ከ50 በላይ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች በሱዳን ኃይሎች እንደምርኮኛ መያዛቸው ተነገረ

በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ ለማቋረጥ ሲሞክሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ወጣት ስደተኞች ለአንድ ዓመት በቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በሚገኙ ተዋጊ ኃይሎች እንደ ምርኮኛ ተይዘው እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ።

በቅርቡ በርካታ ወጣቶች ከጭነት መኪና በሚወርዱበት ወቅት ሲደበደቡ እና ሲንገላቱ የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።

አብዛኞቹ ኤርትራውያን እና አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ሊቢያ ለመሻገር ሲሞክሩ ሱዳን ላይ የተያዙ እንደሆኑ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የታጋች ቤተሰቦች ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል ግጭት ተቀስቅሶ አገሪቱ አገሪቱ ከባድ ቀውስ ውስጥ መግባቷ ይታወቃል።

ሚያዝያ 7/2016 ዓ.ም. በጄኔራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው የሱዳን ሠራዊት እና ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሱዳን በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች።

ሁለቱም ኃይሎች አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል ተቆጣጥረው የበላይነት ለመያዝ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት እና ለስደት ተዳርገዋል።

ከእነዚህም መካከል ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተዋጊ ኃይሎች በተለይም በፈጥኖ ደራሹ ቡድን እንደተያዙ እና በሱዳን ጦር አባልነት በምርኮ መያዛቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ እየተሰራጩ ባሉ ቪዲዮች ላይም እነዚህን ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውን ስደተኞች እየታዩ መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሰ ገልጸዋል።

በተሰራጩት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ የሚታዩ ወጣቶችን መለየት የቻሉ ዘመዶቻቸው ግን በፈጥኖ ደራሹ ኃይል እጅ የሚገኙት ወጣቶች “ምርኮኞች ሳይሆኑ ተራ ስደተኞች” ናቸው ይላሉ።

ቢቢሲ ስደተኞቹ የታገቱበትን ስፍራ እና ሁኔታ ከሦስተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

በቪዲዮው ላይ ከሚታዩት መካከል አንዱ የሆነው ማትዮስ ከጓደኛው ጋር በኅዳር ወር በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ ለመሻገር በሚል ከአዲስ አበባ እንደተነሱ ባለቤቱ ትምኒት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ወሬያቸው ለሦስት ሳምንታት ጠፍቶ ከቆየ በኋላ ማትዮስ በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ ለሚስቱ ደውሎ በሱዳን ወታደሮች እንደተያዙ እና እንዳትጨነቅ እንደነገራት ታስታውሳለች።

ነገር ግን የሚደውሉት ከሆስፒታል እንደሆነ ሲነግራት ተጨንቃ ሆስፒታል ሊገቡ የቻሉበት ሁኔታን ስትጠይቀው 57 ሰዎች እንደነበሩ እና ከእነርሱ መካከል አንዱ እንደሞተ ሌሎች ሁለት ደግሞ እንደቆሰሉ ነግሯት ነበር።

የያዟቸው ወታደሮች ‘ወንድሞቻችሁን ትታችሁ ወዴት ትሄዳላችሁ?’ በማለት የተጎዱት እስኪያገግሙ እና ሱዳንም ችግር ውስጥ ስላለች ለደኅንነታቸው ሲሉ እንደያዟቸው በመግለጽ እንዳትጨናነቅ ነገራት።

ነገር ግን ማትዮስ እና ጓደኞቹ ለሦስት ወራት ያህል ድምጻቸው ጠፍቶ ቆየ።

ረዘም ላለ ሳምንታት ወደ ባለቤቱ ሳይደውል የቆየው ማቲያስ፣ በድንገት ደውሎ “በጣም መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። ይለቁናል ብለን ስንጠብቅ ቆየን፤ እነርሱ ግን ዛሬ እና ነገ እያሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነን ያለነው። ጋሪሪስኬሪ በሚባል ቦታ 56 ሰዎች ታግተዋል ብላችሁ ድምጻችንን አሰሙልን። ስልክ ማግኘት በጣም ከባድ ስለሆነ መደወል አንችልም” ሲል እንደነገራት ለቢቢሲ ገልጻለች።

ከዚያ በኋላ ትምኒት ሰው እያፈላለገች እያለ ድንገት በሱዳን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ ቪድዮዎች ብዙ ሱዳናውያን ሲቀባበሉ እና አስተያየታቸውን ሲሰጡ መመልከቷን ትናገራለች።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀው ምስል ላይ የሱዳን ታጣቂዎች ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ሲደበድቧቸው እና ሲያንገላቷቸው ያሳያል።

