ዛሬ የአማራ ክልል መንግሥት ይፋዊ መግለጫ ሰጠ።

የክልሉ መንግሥት ፥ ” ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ መማር የተሳነው ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሓት) የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል ” ሲል ከሷል።

” ህወሓት የአማራ ክልል ተማሪዎችን መማሪያ መጽሐፍ እንደ ሰበብ ተጠቅሞ በይፋ ጦርነት ማወጁና መቀስቀሱ ይታወቃል ” ሲል አስታውሷል።

የአማራ ክልል መንግሥት ህወሓትን ” የመላ ኢትዮጵያ ጠላትና የደኅንነት ስጋት ” እንደሆነ ገልጾ ” ባለፉት 3 ዙሮች ከተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት ትምህርት ሊወስድ ይችል ይሆናል በሚል ጭላንጭል ተስፋ የፌዴራል መንግሥት እጅግ እልህ አስጨራሽ ትዕግስት ተላብሶ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደረግ ቆይቷል ” ብሏል።

” የአማራ ክልል መንግሥትም በተደጋጋሚ ከትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር ጋር በፌዴራል መንግሥት አማካኝነት ውይይት ለማድረግ በርካታ ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም ህወሓት ይህን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረምና ዛታ አካባቢዎች ላይ ወረራ ፈፅሟል ” ሲል ገልጿል።

” ህወሓት ወረራ የፈፀመባቸው ፦

  • የራያ አላማጣ፣
  • ራያ ባላ፣
  • ኦፍላ፣
  • ኮረምና ዛታ እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት አካባቢዎች የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊት በነበሩ አሥተዳደራዊ መዋቅርና አደረጃጀት በኀይል ጠቅልሎ ከመውሰድ ጀምሮ የዘር ማጥፋት ወንጀል እስከመፈፀም ድረስ አሰቃቂ ጥፋት የፈፀመባቸው አካባቢዎች  ናቸው ” ብሏል።

” ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ህወሓት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የከፈተውን አሰቃቂ ጥቃት ተከትሎ ከተቀሰቀሰው ጦርነት በኃላ አካባቢዎቹ በጉልበት ተገፎባቸው የነበረውን ራሳቸውን የማሥተዳደር ነጻነት መቀዳጀት እንደቻሉ ” የአማራ ክልል መንግሥት ገልጿል።

በኃላም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ፤ ህወሓት ግን ስምምነቱን በማክበር በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻውን ከመወጣት ይልቅ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ በመጣስ የተለያዩ ጥፋቶችን ሲፈጽም እንደቆየ አመላክቷል።

” አሁንም እየፈጸመ ይገኛል ” ብሏል።

የአማራ ክልል መንግሥት ፥ ህወሓት ደም አፋሳሽ የሆነ ጦርነት ለማድረግ ከመሞከር እንዲታቀብ እና የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲያከብር አሳስቧል።

” በአጭር ጊዜ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ ” ሲል ጠይቋል።

” ይህ የማይሆን ከሆነ የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድምና እህት ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ በመሆን ሀገርን ከማፍረስ መታደግና ሕዝባችንንም ከጥቃት ለመከላከል እንገደዳለን ” ሲል አስጠንቅቋል።

(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(@tikvahethiopia)