የሴት ልጅ ግርዛትን የተመለከተው አወዛጋቢው የኢትዮጵያ ዑለማዎች ውሳኔ

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የዑለማ ጉባዔ፣ የ2ኛ ዓመት መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔን በማስመልከት የወጣው መግለጫ በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ ጥር 22 ቀን፣ 2016 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የሴት ልጅ ግርዛትን በተመለከተ በቁጥር 12 እና 13 ላይ የሰፈረው ውሳኔ ከሴቶች መብት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንጻር ተቃርኖ እንዳለው እንደ “አዲስ ፓወር ሃውስ’’ እና “አርቲክል 35” ያሉ በሴቶች መብት ላይ የሚሠሩ ንቅናቄዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ድምጻቸውን እያስተጋቡ ነው።

በመግለጫው ላይ በቁጥር 12 እና 13 የሰፈሩት ውሳኔዎች እንደሚከተለው ተቀምጠዋል። እነዚህንና ሌሎች በመግለጫው የተካተቱ “ውሳኔዎችና ፈትዋዎችን የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንዲያስፈጽምልን በአንድ ድምጽ ወስነናል” ሲል የዑለማዎች ጉባዔ መደምደሚያው ላይ ይጠይቃል።

  • 12. በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በግርዛት ስም ከሸሪዓችን በተጻረረ መልኩ በሴቶች እህቶቻችን ላይ የሚደረግ ኢሰብአዊ የሆነ ፈርኦናዊ ግርዛት (የሴት ልጅ ብልት ትልተላ) በሸሪዓችን የተወገዘ ተግባር መሆኑን እናሳውቃለን።
  • 13. ሸሪዓዊው ግርዛት ዋጂብ ወይም ሱና ነው የሚል የኡለማዎች የሐሳብ ልዩነት ቢኖርም ግርዛት ከተደረገም ባለሙያ በሆነ ሐኪም አማካኝነት ብቻ መደረግ እንዳለበት ተስማምተናል።

የሴት ልጅ ግርዛት ሕገ ወጥ ሆኖ ሳለ “ከተደረገም ባለሙያ በሆነ ሐኪም አማካይነት ብቻ መደረግ እንዳለበት ተስማምተናል” የሚለው ውሳኔ በሕግ ዐይን እንዴት ይታያል?

የሴት ልጅ ግርዛት በወንጀል የሚያስቀጣ ሆኖ ሳለ፣ ይህንን የሚፈጽም “ባለሙያ የሆነ ሐኪም” ተብሎ መቀመጡ ተቃርኖ አይፈጥርም?

የሴት ልጅ ግርዛትን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስወገድ በሚደረግው ንቅናቄ የሃይማኖት ተቋማት ሊኖራቸው ከሚገባው ሚና ጋር አይጣረስም? የሚሉትና ተያያዥ ነጥቦች በዚህ ዘገባ ይዳሰሳሉ።

የአገሪቱ ሕግ በ ‘ዑለማዎች ፈትዋ’ ሊጣስ ይችላል?

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ፣ በሕገ መንግሥት እንዲሁም ኢትዮጵያ ፈርማ ባጸደቀቻቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች የሴት ልጅ ግርዛት ወንጀል መሆኑ፣ ሰብአዊ መብትን እንደሚጥስ፣ የከፋ የጤና እክል እንደሚያስከትልም ተቀምጧል።

በወሎ ዩኒቨርስቲ የኢስላሚክ ሕግ መምህርት የሆነችው ሀሊፈት አይመሐመድ ዩሱፍ እንደምትናገረው፣ የዑለማዎችን ጉባዔ ተከትሎ የወጣው የአቋም መግለጫ የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነውን ሕገ መንግሥት፣ የወንጀል ሕግን እንዲሁም አገሪቱ የተስማማችባቸው የሰብአዊ መብት ሰነዶችንም የሚጥስ ነው።

ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መብት ስምምነት (CRC) እና በሴቶች ላይ የሚደርስ ማንኛውንም መድልዎ ለማስወገድ የተፈረው ስምምነት (Convention on the Elimination of All Forms of Discrimination Against Women ወይም CEDAW) ፈርማለች።

በአፍሪካ ኅብረት የተዘጋጀው በአህጉሪቱ የሴቶችን መብት ለማስከበር የተፈረመው ስምምነት (Maputo Protocol) ፈራሚም ናት።

‘ሲአርሲ’ በአንቀጽ 24 ላይ ግርዛትን ጨምሮ በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ማንኛውም ጥቃቶችን ይከለክላል።

በ‘ሲዶው’ አንቀጽ 2 ላይ ደግሞ የጤና መብትን መግፈፍን ጨምሮ በሴቶች ላይ የሚደረግ መድልዎን ይከለክላል።

በ ‘ማፑቶ ፕሮቶኮል’ አንቀጽ 5 የሴት ልጅ ግርዛት የተከለከለ ነው።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና የወንጀል ሕግ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች ቀጣዮቹ ናቸው።

  • የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 565- ግርዛትን ወንጀል አድርጎ አስቀምጧል።
  • የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 561-570- በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሴቶችና ሕጻናት ሕይወት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ሴትን መግረዝ፣ የሴትን ብልት መስፋት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን የሚከለክሉ ድንጋጌዎች እንዳይፈጸሙ ማነሳሳት፣ የሰውን ሕይወት ለአደጋ ማጋለጥ በወንጀልነት ተቀምጠዋል።
  • የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 16- ማንኛውም ሰው በአካሉ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት እንዳለው ይገልጻል።
  • የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 35 (4)- መንግሥት ሴቶች ከጎጂ ባሕል ተጽዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን ማስከበር እንዳለበትና ሴቶችን የሚጨቁኑ፣ በአካል ወይም በአእምሮ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶች የተከለከሉ መሆናቸው ተደንግጓል።
  • የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (1)- ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ሕገ መንግሥቱ የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ይገልጻል።
  • የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (4)- ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል መሆናቸውን ይደነግጋል።

የሆርን ሆራይዘን አጋር መሥራችና ምክትል ኃላፊ ሱዓድ አሕመድ እንደምትለው፣ የሴት ልጅ ግርዛትን ወንጀል አድርጎ የሦስት ወር እስራትና የ500 ብር ቅጣት የሚጥለው ሕግ፣ ቅጣቱን ከፍ ለማድረግ መሻሻል አለበት በሚለው ላይ መወያየት በሚያስፈልግበት ወቅት በዑለማዎች የተላለፈው ውሳኔ ግርዛትን ለመግታት የተደረገውን ጥረት የሚጣረስ ነው ትላለች።

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 25 የሰጠውን የእኩልነት መብት፣ በአንቀጽ 35 የሰጠውን የሴቶች መብት እንዲሁም በአንቀጽ 36 የሰጠውን የሕጻናት መብት የሚነጥቅ ነው ስትል ታስረዳለች።

‘አርቲክል 35’ የተባለው የጾታ እኩልነት ንቅናቄ፣ ከሙስሊም ሴቶች በተሰጠ ጥቆማ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እያደረገ ይገኛል።

የ ‘አርቲክል 35’ መሥራች ኪያ ዓሊ፣ “ግርዛት ከተደረገም ባለሙያ በሆነ ሐኪም” በሚል መቀመጡን በመጥቀስ “የሕክምና ባለሙያ በሚል ሰበብ ወንጀልን የሚያበረታታ ነው” ትላለች።

የዓለም ጤና ድርጅት እአአ በ2017 ባወጣው ሪፖርት እና በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትር ሰርኩላር መሠረት የሕክምና ባለሙያዎች የሴት ልጅ ግርዛትን መፈጸም እንደማይችሉና ፈጽሞ የተገኘም በሕግ ተጠያቂ እንሚሆን መጠቀሱን በማስረጃነት ታጣቅሳለች።

የዑለማዎች ምክር ቤት ምን አለ?

በአገሪቱ ሕግ ግርዛት የተከለከለ ሆኖ ሳለ ለግርዛት ይሁንታ የሚሰጥ መግለጫ ለምን ወጣ? በሚል የኢትዮጵያ ዑለማዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም የዐብይ ፈትዋ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሼኽ ሙሐመድ ዘይን ዘሕረዲንን ጠይቀናል።

እሳቸው እንደሚሉት፣ ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት ግርዛትን በሚደግፉና በሚነቅፉ ዑለማዎች መካከል የሐሳብ ልዩነት የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻ ግን መግለጫው እንዲወጣ ውሳኔ ተላልፏል።

“የኢትዮጵያ ሕግ ስለከለከለ ሃይማኖቱ አይቀርም። የኢትዮጵያ ሕግ አይደለም፣ የዓለም ሕግ፣ የመሬት ሕግ ተነስቶ ክልክል ነው ቢል ሃይማኖቱ የፈቀደው ክልክል ይሆናል ማለት አይደለም” ሲሉ ላነሳልናቸው ሕግን የመቃረን ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

የወጣው መግለጫ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር “በውይይት ላይ ነው” ከሚል በዘለለ ማብራሪያ ሊሰጡን አልፈቀዱም።

የጤና ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍሎችም ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በመግለጫው ላይ ያለውን አስተያየት ከቢቢሲ ተጠይቆ፣ “አሁን ላይ ተቋሙ ምንም ማለት አይችልም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

የዑለማዎች ምክር ቤት ለምን ራሱን ይቃረናል?

የሴት ልጅ ግርዛት ላይ ንቅናቄ የሚያካሂደው ‘ኦርኪድ ፕሮጀክት’ በ2010 ዓ. ም. ባወጣው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ15-49 ከሆኑት ሴቶች መካከል 65.2% የሚሆኑት ሴቶች ለሴት ልጅ ግርዛት የተጋለጡ ናቸው፡፡

“ለሴት ልጅ ግርዛት በከፍተኛ ደረጃ ተጋለጭ የሆኑት አካባቢዎች በብዛት የሚገኙት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል” እንደሆነ ጠቅሶ፣ ከ15-40 ዕድሜ ካላቸውና ከተገረዙ እናቶች ከተወለዱ ሴት ልጆች መካከል 64% ዕድሜያቸው አራት ዓመት ሳይሞላ መገረዛቸውን ይገልጻል።

በአብዛኛው በባሕላዊ ገራዦች የሴት ልጅ ግርዛት እንደሚከናወን እና የሴት ልጅን ብልት “የተወሰነውን ስጋ ማስወገድ እና መቁረጥ” የተለመደው የሴት ልጅ ግርዛት ዓይነት እንደሆነ በጥናቱ ተቀምጧል።

ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች፣ በዑለማዎች ውሳኔ ላይ ግርዛት “ኢ-ሰብአዊ” ተብሎ ከተገለጸ በኋላ “መደረግ ካለበት ባለሙያ በሆነ ሐኪም” የሚለው አገላለጽ እርስ በራሱ የሚቃረን ነው ይላሉ።

ግርዛትን ‘በሕክምና ባለሙያ’ ማከናወን የሚለውን በተመለከተ የኦርኪድ ፕሮጀክት ዳሰሳ እንደሚለው፣ በጤና ባለሙያዎች የሚደረግ ግርዛት በወንጀል ሕጉ ላይ በተለየ ሁኔታ ባይጠቀስም፣ ከአንቀጽ 561-570 በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው ሁኔታ ሁሉንም ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ፈጻሚ አካላትን ስለሚያወግዝ የክምና ባለሙያዎችንም ማጠቃለሉ አይቀርም።

ከዚህም ባሻገር በሕጉ መሻሻል አለባቸው ብሎ ከጠቀሳቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ይህ ነው።

“ሕጉ በሕክምና የታገዘ የሴቶች ግርዛትን ግልጽ የሆነ ትርጉም በመስጠት፣ የትኛውም ዓይነት የሕክምና ባለሙያ በየትኛውም አካባቢ ላይ ይህንን ድርጊት ቢፈጽም፣ ሊፈጽም ቢሞክር ወይም ቢያግዝ ጠበቅ ያለ ቅጣት ሊከተለው ይገባል” በማለት ምክረ ሐሳብ ይሰጣል።

“በሕክምና የታገዘ የሴት ልጅ ግርዛትን” በተመለከተ ባለው መረጃ፣ ዕድሜያቸው ከ15-49 ከሆኑ ሴቶች መካከል 1% ያህሉ እና ዕድሜያቸው ከ0-14 ዓመት የሆኑ ሴቶች 1.9% ያህሉ ብቻ ወደ ሕክምና ተቋማት መወሰዳቸውን ይጠቅሳል።

ማንኛውም ዓይነት ግርዛት ተቀባይነት እንደሌለው በአጽንኦት የምትገልጸው ሱዓድ፣ የዑለማዎች የውሳኔ መግለጫ “ባለሙያ የሆነ ሐኪም” የሚል አገላለጽ መጠቀሙ፣ የሕክምና ተቋማት ወይም የሕክምና ባለሙያዎች ከአግባብ ውጭ ግርዛትን እንዲፈጽሙ መንገድ ያመቻቻል ትላለች።

“የሕክምና ተቋማት ይህንን ተግባር አንፈጽምም ሲሉ ደግሞ ማኅበረሰቡ ወደሚያውቀውና ወደለመደው በተለምዶ ግርዛት ወደሚፈጽሙ ሰዎች ይሄዳል። ሴቶችና ሕጻናትን ለጤና እክል ይዳርጋል” ትላለች ሱዓድ።

የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት እአአ በ2016 ባወጣው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ 25% የሚሆኑ ሴቶች ምን ዓይነት ግርዛት እንደተፈጸመባቸው አያውቁም።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም ሱዓድ “በምን ዓይነት ሁኔታ፣ በማን፣ እንዴት ዓይነት ግርዛት ተፈጸመ የሚሉት መረጃዎች ትርጉም አልባ ናቸው። የሴት ልጅ ብልት አካልን መቁረጥ ወይም መስፋት በሐኪምም ተደረገ በተለምዶ፣ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ሕመም አይለውጠውም” ስትል ታስረዳለች።

“የትኛውም ዓይነት ግርዛት ተቀባይነት የለውም። ሊኖረውም አይገባም” የምትለው ሀሊፈት፣ ከፍተኛ የደም መፍሰስ፣ ኢንፌክሽን፣ ከወሊድ ጋር ለሚያያዝ ችግር መጋለጥና ሕይወትን ማጣትም የሚያስከትል መሆኑን ትናገራለች።

“ሕጋዊ ግርዛት’’ የሚባል አለ?

የዑለማዎች ምክር ቤት ውሳኔ በማያሻማ ሁኔታ ወንጀል የሆነን ተግባር ለማባበልና ግማሽ ሕጋዊነትን ለመስጠት የሞከረ እንደሚመስል ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ኪያ እንደምትለው፣ የሴት ልጅ ግርዛትን በሚደግፉና በሚቃወሙ ዑለማዎች መካከል ከተፈጠረው የሐሳብ ልዩነት በመነሳት ምናልባት “መሀል ላይ ያለውን መንገድ ለማምጣት” በሚል “በሕክምና ባለሙያ” ይደረግ የሚለው ተነስቶ ሊሆን ይችላል።

ሆኖም ግን የሴት ልጅ ግርዛት “የሚያስከትለውን ዘላቂ ጉዳት ማስቆም አይቻልም” ትላለች።

አያይዛም “ድርጊቱ የሚፈጸመው ሕጻናት ላይ መሆኑ የከፋ ያደርገዋል። ሴት ልጅን ዕድሜዋን በሙላ የሚከተላት ጉዳት ነው። በማንም ቢፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው” ስትል ታስረዳለች።

በሌላ በኩል ደግሞ የሕክምና ባለሙያዎችን “በሴት ልጅ ግርዛት እንዲሳተፉ የሚያደርግና ሕጋዊ መልክ የሚሰጥ” ስለሆነ የጤና ሚኒስትር ካወጣው ሕግና መመሪያ አንጻር ምላሽ መስጠት እንዳለበት ኪያ ታሳስባለች።

የሴት ልጅ ግርዛትን ማውገዝ

በአገር አቀፍ ደረጃ ግርዛትን ለማስወገድ የሚደረጉ ንቅናቄዎች ታሳቢ ከሚያደርጓቸው አካላት መካከል የሃይማኖት ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው።

የሃይማኖት ተቋማት በማኅበረሰቡ ዘንድ ካላቸው ተደማጭነትና ተቀባይነት አንጻር መልዕክት ሲያስተላልፉ ማኅበረሰቡ ድርጊቱን መፈጸም “አስፈላጊ ነው” ብሎ እንደሚወስድ ኪያ ትናገራለች።

ድርጊቱን አለመፈጸም “እንደ ነውርና እንደ ኀጥአትም ጭምር እንደሚቆጠር” ሱዓት ትገልጻለች። ሀሊፈትም “ጎጂ ድርጊቶች በሃይማኖት ተደግፈው እንዲቀጥሉ” ያደርጋል ስትል ታስረዳለች።

በዑለማዎች መካከል የሐሳብ ልዩነት እያለ የሴት ልጅ ግርዛትን የሚያወግዝ መግለጫ ለምን አልወጣም? በሚል የተጠየቁት ሼኽ ሙሐመድ ዘይን ዘሕረዲን በበኩላቸው “ግርዛት ይቅር የሚል መልዕክት ማስተላለፍ አልቻልንም። አንችልምም። ትልቁ አስተማሪ ይቅር አላሉም። ከተደረገ ጥንቃቄ ይደረግ ነው ያሉት። እኛም ያንን ነው የደገምነው” ሲሉ ሃይማኖታዊ መከራከሪያ አቅርበዋል።

ይህን ሃይማኖታዊ መከራከሪያ የኢስላሚክ ሕግ መምህርቷ ሀሊፈት አትቀበለውም። “የሴት ልጅ ግርዛት በእስልምና ግዴታ አይደለም። በቁርዓን እና በሱና ላይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለውም” ትላለች።

ከዚህ በተቃራኒው የሚነሳው ሃይማኖታዊ መከራከሪያ መነሻ ያደረገው “ደካማ ወይም ልል (በአረብኛ ደኢፍ) ሐዲስን በመጥቀስ ነው” ስትልም ታክላለች።

ይህንንም “ጠንካራ መሠረት የሌለው፣ የሴቷን ሰብአዊ መብትና እስላማዊ መብትም የሚጥስ፣ ከቁርዓን እና ከሱና ጋር የሚጣረስ” በማለት ትገልጸዋለች።

የዑለማዎች ምክር ቤት ትክክለኛ አቋም የቱ ነው?

