የተኩስ አቁም ብትነቅፍም ንግግሮች እንደሚቀጥሉ አስታወቀች

አዲሱ የጋዛ የተኩስ አቁም ሃሳብ “ከእስራኤል መሠረታዊ መስፈርቶች የራቀ” ቢሆንም ድርድሩ ይቀጥላል ሲሉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን የገለጹት ሐማስ የኳታር እና የግብጽ ሸምጋዮች ያቀረቡትን የእርቅ ስምምነት መቀበሉን ተከትሎ ነው።

የፍልስጤም ተደራዳሪ አባላት “አሁን ውሳኔው የእስራኤል ነው” ብለዋል።

የእስራኤል ወታደሮች እና ታንኮች ለሊት ላይ በራፋህ ድንበር ማቋረጫ አካባቢ መታየታቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያን የራፋህን ምሥራቃዊ ክፍል ለቀው እንዲወጡ ካስጠነቀቀ በኋላ በግብጽ ድንበር ላይ በምትገኘው ከተማ የአየር ጥቃት ፈጽሟል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሰኞ ዕለት በተሽከርካሪዎች ወይም በጋሪ ታጭቀው ሲወጡ ታይተዋል።

እስራኤል 1.4 ሚሊዮን ሰዎች በሚኖሩባት ከተማ ላይ “በሐማስ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት” ልትሰነዝር እንደምትችል ስታስፈራራ ቆይታለች። የከተማዋ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ከሌሎች የጋዛ አካባቢዎች ጥቃቶችን ሸሽተው የተጠለሉባት ናት።

ሰኞ ዕለት የናታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጠው መግለጫ “የሐማስ ሃሳብ ከእስራኤል መሠረታዊ ፍላጎቶች የራቀ ቢሆንም፤ በእስራኤል ተቀባይነት በሚያገኝ ሁኔታ ከስምምነት ለመድረስ የሚያስችለውን ዕድል ለመጠቀም እስራኤል የተደራዳሪ ልዑካንን ትልካለች” ብሏል።

የእስራኤል የጦር ካቢኔ “ዓላማችንን ለማሳካት እና በሐማስ ላይ ወታደራዊ ጫና በማሳደር ታጋቾችን ለማስለቀቅ፤ የሐማስ ወታደራዊ እና የአስተዳደራዊ አቅምን ለማጥፋት እና ወደፊትም ጋዛ የእስራኤል ላይ ስጋት እንዳትሆን” የራፋህ ዘመቻ እንዲቀጥል ወስኗል ሲል አክሏል።

ሐማስ የፖለቲካ መሪው እስማኤል ሃኒዬህ ቀደም ሲል ለኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና ለግብጽ የስለላ ኃላፊ “የተኩስ አቁም ስምምነትን በተመለከተ ያቀረቡትን ሃሳብ መቀበላቸውን” የሚገልጽ መግለጫ አውጥተዋል።

ሐማስ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ “የጥቃት እንቅስቃሴን እስከመጨረሻው” ለማስቆም መስማማቱን ጉዳዩን የሚያውቁ ከፍተኛ የፍልስጤም ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህም ሐማስ የትጥቅ ትግሉን ሊያቆም እንደሚችል ፍንጭ ቢሰጥም ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫ አልተሰጠም። ስምምነቱ በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ነው።

በመጀመሪያው ምዕራፍ በእስር ላይ የሚገኙትን ሴት የእስራኤል ወታደሮች ከእስር መልቀቅን ያካትታል። በእያንዳንዱ ወታደርም የዕድሜ ልክ የተፈረደባቸውን ጨምሮ በእስራኤል እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ 50 ፍልስጤማውያን እስረኞች ይፈታሉ።

በዚህ ጊዜ የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ውስጥ ይቆያሉ። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሥራ ላይ በዋለ በ11 ቀናት ውስጥ እስራኤል በግዛቱ መሃል የሚገኙትን ወታደራዊ ተቋሞቿን በማፈራረስ ከሳላህ አል-ዲን መንገድ እና ከባህር ዳርቻው መንገድ ትወጣለች።

ከ11 ቀናት በኋላም የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜን ጋዛ እንዲመለሱ ይፈቀድላቸዋል።

እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ ከሆነ ገለጻ በሁለተኛው ምዕራፍ “ዘላቂ የመረጋጋት ጊዜ” እና የጋዛን እገዳ ሙሉ በሙሉ ማንሳትን ያጠቃልላል።

ከኳታር እና ከግብጽ ጋር በአደራዳሪነት ስትሠራ የቆየችው አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር በኩል የሐማስን ምላሽ እየገመገመች እና “ከአጋሮቻችን ጋር እየተወያየን ነው” ብላለች።

የአሁኑ ጦርነት የጀመረው መስከረም 26 የሐማስ ታጣቂዎች ወደ ደቡብ እስራኤል ዘልቀው በመግባት ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደሉ እና ከ250 በላይ ታጋቾችን ከወሰዱ በኋላ ነው።

እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እያደረገች ባለው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት 34ሺህ 683 ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል፤ 70ሺህ 18 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስትር እንደሚለው ከሟቾቹ መካከል የሚበዙት ሴቶችና ሕጻናት ናቸው።

ከዚህ ቀደም ኳታር ሁለቱን ተዋጊዎች አሸማግላ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ተደርጎ፣ 105 እስራኤላዊ ታጋቾች መለቀቃቸው አይዘነጋም።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )