“ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ልጆቻችንን ለማስመዘገብ ስንሄድ ለሚቀመጡበት ወንበር 6 ሺሕ ብር ክፈሉ እያሉን ነው ” – የተማሪ ወላጆች…….

“ እኔ የማውቀው ችግር የለም ” – የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ

በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዙሪያ የሚገኙ ወላጆች በጸጥታው ችግር በአካባቢያቸው መማር ያልቻሉ ልጆቻቸውን በባህር ዳር ከተማ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ለማስመዝገብ ሲሄዱ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ገንዘብ ክፈሉ እየተባሉ መሆኑን ለቲካቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

የተማሪ ወላጆች በዝርዝር ምን አሉ ?

“ በጸጥታው ችግር ምክንያት በባህር ዳር ዙሪያ ያሉ ወረዳዎች ትምህርት መቀጠል አልቻሉም፡፡

ጫናውን ተቋቁመን አንጻራዊ ሰላም ወዳለበት ወደ ባህር ዳር ልጆቻችንን ለማስመዘገብ መሸኛ ይዘን ስንሄድ ተማሪዎቹ የሚቀመጡበት አንድ ወንበር ለሦስት ይዛችሁ ስትመጡ ብቻ ነው የሚመዘገቡት እያሉን ነው።

በወላጅ ተለምነው በድርድር ወደ ገንዘብ ይቀይሩታል፡፡

አንድን ሰው 2 ሺሕ ብር፣ ለአንድ ወንበር 6 ሺሕ ብር ይጠይቃሉ፡፡ ልጆቻችን በጭንቀት ውስጥ ስለሆኑ ገንዘቡን በመክፈል ምዝገባ አካሂደናል፡፡

ተማሪዎቹ ቤተሰቦቻቸው በሚገብሩት ግብር የተሰሩ ትምህርት ቤቶች ነበሯቸው ፤ በጦርነቱ ምክንያት ስላልቻሉ ነው የመጡት። ከዚሁ ክልል ውስጥ ነው፡፡

ችግሩ ደግሞ የመጣው እራሳቸው መቆጣጠር ባለመቻላቸው ነው መስዋዕትነት እየከፈልን ያለነው። ችግሩን ተቋቁመን ስንሄድ አበረታትተው መቀበል ሲገባቸው ገንዘብ ያስከፍላሉ፡፡

ገንዘቡን ወንበር ይገዙበታል ወይ የሚለውም አጠያያቂ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ገንዘቡን ስንከፍል ደረሰኝ እንኳ አይሰጡንም፡፡

ክፍያውን የሚቀበሉት ለመመዝገብ የተወከሉ ሰዎች ናቸው፡፡ እንዲህ የሚደረገውም በባህር ዳር በሚገኙ ሃይስኩል ትምህርት ቤቶች ነው፡፡ ዞረን በጠየቅንባው ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ አሰራር ገጥሞናል፡፡

በጸጥታ ችግር መማር ሳይችሉ ከሚቀሩ አንጻራዊ ሰላም ወዳለበት አጎራባች ቦታ ሲሄዱ መባል የነበረበት ‘ እንኳን ደኀና መጣችሁ ‘ ነበር፡፡ ነገር ግን ተማሪዎቹ ሲሄዱ ሌላ ጫና እየተፈጠረ ነው፡፡

የወንበር ችግር ገጥሟቸውም አይመስለንም፡፡ ወላጅ ላይ የተለዬ ምሬትና ጫና ከመፍጠር በመተዛዘን ተማሪዎቹን ቢያስተናግዷቸው መልካም ነው፡፡ ገንዘቡን መክፈል ያልቻሉ መመዘገብ አልቻሉም። ” ብለዋል።

ለተነሳው ለዚህ ቅሬታ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያን ጠይቋል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ ኃላፊ በሰጡት ቃል፣ “ ባሕር ዳር ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሊመዘገብ መጥቶ ሁሉም ትምህርት ቤት ጋር ‘ ለሦስት፤ ለሦስት አንድ ወንበር አምጡ ወይም ወንበር ይዛችሁ ካልመጣችሁ አላስተናግድም ‘ ያለ ትምህርት ቤት የለም። ” ብለዋል።

“ እኛ ጋ ‘ ችግር ደረሰብኝ ‘ ብሎ የመጣም የለም፡፡ ‘ ወንበር አምጣ ተብያለሁ ‘ ብሎ መጥቶ የጠየቀኝ ተማሪም የለም፡፡ ሁሉንም ትምህርት ቤት እየዞርኩ እያየሁ ነው፡፡ የትኛውም ትምህርት ቤት ላይ እየተመዘገቡ ነው። ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ አልፎ አልፎ አንመዘግብም ያሏቸውን እራሴ እየመራሁ ነው ያስመዘገብኳቸው፡፡ ትምህርት ቤቱ የማህበረሰብ ተሳትፎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ግን አግሪመንት ወስዶ ማህበረሰቡ የፈረመውን ነው እያስከፈለ ያለው። ” ሲሉ አክለዋል።

“ እኔ የማውቀው ችግር የለም ” ያለው ትምህርት መምሪያው፣ እንዲህ የሚያደርጉ ትምህርት ቤቶች ካሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቢያሳውቁት ታች ድረስ ወርዶ እርማት እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

ወላጆች መሰል ችግር ያለባቸውን ቦታዎች ለትምህርት መምሪያ መጠቆም እንደሚችሉ ተመላክቷል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (@tikvahethiopia)