የኢትዮጵያ ዑለማዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የዓቢይ ፈትዋ ኮሚቴ አባል ሼኽ ሙሐመድ ዘይን ዘሕረዲን፣ “ሴት ልጅ ለምን ትገረዛለች ብሎ የሚያወግዝ መረጃ የለም። ብትገረዝ ከፈጣሪ ዘንድ ትልቅ ምንዳ አላት የሚልም ማስረጃ የለም” ሲሉ ያስረዳሉ።

በእሳቸው ማብራሪያ መሠረት ሴት ልጅ “ካልተገረዘች ወንጀል አለባት። በፈጣሪ ዘንድ ጀነት ትከለከላለች። ገሃነም ትወረወራለች የሚል በቁርዓንም በሐዲስም የለም” ነገር ግን “ግርዛትን የሚያወግዝም መረጃ” የለም በማለት ይከራከራሉ።

የሴት ልጅ ግርዛትን “ግዴታ ነው” ያሉ ዑለማዎች “ማስረጃቸው ጠንካራ አልነበረም” ቢሉም፣ “ነብዩ መሐመድ በአካባቢያቸው ሴት ልጆችን የምትገርዝ ሴትን፣ ሥራዋ ይሄ ከሆነ ጥሯት አሉና፣ ገርዢ ብለው ትዕዛዝ አልሰጧትም። ከገረዝሽ አደራሽን ከሥር ዝቅ ያለ ሳይሆን የሽታ ያህል ጫፉን ብቻ ንኪ (በአረብኛ አሺሚሃ) አሏት” ሲሉ ሃይማኖታዊ መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ።

ይህንን መነሻ አድርገው “መገረዝ ካለበት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል” በሚል ይከራከራሉ።

ሀሊፈት ከዚህ በተቃራኒው እንደ ማስረጃ የተጠቀሰው ሐዲስ “ደካማ ወይም ልል” የሚባል እንደሆነ በመጥቀስ፣ “የሴት ልጅ ወሲባዊ ደስታ የማግኘት መብት በቁርዓን እና በሱና ላይ የተቀመጠ ነው። ይሄንን የሚጻረር ነው። በቁርዓን እና በሐዲስ ላይ የሰው ልጅ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመፈጸም፣ አላህ የሰጠውን አካላዊ ቁመና አለመቀየር ተቀምጧል። የሴት ልጅ ግርዛት እነዚህንም ይጥሳል” ትላለች።

ሱዓድም ከሀሊፈት ጋር ትስማማለች። “በዓለም ላይ ያሉ ዑለማዎች የሴት ልጅ ግርዛት እስላማዊ የሃይማኖት መሠረት የሌለው መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸዋል” ትላለች።

እንደ ማስረጃ የምትጠቅሰውም፣ እአአ በ2006 ታርጌት በተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና በPro Islamic Affairs Against FGM በአል አዝሀር ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ነው።

“ከኢትዮጵያ ሼኽ መሐመድ ደረሳ ተገኝተዋል። የተስተጋባው ሐሳብ የሴት ልጅ ግርዛትን የሚከለክል ነው” ስትል ትገልጻለች።

በዓለም ጥንታዊ ከሆኑ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ በሆነው የግብፁ አል አዝሀር ዩኒቨርስቲ እና 57 አባል አገራት ባሉት Organization of Islamic Cooperation ግርዛት ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ብይን ተሰጥቷል።

ሀሊፈት እንደምትለው “ጠንካራ ወይም አስተማማኝ ማስረጃ የሌለውና ልል ሐዲስ ላይ ተመሥርቶ ሃይማኖት ከባህል ጎን ለጎን የተተረጎመ ነው”።

አያይዛም የሴት ልጅ ግርዛትን በተመለከተ “ግልጽ የሆነ ዓለም አቀፍ ስምምነት ያለው ሱና ወይም ሐዲስ አለመኖሩ ችግር ያለበት ነው ተብሎ እንዲከለከል አድርጎታል” ስትል ታስረዳለች።

በዑለማዎች ጉባዔ ላይ በወጣው መግለጫ በቁጥር 12 ላይ “ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተብሎ የተቀመጠውም ለዚያ ነው” ትላለች።

ሼኽ ሙሐመድ ዘይን ዘሕረዲን ከዚህ የተለየ ሐሳብ አላቸው።

የተላለፈው ውሳኔ “ለመጀመሪያ ጊዜ በድፍረት የወጣ፣ የሴት ልጅ ግርዛትን ከግዴታነት ወደ ቢደረግም ባይደረግም ችግር የለውም ወደማለት የመጣ፣ በጣም ጠንካራ አቋም ያለው ፈትዋ ነው ብለን ነው የምናስበው” ሲሉ ይገልጹታል።

