇ አይቮሪ ኮስት እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnnn

ምንጭ (ቢቢሲ)