የአርሰናል አስደናቂ ድል “ዋንጫው ከሦስት ክለቦች እንደማይወጣ ያሳየ ነው”

አርሰናል የዋንጫ ተፎካካሪነታቸውን ለማስጠበቅ የትናንት ምሽቱን ጨዋታ “የግድ ማሸነፍ” ነበረባቸው ባይባልም፤ የዋንጫ ተስፋቸውን ለማስቀጠል ግን “መሸነፍ በጭራሽ የሚታሰብ አልነበረም” ይላል የቢቢሲ እግር ኳስ ጸሐፊ ፊል ማክነለቲ።

መድፈኞቹ ይህን ጨዋታ ቢሸነፉ ኖሮ ሊጉን እየመሩ ካሉት ሊቨርፑል በ8 ነጥብ ርቀው ይቀመጡ ነበር። የመድፈኞቹን ድል ተከትሎ ልዩነቱ ወደ 2 ነጥብ ብቻ ጠብቧል።

ሊቨርፑል ሁሌም ለአርሰናል ቀላል ተጋጣሚ አይደለም። ሊቨርፑል በኢሚሬትስ የተሸነፈው አንድ ግዜ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የሚኬል አርቴታ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ በአስደናቂ ብልጭ ጎል አስቆጥሮ ቀዳሚ መሆን ችሎ ነበር።

መድፈኞቹ ጨዋታውን ተቆጣጥረው እና ጎል አስቆጥረው የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ በመድፈኞቹ ተከላካዮች የተፈጠረው ስህተት በኢሚሬትስ በደስታ ድምጻቸው ጎልቶ ይሰማ የነበረውን ደጋፊ ዝም ያሰኘ ነበር።

የመጀመሪያ አጋማሽ በ 1 አቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ በእረፍት ሰዓት በኢሚሬትስ ስታዲየም ሲጨፈሩ የነበሩት የሊቨርፑል ደጋፊዎች ነበሩ ይላል ፊል።

በሁለተኛው አጋማሽ መድፈኞቹ ዳግም ሊቨርፑልን መፈተን ጀመሩ። ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬ ወደ ኋላ አድርገው ተደራጅተው እና የሊቨርፑል ደካም ጎን እና ስህተት ተጠቅመው ግብ አስቆጥረው መልሰው መምራት ችለዋል።

ቫይዳይክ እና አሊሰን በሰሩት ስህተት ገብርኤል ማርቲኔሊ አርሰናልን ወደ መሪነት የመለሰች ግብ አስቆጥሯል።

ተቀይሮ የገባው ትሮሳርድ ያስቆጠራት 3ኛዋ አስደናቂ ግብ የአርሰናልን ድል ያረጋገጠች ነበረች።

የአርሰናል የትናንት ምሽቱ ድል ዋንጫው ወደ ሦስት ቡድን ሊሄድ እንደሚችል ያመላከተ ነው። ከዚህ በላይ ግን በወሳኝ የውድድር ዓመቱ ምዕራፍ ላይ እንደ ሊቨርፑል ያለ ጠንካራ ቡድንን ማሸነፍ ለአርሰናል ተጫዋቾች ትልቅ ትርጉም እንደነበረ ከጨዋታው በኋላ ተመልክተናል።

ዳኛው ጨዋታው መጠናቀቁን በፊሽካቸው ሲያበስሩ ስታዲየሙ በደስታ ጩኸት ተናግቷል።

አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ የክለቡን ፎቶግራፈር ካሜራ ተቀብሎ ፎቶ አንሺውን ፎቶ ሲያነሳው ታይቷል። አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታት ክሎፕ በሚታወቁበት የደስታ አገላለጽ ደስታውን ሲገልጽ ነበር።

ለዋንጫው ትልቅ ግምት የምሰጣቸው ማንቸስተር ሲቲ የአርሰናል ድል ምቾት እንደሚሰጣቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

መድፈኞቹ ሊቨርፑል በነጥብ ርቆ እንዳይሄድ አድርገዋል። ሲቲ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች እየቀሩት በ46 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እነዚህን ሁለት ቀሪ ጨዋታዎችን የሚያሸንፍ ከሆነ በ52 ነጥብ የሊጉን መሪነት የሚረከብ ሲሆን ሊቨርፑል እና አርሰናል እንደ ቅድመ ተከተላቸው በ51 እና 49 ነጥቦች ሁለተኛ እና ሦስተኛ ይሆናሉ።

ደክላን ራይስ በትክክልም የ105 ሚሊዮን ፓዎንድ ተጫዋች መሆኑን ዳግም አስመስክሯል። ራይስ በትክክለኛው ሰዓት በትክክለኛው ቦታ ሁሉ ይገኝ ነበር። መድፈኞቹ መሃል ሜዳው ላይ የሚያስፈልጋቸውን የበላይነታቸውን እንዲያረጋግጡ አስችሏል።

ለመድፈኞቹ የአቻነት ግብን ያስቆጠረው ማርቲኔሊ በግራ ክንፍ በኩል የጨዋታ አቀጣጣይ ሆኖ አምሽቷል። ኳስ የመያዝ ጽኑ ፍላጎት እና ጥራት ነበረው። ያላሰለሰ ጥረቱም በተከላካይ ስህተት ኳስን ከመረብ እንዲያገናኝ ዕድል ሰጥቶታል።

በትናንቱ ድል የጆርጂኒዮ ሚና መዘንጋት የለበትም። መደፈኞቹን ጨዋታውን ተቆጣጥረው እንዲወጡ ብዙ ልምድ ያለው አማካይ ትልቅ ስራን ሰርቷል። የጨዋታው ምርጥ (ማን ኦፍ ዘ ማች) ተብሎም ተመርጧል።

ምንጭ (ቢቢሲ)