ከእነዚህ መካከልም ትምኒትን ጨምሮ የተወሰኑትን ዘመዶቻቸው ሊለይዋቸው የቻሉ ሲሆን፣ ካናዳ የምትኖረው ኤርትራዊት ሃዋ መሐመድ ወንድሟን እና ጓደኛዋን በስቃይ ውስጥ ሆነው ቪዲዮው ላይ መለየት እንደቻለች ትናገራለች።

“ወንድሜ አብዱላህ መሐመድ አህመድ ይባላል። በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ሊቢያ ተነሳ፤ ከአዲስ አበባ ወጥቶ መተማ ላይ እያለ አግኝቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ሱዳን ገቡ ሲባል እንሰማለን፤ ግን አልተገናኘንም። ቆይተው ደውለው አንድ ሰው እንደተመታባቸውና ሕክምናውን እስኪጨርስ ከወታደሮቹ ጋር ተይዘናል ሲል ነገረን።”

ከዚህ በኋላ ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸው ሃዋ እና ትምኒት በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ተገናኝተው በሱዳን ውስጥ ስለሚገኙት ስደተኞች መረጃ በመለዋወጥ እና ነጻ የሚወጡበትን መንገድ መፈለግ ጀመሩ።

ባለቤት እና ወንድም ሱዳን ተዋጊ ኃይሎች የተያዙባቸው ሁለቱ ሴቶች ከአዲስ አበባ እና ከካናዳ ሆነው ስደተኞቹ ከየትኛው የሱዳን ኃይል ጋር እንደነበሩ ባለማወቃቸው ምን ማድረግ እንደሚችሉ ግራ ገብቷቸው መቆየታቸውን ይናገራሉ።

ነገር ግን በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተለቀቀው ቪዲዮ አማካኝነት በሱዳን ጦርነት ውስጥ አንደኛው ተፋላሚ ወገን ከሆነው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር እንደቆዩ መረዳታቸውን ሃዋ ትገልጻለች።

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ደላሎች ጋር የሚቀራረቡ ሰዎችን ሲያነጋግሩ፣ “ከእጃችን ወጥተው በመንግሥት ስር ገብተዋል። ጉዟቸው ሊቀጥል አይችልም። እነሱን ለማስለቀቅ ማድረግ የምችለው ነገር የለም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውም ትናገራለች።

“በቪዲዮዎቹ ላይ ሀበሾች፣ ሶማሊያውያን እና ሌሎችም ሲናገሩ ይሰማሉ፤ ነገር ግን ወንድሜን ጨምሮ አብረውት ከጠፉት መቶ በመቶ የለየኋቸው ኤርትራውያን አሉ” ትላለች።

በቪዲዮው ላይ የሱዳን ተወጊው ቡድን እነዚህን ስደተኞች ምርኮኞች ናቸው ብለው እያቀረቡ እንደሆነ የምትናገራው ሃዋ፤ ባሏ እና በቪዲዮው ላይ የተመለከተቻቸው ግን ወደ ሊቢያ ለመድረስ ከጥቂት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ የተነሱ ስደተኞች ትላለች።

“. . . እነሱ 53 ምርኮኞችን ይዘናል እያሉ የሚለቁት ቪዲዮ አለ፤ ግን እነዚያ 56 ነበሩ ሦስቱ የት አሉ? ወጣቶቹ ስደተኞች ናቸው ግን እንደጠላት ነው የሚያይዋቸው። ተከፍሏቸው ከጠላቶቻችን ከሱዳን ጦር ጋር ሲሠሩ ነበር እያሉ ነው። ሴቶችም አብረዋቸው እንዳሉ ቪዲዮው ላይ ይታያሉ” ትላለች ሃዋ።

አዲስ አበባ ያለችው ትምኒት ባሏ እንዲሁም ካናዳ የምትገኘው ሃዋ ወንድምን ጨምሮ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የሚገኙት ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ወጣቶች በጦርነቱ ውስጥ ምንም ሚና እንደሌላቸው ይናጋራሉ።

ከ50 በላይ የሚሆኑት እና በሱዳን ተፋላሚ ቡድን እንደምርኮኛ ተይዘው የሚገኙት ስደተኞች አሁን በትክክል የሚገኙበት ቦታ እና ሁኔታ የማይታወቅ ሲሆን፣ ደኅንነታቸውም አስጊ እንደሆነ ቤተሰቦቻቸው ይናጋራሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(BBC)