ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚዎች ይለያሉ

ዛሬ ረቡዕ ጥር 29/2016 ዓ.ም. ምሽት 2 እና 5 ሰዓት ላይ በሚደረጉ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ተፋላሚዎች ይለያሉ።

በግማሽ ፍጻሜው ቀድመው የሚገናኙት ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው።

የናይጄሪያ የፊት መስመር ተጫዋች ቪክተር ኦሲመሄን በጉዳት ተሰልፎ የመጫወቱ ጉዳይ አጣራጣሪ ሆኗል።

ባለፈው ዓመት በጣሊያን ሴሪአ ቁጥር አንድ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የውድድር ዓመቱን የጨረሰው ቪክተር ኦሲመሄን በአፍሪካ ዋንጫም የናይጄሪያን የፊት መስመር ሲመራ ቆይቷል።

በ24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ጎል ያስቆጠረው ኦሲመሄን የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ የሆነው በሆድ ህመም መሆኑ የቡድኑ ሐኪሞች ገልጸዋል።

የናይጄሪያ ተጋጣሚ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ በዚህ ውድድር ደካማ አጀማመሯን እያሻሻለች ከዚህ ደረጃ ላይ ደርሳለች።

ባፋና ባፋናዎች በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታቸው በማሊ 2 ለ 0 ተሸንፈው የነበረ ቢሆንም፣ በሂደት መሻሻልን አሳይተው ሞሮኮ እና ኬፕ ቨርድን ጥለው ነው ከዚህ የደረሱት።

የዚህ ግጥሚያ አሸናፊነት ሰፊ ግምት ለናይጄሪያ የተሰጠ ቢሆንም ባፋና ባፋናዎች ድንቅ ብቃት እያሳየ በሚገኘው አምበል እና ግብ ጠባቂያቸው ሮንዌል ዊሊያምስ ታግዘው በቀላሉ እጅ የሚሰጡ አይሆንም።

የደቡብ አፍሪካው ግብ ጠባቂ በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ከኬፕ ቨርድ ጋር በፍጹም ቅጣት ምት ሲለያዩ አራት ኳሶችን በማዳን ታሪክ ሠርቷል።

ከናይጄሪያ እና ከደቡብ አፍሪካ ጨዋታ በኋላ አስተናጋጇ አይቮሪ ኮስት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ዕድለኛ የሆነ ቡድን ቢኖረው የአይቮሪ ኮስት ብሔራዊ ቡድን ነው። በምድብ ጨዋታው አንድ ጨዋታ ብቻ አሸንፎ፤ በሁለት ጨዋታ ተሸንፎ እና የግብ ዕዳ ውስጥ ሆኖ ነው ምርጥ ሦስተኛ በመሆን ከምድቡ ማለፈ የቻለው።

ከምድቡ ካለፈ በኋላ በጥሎ ማለፍ ሴኔጋልን፣ በሩብ ፍጻሜው ደግሞ ማሊን አሸንፎ ነው ከግማሽ ፍጻሜው የደረሰው።

በዚህ ውድድር ብዙ ግምት ያልተሰጣት ዴሞክራቲክ ኮንጎ አስተናጋጇን በቃሽ የምትልበት ጨዋታ ይሆን?

ግብፅን በጥሎ ማለፉ አሸንፋ፣ ጊኒን በሩብ ፍጻሜው በመርታት ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው ዴሞክራቲክ ኮንጎ ዛሬ ምሽት አስተናጋጇን እንደምትፈትን ይጠበቃል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnnn

ምንጭ (ቢቢሲ)