“አብዛኛው ማኅበረሰብ ግርዛትን እየተወ ነው የመጣው” ያሉት ሼኽ ሙሐመድ ዘይን ዘሕረዲን፣ “እኛም ወደ መገፋፋቱ መሄድ ነው የጀመርነው። ቀስ በቀስ ይቀራል ብለን ነው የምናምነው” በማለት ገልጸዋል።

አሁን ላይ የሴት ልጅ ግርዛትን ይሁንታ የሚሰጥ ውሳኔ ማስተላለፍና በውሳኔው የሴቶችን ዕይታ አለማካተትን በተመለከተ ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ “ፈትዋው እዚህ መድረሱ ጥሩ ነገር ነው። ከዚህ በኋላ ቢተው ለምን ተዋችሁ? ብሎ የሚያወግዝ የለ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

“የሴቶችን ሰውነት መቆጣጠር”

ሀሊፈት፣ ሱዓድ እና ኪያ ግን የወጣው መግለጫ አሁናዊ አደጋ የደቀነ እንደሆነ ይስማሙበታል። ሰብአዊ መብትና ሕግን የሚጥስ እንዲሁም የሴት ልጅ ግርዛትን “ሃይማኖታዊ ወይም ተቋማዊ ይሁንታ” የሚሰጥ እንደሆነ ያሰምሩበታል።

እስካሁን ድረስ በመንግሥት ተቋማት በኩል በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ በመንግሥት አካለት፣ በሲቪክ ማኅበራትና በሌሎችም ግርዛትን ለማስወገድ በሚሠሩ ድርጅቶች በኩል ምላሽ እንዲሰጥ ይጠይቃሉ።

“የሴቶችን ሰውነት ለመቆጣጠር መሞከር ነው። የሚያሳዝነው ያለውን ባህላዊ ልምድ ለማስቀጠልና ለአባታዊ ሥርዓት [ፓትሪያርኪ] ተብሎ እስከየትኛው ጥግ ድረስ እንደሚኬድ ነው የሚያሳየው” ትላለች ሀሊፈት።

የፍትሕ ሚኒስትርና የሴቶችና ማኅበራዊ ሚኒስትር እንዲሁም ሙስሊሙ ማኅበሰረብ ውሳኔውን በግልጽ ማውገዝ አለበት” የምትለው ሀሊፈት፣ የወጣው መግለጫ “እንደ መደበኛ ታይቶ ዝም ከተባለ ከዚህ የባሰ ነገር ያስከትላል” ስትል ታሳስባለች።

ኪያ እንደምትለው፣ የሴቶችን ሕጋዊ መብትና እኩልነት ከመግፈፍም ባሻገር “አካላቸውና ፍላጎቶታቸውን ለመቆጣጠርና በራስ ላይ የመወሰን ውክልናን” መንጠቅ ነው።

“ሴት ማንም ሊያዝበት በማይችለው በተፈጥሯዊ አካሏ በራሷ እንኳን እንዳታዝ የማድረግ የአባታዊ ሥርዓት ቅጥያ ነው” ስትል ታክላለች።

ሱዓድ በበኩሏ፣ ይህ “የሴቶችን ሰውነት ለመቆጣጠር መሞከር ነው። አባታዊ ሥርዓትን ለማስቀጠል እስከየትኛው ጥግ ድረስ እንደሚኬድ ነው የሚያሳየው” ትላለች።

በዚህ ውሳኔ የሚስተጋባው “የሃይማኖት ግዴታን ማስፈጸም” ሳይሆን “የሴቶችን ሰውነት መቆጣጠር” ብቻ ነው ስትል ውሳኔውን በብርቱ ትነቅፋለች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )